ጠ/ሚ ዐቢይ በትግራይ የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፈፀሙ እንደሚጠየቁ ገለፁ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE/FB

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ትግራይ ውስጥ ከተካሄደው ዘመቻ ጋር ተያይዞ ተፈጸሙ የተባሉት በደሎች "የተጋነኑ ቢሆኑም" የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል አሉ።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ ማክሰኞ፣ በተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ማብራርያ በሰጡበት ወቅት እንደተናገሩት፣ ትግራይ ውስጥ የሰብአዊ መብት ጥሰትና በደሎች መፈጸማቸውን የሚያመለክቱ መረጃዎች መኖራቸውን ጠቅሰው መንግሥታቸው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ላይ እርምጃ ይወስዳል ብለዋል።

"እኛ ወታደሩን የላክነው ወንጀለኞችን እንዲቆጣጠር እንጂ እንዲደፍር አይደለም። በዚህ ወንጀል የተሰማራ ወታደር ካለ በሕግ ተጠያቂ ይደረጋል" ብለዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል ውስጥ ተፈጸሙ የተባሉትን የመብት ጥሰቶች በተመለከተ "ከፍተኛ ግነት እና ፕሮፖጋንዳ አለ" በማለት "የሚጋነነውን ነገር እንዳለ ሆኖ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት ተፈጽሟል" በማለት "የተፈጸመው ጥፋት አንድ እንኳን ቢሆን ተጠያቂነት ይኖራል" ሲሉ ተናግረዋል።

ከዚህ አንጻር ከአገር መከላከያ ሠራዊት አመራሮች ጋር ግምገማ ማድረጋቸውን የጠቀሱት ጠቅላእ ሚኒስትር ዐብይ "እንዲጠብቃቸው የተሰማራውን ሴቶች የደፈረና ሌላ ጉዳት ያደረሰ ማንኛውም ኃይል ተጠያቂ ይሆናል" ብለዋል።

የኤርትራ ሠራዊት

በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ከትግራይ ክልል ግጭት ጋር ተያይዞ በተደጋጋሚ ሲነሳ ለነበረው የኤርትራ ሠራዊት ተሳትፎ ምላሽ ሰጥተዋል።

በዚህም የኤርትራ ሠራዊት በድንበር አካባቢ "የደኅንነት ስጋት እንዳለበት" ገልጾ በዚያው አካባቢ ሠራዊቱ እንዳለ ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ፣ ለዚህም ምክንያቱ በኢትዮጵያ ሠራዊት ላይ በህወሓት የተፈጸመው ጥቃት እንደሆነ ተናግረዋል።

ጨምረውም የኢትዮጵያ ሠራዊት ከጀርባው ጥቃት እየተፈጸመበት የድንበር አካባቢውን መጠበቅ አስቸጋሪ ስለሆነበት የህወሓት ኃይሎችን ለመዋጋት ወደ ሌሎች የትግራይ አካባቢዎች በመንቀሳቀሱ ክፍተት እንደተፈጠረና የኤርትራ መንግሥትም በዚህ ክፍተት ጥቃት እንዳይፈጸምበት በመስጋቱ ወደ ስፍራዎቹ መግባቱን ገልጸዋል።

ነገር ግን ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኤርትራ ሠራዊት በየትኞቹ የኢትዮጵያ አካባቢዎች እንደሚገኝ አልተናገሩም። ቢሆንም ግን የኢትዮጵያ ሠራዊት ሌላውን ተልዕኮ ሲያጠናቅቅና አካባቢዎቹን መቆጣጠር ሲችል በቀጣዩ ቀን የኤርትራ ኃይሎች ከስፍራው እንደሚወጡ ተናግረዋል።

ትግራይ ውስጥ በኤርትራ ሠራዊት ተፈጸሙ ከተባሉ ግድያዎችና የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ አሜሪካንና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅትን ጨምሮ የተለያዩ አገራትና ዓለም አቀፍ ተቋማት ሠራዊቱ ከክልሉ እንዲወጣ በተደጋጋሚ ሲተይቁ ቆይተዋል።

"የኤርትራ መንግሥት ለሚያቀርበው የደኅንነት ስጋት ዋስትና መስጠት አንችልም" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ "ምክንያቱም ከኋላ የሚወጋን ኃይል አለ" ሲሉ ተናግረዋል።

በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ተሟጋቾችና ድርጅቶች በተደጋጋሚ በሚወጡ ሪፖርቶች ላይ የኤርትራ ሠራዊት በትግራይ ክልል ውስጥ አስከፊ የሰብአዊ መብት ጥሰት፣ ግድያና ዘረፋዎችን መፈጸሙ ሲገለጽ መቆየቱ አይዘነጋም።

ከዚሁ ጋር በተያያዘ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የኤርትራ ወታደሮች የኢትዮጵያን ድንበር አልፈው የሚያደርሱትን ጥፋቶች መንግሥታቸው ፈጽሞ አይቀበለውም ብለዋል።

ይህንን በሚመለከት ከኤርትራ መንግሥት ጋር መነጋገራቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ የኤርትራ መንግሥት ወታደሮቹ አደረሱት ስለሚባለው በደሎችና ዘረፋን በተመለከተ ጥፋቱን በሚፈጽሙ ወታደሮቹ ላይ እርምጃ እንደሚወስድ መግለጹን ተናግረዋል።

ቀደም ሲል የኢትዮጵያም ሆነ የኤርትራ መንግሥት የኤርትራ ሠራዊት በኢትዮጵያ ግዛት ውስጥ ስለመገኘቱ የሚወጡ ሪፖርቶችን ሲያስተባብሉ እንደነበር ይታወሳል።

በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ ቀውሱ በተከሰተበት ጊዜ ከኤርትራ በኩል ስለተደረገላቸው ድጋፍ የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የመከላከያ ሠራዊት ክህደት በተፈጸመበት በወቅት የኤርትራና ሕዝብ እና መንግሥት ድጋፍ ሰጥቷል" በማለት በዚህም የኤርትራ መንግሥት "የምን ጊዜም የኢትዮጵያ ባለውለታ ነው" በማለት አመስግነዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም የኤርትራ መንግሥት፣ የኤርትራ ዕጣ ፈንታ ከኢትዮጵያ እና ከትግራይ ሕዝብ ጋር የተሳሰሰረ መሆኑን እንደሚያምን ገልፀዋል።

ሰብአዊ እርዳታ

በትግራይ ክልል በተካሄደው ጦርነት ወቅት በርካታ መሠረተ ልማቶች መውደማቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ይህንን መልሶ ለመገንባት መንግሥት ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ማውጣቱን ተናግረዋል።

አክለውም በግጭቱ ምክንያት ተፈናቅለው የሰብዓዊ እርዳታ ጠባቂ ለሆኑ 4.2 ሚሊዮን ለሚደርሱ ሰዎች ከ92 በላይ የእርዳታ መስጫ ጣብያዎች መንግሥት ከፍቶ እርዳታ እያረበ መሆኑን ገልጸዋል።

ከዚሁ ጋር በማያያዝም በርካታ የውጭ እርዳታ ሰጪዎች ክልሉ ላልተገደበ የተራድኦ አቅርቦት ክፍት ይሁን ሲሉ የቆዩ ቢሆንም ከተከፈተ በኋላ ግን ገብተዉ እርዳታ እየሰጡ አለመሆናቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አንስተዋል።

የሰብአዊ መብት ጥሰቶች

ግጭቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በትግራይ ክልል 30 ሺህ የሚደርሱ እስረኞች ሆን ተብሎ መፈታታቸውን የጠቀሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከእነዚህ መካከል 10 ሺህ የሚሆኑት በመቀሌ ውስጥ መሆናቸውን ጠቅሰዋል።

የመከላከያ ሠራዊት የተለያዩ የትግራይ ከተሞችን ከተቆጣጠረ በኋላ በአንዳንድ ያልተደራጁ ግለሰቦች ጥቃቶች እንደተጸጸመበት ያስታወሱት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ይህንን ተከትሎ በተፈጠረ ቁጣ የተከሰቱ ችግሮች አሉ ብለዋል።

በክልሉ በተደረገው "የሕግ ማስከበር ዘመቻ" ወቅት የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ያቀረቧቸው ጥቃቶችና በደሎች መፈፀማቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፣ ይህንንም ከመከላከያ ከፍተኛ ኃላፊዎች ጋር በመሆን መገምገማቸውን ተናግረዋል።

ከአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ሆኖ በትግራይ ውስጥ የመድፈርና የዘረፋ ወንጀል የፈፀመ "ማንኛውመ ወታደር በሕግ ይጠየቃል" ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ጀግኖችን እንሸልማለን ጥፋተኞችን በሕግ እንጠይቃለን" ብለዋል።

ኦነግ-ሸኔ

በአንዳንድ የአገሪቱ አካባቢዎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ከሚፈጸሙ ጥቃቶችና ግጭቶች ጋር በተያያዘ ስሙ የሚነሳው ኦነግ-ሸኔ የተባለውን ታጣቂ ኃይል ጠቅላይ ሚኒስትሩ "የሰው ጠላት ነው" በማለት ከማንም በላይ በርካታ ኦሮሞዎችን ገድሏል ብለዋል።

"ኦነግ-ሸኔ እየገደለ ያለው አማራን ብቻ አይደለም፤ ኦነግ-ሸኔ ከሁሉም በላይ የገደለው አሮሞን ነው።"

ቡድኑን የህወሓት ተላላኪ ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ "ቡድኑ ሰው የሚድገል የሰው ጠላት እንጂ ብሔርን ለይቶ ብቻ የሚገድል አይደለም" ብለዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በትግራይ "የሕግ ማስከበር እርምጃ በተወሰደበት ወቅት 300 የሚደርሱ የኦነግ-ሸኔ አባላት ሲሰለጥኑ ተገኝተዋል" ብለዋል።

በዚህ ዓመት ለሁለተኛ ጊዜ ወደ ምክር ቤቱ የቀረቡበት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ፤ በዛሬው የምር ቤቱ ስብሰባ በአገሪቱ የ10 ዓመት የልማት ዕቅድ ላይ እንዲሁም በተለያዩ በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ከተወካዮች ምክር ቤት አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች መልስና ማብራሪያ ሰጥተዋል።