ኤርትራ በአውሮፓ ሕብረት የተጣለባትን ማዕቀብ ተቃወመች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ኤርትራ በአውሮፓ ሕብረት በደኅንነት ተቋሟ ላይ የተጣለባትን ማዕቀብ "ውጤት የማያስገኝ" በማለት እንደማትቀበለው ገለፀች።
ሕብረቱ በኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ላይ ማዕቀብ የጣለው ከከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች ጋር በተያያዘ ነው።
የአውሮፓ ሕብረት ይህንን ማዕቀብ በደኅንንት ተቋሙ ላይ ለመጣል የወሰነው የኤርትራ ብሄራዊ የደኅንት መስሪያ ቤት ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጽሟል በሚል ነው።
በዚህም ተቋሙ በዘፈቀደ በተፈጸሙ ግድያዎች፣ በእንግልቶች፣ በሰዎች እስር እና መሰወር ጋር በተያያዘ በተፈጸሙ በደሎች ውስጥ እጁ አለበት በሚል ነው እገዳው የተጣለው።
የሕብረቱን እርምጃ ተከትሎ የኤርትራ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በሰጠው ምላሽ የሕብረቱን ውሳኔን "ጥቃት እና ውጤት የማያስገኝ" እንደሆነ በመግለጽ እንደማይቀበለው ገልጿል።
ጨምሮም ሕብረቱ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ሕጋዊም ሆነ የሞራል የበላይነት የለውም በማለት "ለሌላ ድብቅ አላማ ሲባል ኤርትራን ለማሸማቀቅ በሐሰት የተቀነባበረ ክስ ነው" ሲል አጣጥሎታል።
የአውሮፓ ሕብረት ምን አይነት ማዕቀብ አንደጣለና ማዕቀቡን በዚህ ወቅት ለምን መጣል እንዳስፈለገ ዝርዝር መረጃ አልሰጠም።
ሮይተርስ የዜና ወኪል እንደዘገበው አውሮፓ ውስጥ የኤርትራ ብሔራዊ ደኅንነት መስሪያ ቤት ንብረቶች ይታገዳሉ።
ይህ ቢሮ የሚመራው በሜጀር ጀነራል አብርሃ ካሳ ሲሆን፤ ተጠሪነቱም ለአገሪቱ የፕሬዝዘዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ ጽህፈት ቤት ነው።
የአውሮፓ ሕብረት ከኤርትራ በተጨማሪ በቻይና፣ በሊቢያ፣ በሩሲያ፣ በደቡብ ሱዳን እና በሰሜን ኮርያ ያለው የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች እንደሚያሳስቡት አስታውቋል።
በሕብረቱ የተጣለው ማዕቀብ 11 ሰዎችና አራት ተቋማትን ያካተተ መሆኑም ተገልጿል።
የአውሮፓ ሕብረት ሰብዓዊ መብቶች እንዲከበሩና የመብት ጥሰት የፈጸሙ ተጠያቂ እንዲሆኑ በማሰብ ማዕቀቡን መጣሉ ተዘግቧል።
በኤርትራ እና በደቡብ ሱዳን የዘፈቀደ ግድያ እንዲሁም በሩሲያ የፓለቲካ ተቃዋሚዎች የሚደርስባቸውን እንግልት ሕብረቱ አውግዟል።
በቻይና፣ በሊቢያ እና በሰሜን ኮርያ የዘፈቀደ ግድያ፣ የሰዎች መሰወር እና ስቃይንም ኮንኗል።
በአውሮፓ ሕብረት፣ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብት ጥሰትን በሚመለከት ማዕቀብ የሚጥለው አካል ያስተላለፈው ውሳኔ ወደ አውሮፓ የሚካሄድ የጉዞ እገዳን ይጨምራል።
የአውሮፓ ሕብረት አባላት ማዕቀብ ለተጣለባቸው አካላት በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ የገንዘብ ድጋፍ እንዳያደርጉም ዕገዳ እንደተጣለባቸው ተገልጿል።
ይህንን ውሳኔ ያስተላለፈው የአውሮፓ ሕብረት የዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ክንፍ የተቋቋመው አምና ጥቅምት ወር ላይ ነበር።
ኤርትራ በተለያዩ ዓለም አቀፍ የመብት ድርጅቶች በሰብአዊ መብቶች ጥሰትና በግድጃ የብሔራዊ ውትድርና አገልግሎት ምክንያት በተደጋጋሚ ወቀሳ ሲሰነዘርባት እንደቆች ይታወቃል።












