በመድፈር የተወነጀሉት ፓስተር ወደ ቦታቸው መመለስ በናይጀሪያ ቁጣን ቀሰቀሰ

ባይዶን ፋቶይንቦ

የፎቶው ባለመብት, Biodun Fatoyinbo instagram

በመድፈር የተወነጀሉት ባይዶን ፋቶይንቦ የተባሉት ታዋቂው ናይጀሪያዊ ፓስተር ከአንድ ወር በኋላ ወደ ቤተ ክርስቲያናቸው መመለስ ቁጣን ቀስቅሷል።

በናይጀሪያ መዲና አቡጃ ኮመን ዌልዝ ኦፍ ዛየን አሴምብሊ የሚባል ቤተክርስቲያን መስራቹ ፓስተር፤ ባለፈው ወር ነበር አንዲት የፎቶ ባለሙያ ታዳጊ እያለች በፓስተሩ ሁለት ጊዜ መደፈሯን የገለፀችው።

ፓስተሩ በፍፁም አልደፈርኳትም በሚል ያስተባበሉ ሲሆን ፖሊስ ጉዳዩን እየመረመረ መሆኑም ተገልጿል።

ይህ ውንጀላ ከቀረበባቸው በኋላ ለተወሰነ ጊዜ ከቤተ ክርስቲያኗ የመራቅ ውሳኔያቸውን ያሳወቁት ፓስተሩ፤ ተቃዋሚዎች ግለሰቡ ከኃላፊነቱ እንዲነሳ ሰልፍ በመውጣት ግፊት ማድረጋቸውን ተከትሎ ነው።

በትናንትናው ዕለት እሁድ የፀሎት ፕሮግራም ያደረጉት ፓስተሩ "ጥቃቅን ድሎች" በሚልም ርዕስ ተናግረዋል።

ፓስተሩ በንግግራቸው ክርስቲያኖች ሁልጊዜም ቢሆን መከራን ይቀበላሉ፤ ነገር ግን አምላክ ድልን ያረጋግጣል ብለዋል።

" እንደ አንድ ክርስቲያን ተቃውሞ ያጋጥማል፤ ቅዱሱና ታማኙ አምላክ ጠላቶች ካሉት በእርግጠኛነት አንተም አለህ" ብለዋል።

ፓስተሩን በመድፈር የወነጀለችው የፎቶ ባለሙያ ሚስ ዳኮሎ የክሷ ቪዲዮ በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የታየ ሲሆን ናይጀሪያ ላይ ለተነሳውም የ'ሚ-ቱ' እንቅስቃሴ መነሻ ሆኗል ተብሏል።

ፓስተሩ ወደ መንበራቸው መመለሳቸውን ተከትሎ ስማቸው በትዊተር ላይ በከፍተኛ ሁኔታ እየተነሳ ሲሆን ብዙዎችም በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ድንጋጤያቸውንና ብስጭታቸውን ገልፀዋል፤ ተስፋ አስቆራጭ ነው በማለትም ሁኔታውን የገለፁት አልታጡም።