ቀብር አስፈጻሚዎች ከሞት አስነሳሁ ያለውን ፓስተር ሊከሱ ነው

ፓስተር አልፋ ሉካው ከሞት አስነሳሁት ካለው ግለሰብ ጋር

የፎቶው ባለመብት, ALPH LUKAU/FACEBOOK

የምስሉ መግለጫ, ፓስተር አልፋ ሉካው ከሞት አስነሳሁት ካለው ግለሰብ ጋር

ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የቀብር አስፈጻሚዎች የሞተን ሰው አስነሳሁ ያለን አንድ እራሱን ነብይ ብሎ የሚጠራን ግለሰብ ፍርድ ቤት እናቆማለን እያሉ ነው።

ቀብር አስፈጻሚዎቹ እንደሚሉት ፓስተር አልፋ ሉካው ከሞት ማስነሳት እንደሚችል ለምዕመናኖቹ ለማሳየት ባቀናበራው ሀሰተኛ ድርጊት ውስጥ ሳያውቁ እንዲሳተፉ ስላደረጋቸው ነው ጉዳዩን ወደ ሕግ ለመውሰድ የወሰኑት።

በበርካታ ሰዎች እየታየ ባለው ተንቀሳቃሽ ምስል ላይ ፓስተር አልፋ ሉካው ከፊቱ ከተቀመጣ የሬሳ ሳጥን ውስጥ ያለን አስከሬን "ተነስ" በማለት ከፍ ባለ ድምጽ ሲያዝ፣ ሳጥን ውስጥ ያለው ግለሰብ ሲነሳና ምዕመኑም በደስታ ሲጮሁ ይታያል።

የቀብር አስፈጻሚዎቹ ክስም ከዚሁ ጋር የተያያዘ ነው። ምክንያታቸውንም ሲያስቀምጡ በዚህ የተቀነባበረ ድርጊት ውስጥ ተሳታፊ እንድንሆን ተደርገናል ነው የሚሉት።

በዚህ ድርጊትም ደቡብ አፍሪካ ውስጥ ጆሃንስበርግ አቅራቢያ የሚገኘው የፓስትር ሉካው ቤተክርስቲያን ከበርካቶች ውግዘት የገጠመው ሲሆን መሳለቂያም ሆኗል።

"እንዲህ አይነት ተአምር የለም" ሲል የደቡብ አፍሪካ የባህል፣ ሃይማኖትና የቋንቋ ማሰፋፋትና ጥበቃ ኮሚሽን ለሃገሪቱ ብሔራዊ የቴሌቪዥን ጣቢያ ገልጿል።

ጨምሮም "እንዲህ አይነት ነገሮች ተስፋ መቁረጥ ከገጠመው ሕዝብ ላይ ገንዘብ ለመሰብሰብ የሚፈጥሩት ነው" ብሏል።

ሦስት የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ሳያውቁ በዚህ ድርጊት ውስጥ እንዲሳተፉ በመደረጋቸው በመልካም ስማችን ላይ ጉዳት ደርሷል በሚል ሕጋዊ እርምጃ እንደሚወስዱ ተናግረዋል።

ሦስቱ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅቶች ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገሩት የቤተክርስቲያኑ ተወካዮች በተለያየ መንገድ አታለው በድርጊቱ ውስጥ እንድንሳተፍ አድርገውናል ብለዋል።

"የሟች ቤተሰብ ነኝ" የሚል ግለሰብ ወደ አንደኛው የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ቀርቦ ከሌላ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት ጋር አለመግባባት ውስጥ እንደገቡ መናገሩን፤ በተጨማሪም በግል መኪናቸው ላይ የሌላኛውን የቀብር አስፈጻሚ ስም በመለጠፍ እውነተኛ ለመምሰል መሞክራቸው ተገልጿል።

ለዚህ ድርጊት ጥቅም ላይ የዋለው የሬሳ ሳጥንም ከሌላ የቀብር አስፈጻሚ ድርጅት መምጣቱም ተነግሯል።

'ሃሌሉያ ሚኒስትሪስ ኢንተርናሽናል' በመባል የሚታወቀው የፓስተር ሉካው ቤተክርስቲያን በጉዳዩ ላይ ምላሽ እንዲሰጥ በቢቢሲ ለቀረበለት ጥያቄ ፈቃደኛ ሳይሆን ቀርቷል።

ይህ ነገር ይፋ ከወጣ በኋላም በፓስተሩ አማካይነት ከሞት ተነስቷል ስለተባለው ሰው ዜና ቤተክርስቲያኑ ማስተባበያ እየሰጠ ነው። ሞተ የተባለው ግለሰብ ወደ ስፍራው ሲመጣ በህይወት እንደነበረም እየተነገረ ነው።

በዚሁ ዙሪያም 'ሃሌሉያ ሚኒስትሪስ ኢንተርናሽናል' ለመገናኛ ብዙሃን እንደተናገረው "በእግዚአብሔር የተጀመረውን ግለሰቡን ከሞት የማስነሳት ተአምር ፓስተር ሉካው አጠናቆታል" ሲል ምላሽ ሰጥቷል።

ይህ የአንድን ግለሰብ ከሞት መነሳትን የሚያሳየው ቪዲዮ በስፋት መሰራጨትን ተከትሎ በሃሰተኛ ፓስተሮች ዙሪያ ሃገር አቀፍ ክርክር እየተደረገ ሲሆን ድርጊቱም ከቀደምት የዕምነት ተቋማት በኩል ውግዘትን አስከትሏል።