"የተፈጸመው ጥቃት አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው" የአማራ ክልል

በአማራ ክልል ውስጥ በሚገኙት በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬና በክልሉ የኦሮሞ ብሔረሰብ ዞን ጅሌ ጥሙጋ አካባቢዎች በንጹሐን ላይ የተፈጸመው ጥቃት አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው ሲል የክልሉ መስተዳደር ገለጸ።
የአማራ ክልል መስተዳደር ክስተቱን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ በጥቃቱ የሰዎች ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን ጠቁሞ "በንጹሐን ላይ የተፈፀሙው ይህ ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው" ብሏል።
ባለፈው አርብ ምሽት ከሦስት ሰዓት ጀምሮ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን፤ ኤፍራታና ግድም ወረዳና አጣዬ ከተማ ውስጥ በታጣቂዎች በተፈጸመ ጥቃት የሰላማዊ ሰዎች ሕይወት ማለፉን ነዋሪዎችና የአካባቢው ባለሥልጣን ለቢቢሲ ገልጸው ነበር።
የኤፍራታና ግድም ወረዳ የሠላምና የሕዝብ ደኅንነት ጽ/ቤት ኃላፊ እንዲሁም ምክትል አስተዳዳሪ የሆኑት አቶ ሰለሞን አልታየ እስከ ቅዳሜ ረፋድ ድረስ የአራት ሰዎች ሕይወት ማለፉን መመልከታቸውን የተናገሩ ሲሆን፤ ከዚያ በኋላ ከአካባቢው የሚወጡ መረጃዎች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከዚህም ከፍ እንደሚል እያመለከቱ ነው።
የክልሉ አስተዳደር ባወጣው መግለጫ ላይ እንዳመለከተው ለተፈጠረው ግጭት ምክንያቱ ሐሙስ መጋቢት 9/2013 ዓ.ም ምሽት "ጅሌ ጥሙጋ ውስጥ በግለሰቦች መካከል በተፈጠረ ጠብ ምክንያት አንድ ሰው ህይወት መጥፋት" ለው ብሏል።
ይህንንም ተከትሎ በአገር ሽማግሌዎችና በሐይማኖት አባቶች አማካይነት እርቅ ተፈጽሞ እንደነበር ጠቅሶ ነገር ግን "የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ የሆኑ አካላት እርቀ ሰላም ወርዶ መፍትሔ ያገኘውን ክስተት ምክንያት በማድረግ" ጥቃቱ መፈጸሙን ገልጿል።
በዚህም ከአርብ መጋቢት 10/2013 ዓ.ም ጀምሮ "አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ያለው የታጠቀ ኃይል በአጎራባቹ የሰሜን ሸዋ ዞን አጣየ ከተማና አካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ ነውረኛ የሆነ ጥቃት ተፈጽሟል" ብሏል።
ክልሉ እሁድ እለት ባወጣው መግለጫ ላይ ግን በክስተቱ ጉዳት የደረሰባቸውን ሰዎች መጠን አልገለጸም።
ጥቃቱ በአጣዬ ከተማ ዙሪያ ቀበሌ 01፣ 02 እና 03 እንዲሁም በኤፍራታና ግድም ወረዳ በሚገኙ አላላ እና ማጀቴ ቀበሌዎች አርብ ምሽት መጀመሩንና የከተማው ነዋሪ ላይ ከባድ ድንጋጤን ፈጥሮ እንደነበር ቢቢሲ ያናገራቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በአካባቢው ከባድ የተኩስ ድምጽ መሰማት የጀመረው ቀደም ብለው ከነበሩት ቀናት ጀምሮ እንደነበር የአካባቢው ነዋሪዎችና ኃላፊው ለቢቢሲ ገልጸው፤ ነገር ግን ይህ ሁኔታ ከሠርግና ከሌሎች ባላህላዊ ሥነ ሥርዓቶች ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል በማሰብ ችላ ተብሎ መቆየቱን አስረድተዋል።
አርብ ምሽት የነበረው ተኩስ ግን ከነፍስ ወከፍ የጦር መሳሪያ ከፍ ያለና ከባድ እንደነበር ምክትል አስተዳዳሪው አቶ ሰለሞን አልታየ ገልጸው፤ የተከፈተውን ተኩስ ተከትሎ የአጣዬ ከተማ 01 ቀበሌ "ሙሉ በሙሉ በታጣቂዎቹ መያዙን" ለቢቢሲ ተናግረው ነበረ።
ጥቃቱን ለመከላከል በወረዳው ባለው የፀጥታ ኃይል በኩል ሙከተራ ተደርጎ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ ለሚመለከታቸው የበላይ አካላት ቢያሳውቁም፤ አሁን የደረሰውን ጉዳት ቀድሞ መቆጣጠር አለመቻሉን ተስፋ በመቁረጥ ስሜት ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የተከሰተውን የጸጥታ ችግር ተከትሎም ከክልሉና ከፌደራል መንግሥት ተጨማሪ ኃይል ተጠይቆ ወደ አካባቢው መግባቱን ነዋሪዎችና ኃላፊው ገልጸዋል።
የክልሉ መንግሥትም በመግለጫው "በንጹሃን ላይ እየፈፀመ ያለውን ጥቃት ለማስቆም ጥቃቱ ከጀመረበት ሰዓት ጀምሮ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ ይገኛል" ብሏል።
ጥቃቱን የፈጸሙት ታጣቂዎች በከባድና በዘመናዊ መሳሪያ የተደገፉ መሆናቸውን አቶ ሰለሞን ገልጸው፤ "ለደኅንነቱ ስጋት ያደረበት ነዋሪ ሊደርስ ከሚችል ጉዳት ለመሸሽ ከተማውን ለቆ እየወጣ ነው" ሲሉ ቅዳሜ ዕለት ተናገረው ነበር።
ያነጋገርናቸው ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉ የማጀቴ ነዋሪዎችም ከአርብ ሌሊት ከ6:00 ጀምሮ ቢቢሲ ነዋሪዎችን እሰካናገረበት ቅዳሜ እኩለ ቀን ድረስ ተኩስ እንዳለ የገለጹ ሲሆን፤ በስልክ በተደረገው በቃለ ምልልስ ወቅትም ከጀርባ የተኩስ ድምጽ ይሰማ ነበር።
ጥቃቱን ተከትሎ በአካባቢው የስልክ ኔትወርክ ተቋርጦ እንደነበር የሚገልጹት ነዋሪዎች፤ ይህም መረጃ እንዳይለዋወጡ እንዳደረጋቸው ገልፀዋል።
ጥቃቱን በማን እንደተፈጸመ በግልጽ የታወቀ ነገር ባይኖርም የአካባቢው አስተዳደርና ነዋሪዎች የችግሩ ፈጣሪና ጥቃት ፈጻሚው 'ኦነግ ሸኔ' ነው ይላሉ።
የክልሉ መንግሥትም በመግለጫው ጥቃቱ የተፈጸመው "የኦነግ ቡድንና እሱን መሰል ተባባሪ" ባላቸው ኃይሎች መሆኑን ገልጾ፤ "በንጹሐን ላይ የፈፀሙት ጥቃት በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው" ብሏል።
ጨምሮም በአጣየና በአካባቢው የተፈጸመውን ዝርዝር ጥቃት እንዲሁም የደረሰውን ሰብአዊና የንብረት ጉዳት መንግሥት በፍጥነት መረጃውን አጣርቶ ለሕዝቡ ይፋ የሚያደርግ ገልጿል።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ውስጥ የሚገኘው ኤፍራታና ግድም ወረዳ በክልሉ ውስጥ ካለው የኦሮሞ ብሔረሰብ ልዩ ዞን ጋር ይዋሰናል።
ከዚህ ቀደምም በተለያዩ ጊዜያት በወረዳው ውስጥ በሚገኙ አካባቢዎች በተፈጸሙ ጥቃቶችና ግጭቶች በሰውና በንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያናገራቸው የማጀቴ ከተማ ነዋሪ አስታውሰዋል።












