በዋግኽምራ አስተዳደር ፃግብጂ የተከሰተው ምን ነበር?

ካርታ

በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ውስጥ ባለፈው ሳምንት መጋቢት 09/2013 ዓ.ም በተፈጸመ ጥቃት በርካታ ሰዎች ሲሞቱ በሌሎች ላይ የመቁስል ጉዳት መድረሱን የአካባቢው ባለስልጣንና ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናገሩ።

ጥቃቱ የተፈጸመበት የፃግብጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሄኖክ ነጋሽ ለቢቢሲ የ76 ሰዎች ህይወት መጥፋቱ እንደተረጋገጠ ገልጸው ሰላማዊ ሰዎችም በጥቃቱ ሰለባ ሆነዋል ብለዋል።

ይህ አሃዝ እስከ ትናንት ድረስ ያገኙት መሆኑን ያመለከቱት ዋና አስተዳዳሪው ቁጥሩ ከዚህም ከፍ ሊል እንደሚችል ተናግረዋል።

ከፍተኛ የሰው እና የንብረት ጉዳት ከደረሰባቸው የዞኑ ወረዳዎች መካከል አንዷ የሆነችው ፃግብጂ እና የወረዳው መቀመጫ የሆነችው የጻታ ከተማ እንደነበሩ ነዋሪዎች ተናግረዋል።

የዋግኽምራዋ ፃግብጂ ወረዳ በስተሰሜን የአማራ ክልልን ከትግራይ ጋር የምታዋስን ስትሆን፤ ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት ከትግራይ ክልል ድንበር እስከ ወረዳዋ ዋና ከተማ ጻታ ድረስ ያለው ርቀት ከ10 ኪሎ ሜትር ያልበለጠ ነው።

ባለፈው ሳምንት መጋቢት 09/2013 ዓ.ም ሐሙስ ዕለት ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ታጣቂዎች በከተማዋ ላይ በፈጸሙት ጥቃት ስለደረሰው ጉዳት የተለያዩ ነዋሪዎች፣ የተለያየ መረጃ ቢሰጡም ነገር ግን በርካታ የሚባል የሰው ህይወት ማለፉን ይናገራሉ። በተጨማሪም ውድመትና ዝርፊያ እንደተከሰተ ነዋሪዎች ገልጸዋል።

በጻታ ከተማ በመንግሥት ሠራተኝነት ለዓመታት በመስራት ላይ ያሉት አቶ ሕሉፍ ሰለሞን፣ ችግሩ ሲፈጠር በቦታው እንደነበሩ በመግለጽ "ከተማዋ ባልተጠበቀ ሁኔታ በተኩስ መናጥ የጀመረችው ሐሙስ ከሌሊቱ 11፡00 ጀምሮ ነበር" በማለት ያስታውሳሉ።

ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች በዚሁ ዕለት በከተማዋ ውስጥ በሁለት አቅጣጫ ተኩስ በመክፈት ከተማዋንና ነዋሪዋን ሽብር ውስጥ ማስገባታቸውን የሚገልጹት አቶ ሕሉፍ "ድርጊቱ ድንገተኛ ነበር" ብለዋል።

ጨምረውም በአካባቢው የአማራ ክልል ልዩ ኃይልም ሆነ የመከላከያ ሠራዊት እንዳልነበር ጠቅሰው፣ ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመከላከል ጥረት ያደረጉት ከተማዋን ይጠብቁ የነበሩ እና ኋላ ቀር መሳሪያ የታጠቁት የአካባቢው ሚሊሻ አባላት እንደነበሩ ተናግረዋል።

ጨምረውም "ሚሊሻዎቹ የሎጅስቲክስ አቅርቦት ስላልነበራቸው የያዙትን ጥይት እስኪጨርሱ ድረስ ተዋግተው አብዛኛዎቹ ተሰውተዋል" የሚሉት አቶ ሕሉፍ፤ በእዚህ ሳቢያም የወረዳው የሰላምና ደኅንነት ጽህፈት ቤት ኃላፊ የሆኑት ኮሎኔል ጠቅልሌ ጌታሁንን ጨምሮ ብዙዎች መሞታቸውን ተናግረዋል።

ሌሎች ሁለት ነዋሪዎችም ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ሚሊሻዎች በተሻለ የታጠቁና በቁጥርም በርከት ያሉ ስለነበሩ ጉዳቱ የከፋ እንደነበር አመልክተዋል።

ጨምረውም በዚህም ጥቃት ከሚሊሻዎቹ በተጨማሪ በአካባቢው ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ነዋሪዎች ላይ ጉዳት መድረሱን ለቢቢሲ አስረድተዋል።

የፃግብጂ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ሄኖክ ነጋሽ "ጥቃቱ የተፈጸመው በህወሓት ታጣቂዎች" እንደሆነ በመግለጽ ጥቃቱን ለመከላከል ሚሊሻዎችና ግለሰቦች ጥረት ማድረጋቸውን አመልክተዋል።

ይህንን ጥቃት በተመለከተ የአማራ ክልል አስካሁን የሰጠው ይፋዊ መግለጫ ባይኖርም የክልሉን የኮምዩኒኬሽንና የጸጥታ ኃላፊዎችን ምላሽ ለማግኘት ቢቢሲ ያደረገው ጥረት አልተሳካም።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ ከአካባቢው ሚሊሻዎች በተጨማሪ ሰላማዊ ሰዎችን ኢላማ አድርገው እንደነበር አቶ ሄኖክ ጠቅሰው "ወደ ከተማዋ ከገቡ በኋላ በከተማው ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ቢሮዎችንና የግል ተሽከርካሪዎችን አውድመዋል እንዲሁም አቃጥለዋል" ብለዋል።

በከተማው በሚገኙ የጤና ጣቢያና የእርዳታ ማከፋፈያ ላይም ጥቃት ከደረሰ በኋላ በቦታዎቹ በነበሩ የህክምና ቁሳቁሶች፣ በአልሚ ምግቦችና በእርዳታ እህል ላይ ዘረፋ እንደተፈጸመበት አቶ ሕሉፍ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ጥቃት ፈጻሚዎቹ በፃግብጂ ወረዳ ቢያንስ በስድስት ቀበሌዎች ውስጥ ያገኙትን ንብረት ሁሉ ያወደሙ ሲሆን፣ ለመንገድ ሥራ ተሰማርተው የነበሩ እንደ ሎደር እና ኤክስካቫተር እና ሌሎች ማሽኖችን ከነካምፖቻቸው አቃጥለዋቸዋል ብለዋል።

ዋና አስተዳዳሪው አቶ ሄኖክ እንደሚሉት ደግሞ የጥቃት ፈጻሚዎቹ ዘረፋና ውድመት ያጋጠመው "በከተማዋ ውስጥ ብቻ ሳይሆን በገጠሩ አካባቢም በአርሶ አደሩ ቤት እየገቡ በሬና ፍልን ጨምሮ፤ ገንዘብ፣ ቡና፣ ስኳር፣ ጨው፣ በርበሬና ማር ዘርፈዋል" ብለዋል።

ነዋሪዎች ከፍተኛ ነው ያሉት የዚህ ጥቃት አድራሾች ቁጥር እጅግ ብዙ መሆኑንና የተለያየ አይነት ወታደራዊና የሲቪል ልብስ እንደለበሱመልበሳቸውንም ተናግረዋል።

በአማራ ክልል በዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በፃግብጂ ወረዳ ውስጥ ለበርካቶች ህይወት መጥፋትና በንብረት ላይ ለደረሰው ውድመት ምክንያት የሆነው ጥቃት የቆመው መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው መግባቱን ተከትሎ እንደነበር ነዋሪዎች ገልጸዋል።

"በማይጨው በኩል የነበረው የመከላከያ ሠራዊት ወደ ስፍራው በመድረስ ከተማዋን አረጋገግቷል" የሚሉት አቶ ሕሉፍ "መከላከያ መጣ ሲባል ከተማዋን ለቅቀው ወጡ፣ ከመከላከያ ጋር የተደረገ ተኩስም አልነበረም" ብለዋል።

በአሁኑ ጊዜ ወደ ከተማዋ የክልሉ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሠራዊት በመግባቱ ጥቃቱን በመሸሽ ወደ በረሃ አካባቢ የሄደው ነዋሪ በመመለስ ላይ ሲሆን ሰላማዊው እንቅስቃሴ እየተመለሰ መሆኑንም ነዋሪዎች ተናግረዋል።

በአካባቢውም በአሁኑ ወቅት ምንም አይነት የተኩስ ድምጽ ባይኖርም፤ በተፈጸመው ድንገተኛ ጥቃት ምክንያት የመማር ማስተማር ሂደትና የመንግሥት ሥራ ለጊዜው ተቋርጧል።

በአማራ ክልል ስር የሚገኘው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን በአስቸኳይ ጊዜ ስር በሚገኘውና የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በህወሓት ኃይሎች ላይ "ሕግን ማስከበር" ያለውን ወታደራዊ ዘመቻ ካካሄደበት የትግራይ ክልል ጋር በቅርብ ርቀት የሚጎራበት አካባቢ ነው።