በትግራይ የተከሰተው ግጭት አንኳር ነጥቦች ሲዳሰሱ

የፎቶው ባለመብት, EDUARDO SOTERAS
በትግራይ ክልል በጥቅምት ወር መጨረሻ ላይ የተጀመረው ግጭት መቶ ቀናትን ደፍኗል።
በፌደራልና በክልሉ ኃይሎች መካከል በተካሄደ ግጭት ምክንያትም በክልሉ ከፍተኛ ሰብዓዊ ቀውስ ማጋጠሙን የተለያዩ ዓለማ አቀፍ የሰብዓዊ መብት ድርጅቶች በሪፖርቶቻቸው አመልክተዋል።
የግጭቱን መንስዔ እና ከግጭቱ በኋላ የተከናወኑ አበይት ጉዳዮችነ በወፍ በረር ለመቃኘት ሞክረናል።
የግጭቱ አጀማመር
በፌደራል መንግሥትና ህውሓት በሚመራው የትግራይ መንግሥት መካከል እየተባባሰ የመጣው አለመግባባት በጥቅምት 24 2013 ዓ.ም ላይ ወደ ግልጽ ግጭት ማምራቱ ይታወሳል።
በ2011 ዓ.ም ህዳር ወር ላይ የቀድሞው ኢህአዴግ እንደሚዋሃድ ውሳኔ ላይ በመድረሱ ህወሓት ይህንን ባለመቀበል ከውህደቱ ራሱን መነጠሉን አስታወቀ። ኢህአዴግ ራሱን ወደ ብልጽግና መቀየሩን ይፋ ባደረገበት ወቅትም ፖለቲካዊ ፍቺው ይፋ ሆነ። ብልጽግና ሃገሪቱን የሚመራ ፓርቲ ሆኖ ሲቀጥል ህወሓት በበኩሉ ትግራይን ማስተዳደር ቀጠለ።
በ2012 ዓ.ም መጋቢት ወር ላይ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በነሐሴ ወር መካሄድ የነበረበት አገራዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ስጋት ምክንያት መራዘሙን ይፋ ሲያደርግ፣ ህወሓት በበኩሉ 'ቫይረሱን እየተከላከሉ ምርጫ ማካሄድ ያቻላል' በሚል መከራከሪያ ምርጫውን የማራዘም ውሳኔ ሳይቀበለው ቀረ።
የፌደሬሽን ምክር ቤትም የምርጫ ቦርድ ውሳኔን በማጠናከር የፌደራልና ክልል መንግሥቶች የስልጣን ዘመን እንዲራዘም ውሳኔ አስተላለፈ።
ህወሓት እና የትግራይ ክልል ምክር ቤት በበኩላቸው የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ "ህጋዊ አይደለም" በማለት ውድቅ አደረጉ።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የምርጫ ቦርድን እና የፌደሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ ማጽደቁን ተከትሎ የትግራይ ክልል መንግስትም ክልላዊ ምርጫ እንደሚያካሂድ ውሳኔውን በሰኔ 2012 ዓ.ም ላይ ይፋ አደረገ። ምርጫውንም በከፍተኛ ድምጽ ማሸነፉን ህወሓት ይፋ አደረገ።
በጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ የሚመራ መንግሥትና የፌደሬሽን ምክር ቤት ግን በትግራይ የተካሄደውን ምርጫ "ህጋዊነት የሌለውና ትርጉም አልባ" መሆኑን በመግለጽ እውቅና እንደማይኖረው አስታውቀዋል።
ከዚህ በኋላ የሁለቱ መንግሥታት አለመግባባት እየተካረረ ሄዶ ጥቅምት 24 2013 ምሽት ጠቅላይ ሚንስትሩ የትግራይ ኃይሎች በክልሉ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ተከትሎ "ህግ የማስከበር ዘመቻ" ያሉትን ወታደራዊ እርምጃ ማዘዛቸውን አስታወቁ።
የኢትዮጰያ መከላከያ ሠራዊት ግጭቱ በተጀመረ በሶስት ሳምንት ጊዜ ውስጥ፣ ሕዳር 19 2013 ዓ.ም የመቀለ ከተማን ተቆጣጠረ። ጠቅላይ ሚንስትር ዓብይ በተመሳሳይ ቀን በሰጡት መግለጫ "ህግ የማስከበር ዘመቻው" በድል መጠናቀቁን በማሳወቅ የሚቀረው የህወሐት መሪዎችን በቁጥጥር ስር የማስገባት ስራ ብቻ እንደሚሆን ገልፀዋል።
ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜም በተለያዩ አካባቢዎች አልፎ አልፎ ውጊያዎች እንደሚካሄዱ የሚገልጹ መረጃዎች እየወጡ ነው።
በትግራይ ክልል ላይ በተካሄደው ጦርነት በሁለቱም ሐይሎች በኩል ስንት ተዋጊዎች እንደተገደሉ በይፋ የተገለጸ ነገር ባይኖርም ከፍተኛ የሰው ኃይልና የንብረት ውድመት መድረሱ ግን ይገመታል።

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA
የተገደሉና የታሰሩ የህወሐት አመራሮች
የፌደራል መንግሥት ጸጥታ ሀይሎች እንዳስታወቁት በርካታ የህወሐት መስራቾችና አመራሮች እንዲሁም በአገሪቱ ከፍተኛ ስልጣን ላይ ያገለገሉ ተገድለዋል፤ ታስረዋልም።
መከላከያ ሠራዊት በወሰደው እርምጃ ከተገደሉት መካከልም ለ20 ዓመታት የውጭ ጉዳይ ሚንስትር ሆነው ያገለገሉት ከህወሐት መስራቾች አንዱ የነበሩት አምባሳደር ስዩም መስፍን ይገኙበታል።
አብረዋቸው በሚንስትርነት ደረጃ ያገለገሉ አቶ አባይ ጸሃዬና የህወሐት ሥራ አስፈጻሚ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደስላሴ ተገድለዋል።
ከከፍተኛ የህወሐት አመራሮች መካከል አንድ የሆኑት እና አንጋፋ ፖለቲከኛ አቶ ስብሐት ከባለቤታቸው ሌ/ኮ ሪቺና እንዲሁም እህታቸው ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ ጋር በቁጥጥር ስር ውለዋል።
በተጨማሪም ለዓመታት የትግራይ ክልል ፕሬዚደንት በመሆን ያገለገሉት አቶ አባይ ወልዱ እንዲሁም ምክትል ርዕሰ መስተዳድርና የህወሐት ስራ አስፈጻሚ ኮሜቴ አባል የነበሩት አብርሃም ተከስተ [ዶ/ር] የሚገኙባቸው በርካታ የክልሉ አመራሮች በእስር ላይ ሆነው ጉዳያቸው ፍርድ ቤት እየታየ ነው።
ጦርነቱ ያስከተለው ሰብአዊ ቀውስ!
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው ጦርነት በክልሉ ህዝብ ላይ ከፍተኛ የሰብአዊ ቀውስና መፈናቀል ማስከተሉን የመንግስት አካላት እንዲሁም የእርዳታ ድርጅቶች በመግለጽ ላይ ይገኛሉ።
ከ2.3 ሚልዮን ሰዎች በክልሉ ውስጥ ከቀያቸው የተፈናቀሉ ሲሆን ከ60 ሺህ በላይም ወደ ሱዳን በመሸሽ በስደተኛ ካምፖች ውስጥ ተጠልለው ይገኛሉ። እንደ ተባበሩት መንግሥታት አሃዝ 4.5 ሚልዮን ህዝብ በላይም በክልሉ አስቸኳይ የምግብና ህክምና እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው መረጃዎች ያመለክታሉ።
በክልሉ የሚገኙ ትምህርት ቤቶችና የጤና ተቋማት አግልግሎት መስጠት አቁመው ቆይተዋል። ግጭቱ ከተጀመረ ከሁለት ወር በኋላ አምስት ሆስፒታሎች ብቻ አገልግሎት መስጠት ጀምረው እንደነበረ የተባበሩት መንግስታት ድርጅት መረጃ ያመለክታል።
የስልክና ኢንተርኔት አገልግሎቶች በመቋረጣቸውም ስለጦርነቱና በክልሉ ስለሚፈጠሩ ነገሮች መረጃ ለማግኘት የማይቻል ነገር ሆኖ ቆይቷል። የኤሌትሪክ አገልግሎትም ሙሉ በሙሉ ተቋርጦ ነበር። ከጥር ወር የመጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ ግን የስልክና የትራንስፖርት አገልግሎት በተወሰኑ ከተሞች ሊመለስ ችሏል።
ከዚህ በተጨማሪ በትግራይ ክልል በአራት የስደተኞች መጠለያዎች የነበሩ ኤርትራውያን ስደተኞችም በከፍተኛ አደጋ ላይ መውደቃቸው ይገለጻል። መጠለያዎቹ ውጊያው በሚካሄድባቸው አካባቢዎች የሚገኙ ስለሆኑ ለስደተኞቹ የሚሆን እርዳታ ማድረስ ባለመቻሉ እጅግ አስጊ በሆነ ሁኔታ ላይ መቆየታቸው ይታወቃል።
የተባበሩት መንግስታት፣ የአውሮፓ ሕብረትና አሜሪካን ጨምሮ የተለያዩ አካላት በትግራይ ውስጥ ተፈጽመዋል የሚባሉ ጾታዊ ጥቃቶች፣ ግድያዎች፣ እገታና ዘረፋ የሚገኙባቸው ከባድ የሰብአዊ መብት ጥሰቶች በነጻና ገለልተኛ አካል እንዲጣራ ጥያቄ እያቀረቡ ነው።
የኤርትራ ተሳትፎ
የህወሐት መሪዎች ውጊያው በተጀመረ ማግስት የኤርትራ ሰራዊት ከኢትዮጵያ መከላከያ ሰራዊት ጎን በመሰለፍ ድብደባዎች እንዳካሄደና በርካታ የኤርትራ ሰራዊት ወደ ትግራይ መግባታቸውን ሲከሱ ተሰምተዋል።
የአውሮፓ ህብረት እና አሜሪካ በተለያየ ጊዜ የኤርትራ ወታደሮች ከኢትዮጵያ እንዲወጡ የሚጠይቅ መግለጫ አውጥተዋል።
የኤርትራው የውጭ ጉዳይ ሚንስትር አቶ ዑስማን ለሮይተርስ በሰጡት ምላሽ ግን ኤርትራ በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳዮች ላይ እንደማትገባ ተናግረው ነበር። የኢትዮጵያ መንግሥትም የኤርትራ ጦር በትግራዩ ግጭት እንዳልተሳተፈ ሲያስተባብል ቆይቷል።
የህወሓት ኃይሎች በተደጋጋሚ ወደ ኤርትራ ሚሳዔል ቢያስወነጭፍም የኤርትራ መንግስት ስለጥቃቶቹ የሰጠው ይፋዊ መግለጫ የለም።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
በማይካድራ የተፈጸመው ግድያ
በኢትዮጵያ ሰሜን ምዕራብ ክፍል ውስጥ በምትኘው ማይካድራ ከተማ በተፈጸመው ጭፍጨፋ ከ600 በላይ ሰዎች መገደላቸውን የሰብአዊ መብት ቡድኖች አስታውቀዋል።
ማይካድራ ከተማ የተፈጸመው ጥቃት በአካባቢው መስተዳድር የጸጥታ መዋቅርና 'ሳምሪ' በተባለ ኢ-መደበኛ የወጣቶች ቡድን መፈጸሙንም የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በሪፖርቱ ላይ አመልክቷል።
ኮሚሽኑ ይህ ከፍተኛ የሰብአዊ መብቶች ጥሰት "በሰብአዊነት ላይ የተፈጸመ ወንጀል እና የጦር ወንጀል ሊሆን እንደሚችል" ያመለከተ ሲሆን፤ ለዚህም ኢሰመኮ ዝርዝር ማስረጃዎቹን እና ወንጀሉን የሚያቋቁሙትን የሕግና የፍሬ ነገር ትንተና በሙሉ ሪፖርቱ ላይ በዝርዝር አጣርቶ የሚያቀርብ መሆኑን አሳውቋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ በበኩላቸው የፌደራል መንግሥት የምዕራብ ትግራይን "ነፃ ካወጣ" በኋላ የህወሓት ታጣቂዎች በማይካድራ ከተማ በርካታ ንፁሃን ዜጎችን "በአሰቃቂ ሁኔታ ገድለዋል" ብለዋል።















