'የኤርትራ ወታደሮች ስለመውጣታቸው ምንም ማረጋገጫ የለም'

ወታደሮች

የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ስለመውጣታቸው የሚያመለክት ምንም አይነት ማስረጃ እንደሌለ የተባበሩት መንግሥታት ከፍተኛ የሰብአዊ እርዳታ ባለስልጣን ለጸጥታ ጥበቃ ምክር ቤት ተናገሩ።

ማርክ ሎውኮክ በግጭት ከተጎዳው የሰሜን ኢትዮጵያ ክፍል "የኤርትራ ወታደሮች መውጣታቸውን የሚያመለክት ነገር የተባበሩት መንግሥታት ተቋማትም ሆኑ ሌሎች ከእኛ ጋር አብረው የሚሰሩ የሰብአዊ እርዳታ ድርጅቶች አላዩም" ብለዋል።

በጸጥታው ጥበቃ ምክር ቤት የአሜሪካ መልዕክተኛ የሆኑት ሊንዳ ቶማስ ግሪንፊልድም በዚሁ ጊዜ የአስገድዶ መድፈርና ጾታዊ ጥቃቶችን የተመለከቱ ሪፖርቶችን ተከትሎ የኤርትራ ወታደሮች "በአስቸኳይ" ከኢትዮጵያ ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

መልዕክተኛዋ በጽህፈት ቤታቸው በኩል ውይይቱን በተመለከተ ባወጡት መግለጫ የኢትዮጵያው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተፈጸሙ ከተባሉት የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ጥቃቶችና ግድያዎች አንጻር ድርጊቱን የፈጸሙትን በሙሉ ተጠያቂ እንደሚያደርጉ ያሳዩትን ቁርጠኝነት አድንቀዋል።

የኤርትራ መንግሥትም ተመሳሳይ አቋም መያዝ አለበት ብለዋል።

"በተባበሩት መንግሥታት የሰብአዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽንንና በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን አማካይነት ትግራይ ውስጥ የሚካሄደው ምርመራ በበጎ የምንመለከተው ሲሆን በፍጥነትና በዝርዝር እንዲከናወን እንጠይቃለን" ብለዋል።

የሊንዳ ቶማስ መግለጫው ጨምሮም "ከታማኝ ምንጮች የሚወጡ ዘገባዎች የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያ ሠራዊት ልብስን በመልበስ ትግራይ ውስጥ ለመቆየት እየሞከሩ እንደሆነ" አመልክተው ክልሉን ለቀው እንዲወጡ ጠይቀዋል።

ኤርትራ ኢትዮጵያ ውስጥ በወታደሮቿ ተፈጽመዋል የተባሉትን የመብት ጥሰቶች የፈጠራ ክስ በማለት ቀደም ሲል ውድቅ ማድረጓ ይታወሳል።

ትግራይ ውስጥ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ ድንበር ተሻግረው ገብተዋል የተባሉት የኤርትራ ወታደሮች የተለያዩ ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች መፈጸማቸውን በተመለከተ ክስ ሲቀርብባቸው ቆይተዋል።

ኢትዮጵያና ኤርትራ ግን ለወራት ወታደሮቹ ወደ ትግራይ ክልል መግባታቸውን በተመለከተ ይወጡ የነበሩትን ሪፖርቶች ሲያስተባብሉ የቆዩ ሲሆን፤ በመጨረሻም በመጋቢት ወር ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች መኖራቸውን ለአገሪቱ ፓርላማ ተናግረው ነበር።

ከቀናት በኋላም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ኤርትራ ተጉዘው ከፕሬዝዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ከተናጋገሩ በኋላ ወታደሮቹ ከኢትዮጵያ የድንበር አካባቢዎች ለቀው በመውጣት የኢትዮጵያ ሠራዊት ስፍራዎቹን እንዲቆጣጠር ከስምምነት መድረሳቸውን ገልጸው እንደነበር ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ውስጥ ወታደራዊ ግጭት ከተከሰተ አምስት ወራት የተቆጠሩ ሲሆን በዚህ ጊዜ የተባበሩት መንግሥታት በጉዳዩ ላይ ለመምከርና መግለጫ ለመውጣት ምክር ቤቱ የትናንቱን ጨምሮ ለአምስት ጊዜ ተሰብስቦ ተወያይቷል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ማርክ ሎውኮክ ግጭቱ እንዲቆምና የበለጠ የሰብአዊ እርዳታ አቅርቦት መስመር እንዲመቻች ጥያቄ አቅርበዋል።

ትግራይ ውስጥ ግጭቱ የተቀሰቀሰው ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በመንግሥት ጦር ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ወታደራዊ እርምጃ እንዲወሰድ ካዘዙ በኋላ ነበር።

በትግራይ ክልል ውስጥ በተካሄደው ወታደራዊ ግጭት ሳቢያ ምን ያህል ሰዎች እንደሞቱ የሚታወቅ ነገር ባይኖርም አሃዙ በበርካታ ሺዎች ሊሆን እንደሚችል የበጎ አድራጎት ድርጅቶች ይናገራሉ።

ከዚህ ባሻገርም በግጭቱ ውስጥ ተሳታፊ በሆኑ ኃይሎች ግድያዎች፣ ጾታዊ ጥቃቶች፣ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች፣ ዘረፋና የንብረት ውድመቶች መፈጸማቸውን የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንና የተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ባወጧቸው ሪፖርቶች ላይ አመልከተዋል።

በተጨማሪም የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር እንዳለው በግጭቱ ሳቢያ ከሁለት ሚሊዮን ሰዎች በላይ ለመፈናቀል የተዳረጉ ሲሆን፤ ከአራት ሚሊዮን በላይ የሚሆኑት ደግሞ የሰብአዊ እርዳታ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው ናቸው።