የህወሃት ሊቀ መንበር ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሁለት ወራት በኋላ ምን አሉ?

ደብረ ፅዮን ገብረ ሚከኤል (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, Dimtsi woyane

የህወሃት ሊቀመንበር የሆኑት ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) ከሁለት ወራት ዝምታ በኋላ በትናትናው ዕለት፣ ጥር 22፣ 2013 ዓ.ም በድምፂ ወያነ ትግራይ ፌስቡክ ገፅ ለትግራይ ህዝብ ያሉትን መልዕክት አስተላልፈዋል።

ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በተቋረጠው ድምፂ ወያነ ትግራይ የፌስቡክ ገፅ በድምፅ ባስተላለፉት መልዕከት ክልሉ ላይ ደርሷል ስለተባሉ ውድመቶች፣ ቀጥሏል ስላሉት የትግል ሁኔታ እንዲሁም ለትግራይ ህዝብና ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ያሉትን ጥሪ አስተላልፈዋል።

መንግሥት በበኩሉ ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል ያቀረቧቸው ክሶች "መሰረተ የሌላቸው" እና ዓላማቸውም "የህወሓትን አጸያፊ ወንጀሎች ለመሸፋፈን ነው" ይላል።

ከአሜሪካ እየተላለፈ እንደሆነ በተገለፀው የድምፂ ወያነ ገጽ ላይ የተሰራጨው ድምጽ በትክክልም የደብረጺዮን (ዶ/ር) ስለመሆኑ እና መቼ እንደተቀረፀ ቢቢሲ ከገለልተኛ ወገን ማጣራት አልቻለም።

ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል (ዶ/ር) በትግራይ ላይ የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት አስመልክቶ "ህዝቡ ራሱን በራሱን የማስተዳደር መብቱን በተግባር ለማረጋገጥ በፅናት ስለታገለ የተቃጣበት ጦርነት" ያሉት ሲሆን አራት መንግሥታትና የክልሎች ልዩ ኃይሎች ተሳትፈውበታል ብለዋል።

አራቱ ብለው የጠሯቸው መንግሥታት እነማን እንደሆነ ባይዘረዝሩም "በዚህም ምክንያት የኃይል አለመመጣጠን አጋጥሟል" በማለት አስረድተዋል።

በተለያዩ ሪፖርቶች የኤርትራ ወታደሮች መሳተፋቸው የተጠቀሰ ሲሆን በቅርቡ የኤርትራ ወታደሮች ከትግራይ ክልል በአስቸኳይ እንዲወጡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት (ስቴት ዲፓርትመንት) መጠየቁ ይታወሳል።

የኢትዮጵያ መንግሥት በበኩሉ በተደጋጋሚ ይህ ህግ የማስከበር ዘመቻ እንደሆነና በትግራዩ ግጭት የኤርትራ ጦር አለመሳተፉን ማሳወቁ የሚታወስ ነው።

የፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት በኅዳር ወር አጋማሽ ላይ መቀለን ከተቆጣጠረ በኋላ በትግራይ ያካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ መጠናቀቁን መግለጹ ይታወሳል።

መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሰራዊት በቁጥጥር ሥር ከዋለች በኋላ የህወሃት ሊቀ መንበር ለሮይተርስ ትግሉ እንደሚቀጥልና "ትግሉ የራስን መብት በራስ የመወሰን እንደሆነ" ገልጸው ነበር።

በፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ደብረ ፅዮን ገ/ሚካኤል በአሁኑ ወቅት የት እንዳሉ በግልጽ ባይታወቅም የአገሪቱ የመከላከያ አዛዦች ግን ተፈላጊዎቹ የህውሓት አመራሮች በትግራይ ተራራማ ቦታዎች ተደብቀው እንደሚገኙ ሲገልጹ ተሰምተዋል።

ለእስር ማዘዣው ዋነኛ ምክንያቶቹ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈፀም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

ደብረፅዮን ገብረ ሚካኤል በጠቀሱት ትግል "ከፍተኛ ዋጋ ጠይቋል" ያሉ ሲሆን። "የህወሃት መስራች አባላት ከሚባሉት ላለፉት 45 ዓመታት ከያዙት ህዝባዊ መስመር ፈቀቅ ሳይሉ የታገሉና የመሩ፣ ያታገሉና ብዙ ድል ያስመዘገቡ አዛውንት ነባር ታጋዮች በዚህ የወረራ ጦርነት፣ በጠላት እጅ ተጎድተውብናል። ከባድ መስዋዕትነት ከፍለዋል። አሁንም እየከፈሉ ይገኛሉ። የነዚህ ጀግኖቻችን መስዋዕትነት የበለጠ ቁጭትና እልህ ያስንቀናል እንጂ ፈፅሞ ከትግላችን የሚያቆመን አይሆንም።" ብለዋል

ዶ/ር ደብረፅዮን መስዋዕት ሆነዋል ያሏቸውን ግለሰቦች በስም ባይጠቅሱም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ በተለያዩ የሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ በግጭቱ ወቅት እጅ አልሰጥም በማለታቸው መገደላቸው ተነግሯል።

በትግራይ ክልል ደርሷል ስለተባለው ውድመት

ደብረ ፅዮን ገብረ ሚካኤል በክልሉ ላይ ደረሱ ስላሏቸው ጥቃቶችና ዘርፈ ብዙ ሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ተፈጽመዋል ሲሉ ከሰዋል።

"የትግራይ ሴቶች በተናጠልና በደቦ ይደፈራሉ። የትግራይ መንደሮችና ዓብያተ እምነቶች፣ የትግራይ ሰራዊት ይኑርበት አይኑርበት ሳይገዳቸው የቦምቦችና የመድፎ ዒላማ ይደረጋሉ። ውድና መተኪያ የሌላቸው ቅርሶችም ይወድማሉ፣ ይዘረፋሉ። በሚልዮን የሚቆጠር ህዝብ እንዳለ ከቀየው ወጥቶና ተፈናቅሎ የመከራ ኑሮ ይኖራል።" ብለዋል።

ደብረ ፅዮን ህዝቡ ላይ እየተፈፀመ ነው ያሉትን ወንጀል በግልፅ እንዲቃወምና እንዲያወግዝ ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ጥሪ አቅርበዋል። ከዚህም በተጨማሪ በክልሉ ተፈፀመ ያሉት ወንጀል በገለልተኛ አካል እንዲጣራና ህጋዊ እርምጃ እንዲወሰድ ጠይቀው ለዚህ ተጠያቂ ናቸው ብለው የጠሯቸውን የኢትዮጵያና የኤርትራ መሪዎች ወደ አለም አቀፉ የወንጀል ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ጠይቀዋል።

ስለቀጠለው ትግል

የፌደራል መንግሥቱ መቀለን ከተቆጣጣረ በኋላ ውጊያዎች እንደቆሙና በክልሉ ያለውን የመሰረተ ልማት ግንባታ እንደተጀመረ በተለያዩ ሚዲያዎች ገልጿል።

ደብረ ፅዮን ግን በንግግራቸው በአሁኑ ወቅት በርካቶች ትግላቸውን እየተቀላቀሉ እንደሆነ ገልጸው ህዝቡም "ጠላት" ብለው የጠሩትን ኃይል እንዲታገሉ ጠይቀዋል።

በተጨማሪም ደብረ ፅዮን በንግግራቸው በትግላቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።

የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ፕሬስ ሴክረተሪ ቢለኔ ስዩም ከቢቢሲ ለቀረበላቸው ጥያቄ ‹‹ለተቀዣበረ የወንጀለኛ ቡድን የፌስቡክ መልእክት›› ምላሽ መስጠት እንደማይፈቅዱ ገልጠዋል፡፡

ሆኖም ሕግን የማስከበር እርምጃን በተመለከተ የወንጀለኛው ቡድን እና የነሱ ዓለም አቀፍ ጋሻ አጃግሬዎች የዓለም አቀፉን ማኅበረሰብ ለማደናገር ሲሞክሩ እንደቆዩና የዘር ማጥፋት ወንጀል እንደተጸፈመ በማስመሰል የሚያደርጉት ይህ ማደናገር ተግባርም ከኅዳር ወር የጀመረ መሆኑን ገልጠው፣ "ይህን የሚያደርጉትም በዋናነት የህወሓትን አጸያፊ ወንጀሎች ለመሸፋፈን እንደሆነ" ተናግረዋል፡፡

ብለኔ ስዩም ‹የሕወሓትን ወንጀል ለመሸፋፈን ከመሞከር ይልቅ› የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብና ዓለም አቀፍ ሚዲያው እነዚህን የህወሓት ወንጀለኞች ለህግ የማቅረቡን የመንግሥት ጥረት እንዲደግፍ እንሻለን" ብለዋል፡፡

የህወሃት አመራሮች እስር

በቅርቡ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽን ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል ምርመራ ቢሮ ኃላፊ ዘላለም መንግስቴ የእስር ትዕዛዝ የወጣባቸው ሰዎች ብዛት 349 መሆናቸውን ከነዚህ ውስጥ 96 የሚሆኑት የህወሓት ቁልፍ አመራሮች እንደሆኑ አሳውቀዋል፡፡

ተፈላጊ ከሆኑት አጠቃላይ ተጠርጣሪዎች መካከል 124 የሚሆኑት በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው እንደሆነም ገልጸዋል።

ከሰሞኑም አቶ ስብሐት ነጋ፣ አቶ አባይ ወልዱ እና ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂምን ጨምሮ በሶስት መዝገብ የተካተቱ 21 ተጠርጣሪዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል።

ተጠርጣሪዎቹ በሃገር ክህደት ወንጀል፣ በክልሉ በሚገኘው የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በማድረስና፣ በመሳሪያ በታገዘ አመፅና ሁከት በማነሳሳት በሚሉ ወንጀሎች ነው ፍርድ ቤት የቀረቡት።

በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክህደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።

በፌደራል መንግሥቱ እና የትግራይ ክልልን ሲያስተዳድር በነበረው ህወሓት መካከል ለረዥም ጊዜ የዘለቀው መቃቃርና አለመግባባት ተካሮ የህወሓት ኃይሎች የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈጽመዋል በማለት ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ የፌደራሉን ጦር ወደ ትግራይ ማዝመታቸው ይታወሳል።

የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በክልሉ ያለውን የሰብአዊ ሁኔታ "የከፋ" ሲል ገልጾታል።

በተባበሩት መንግሥታት ሪፖርት ላይ እንደተጠቀሰውና የአስቸኳይ ጊዜ ማስተባበሪያ ማዕከል እንደሚለው በትግራይ ክልል 4.5 ሚሊዮን ሕዝብ የአስቸኳይ ጊዜ የምግብ እርዳታ ያስፈልገዋል።

የተባበሩት መንግሥታትም ሆነ የተለያዩ የእርዳታ ድርጅቶች ህዝቡን መደረስ እንዳልቻሉም ሲናገሩና መንግሥት እንዲያመቻች ሲጠይቁም ተሰምተዋል።

በክልሉ ውስጥ ያለው ሁኔታ አስከፊ እንደሆነና "በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በረሃብ ምክንያት ለሞት ሊዳረጉ እንደሚችሉ" አንድ የመንግሥት ባለስልጣን መናገራቸውን ከእርዳታ ሠራተኞች ጋር ከተደረገ ስብሰባ ላይ ሾልኮ የወጣ ማስታወሻ ላይ የሰፈረ ጽሁፍ ማመልከቱ የሚታወስ ነው።

ከዚህም በተጨማሪ ጦርነት በተካሄደባቸው የትግራይ ክልልና አዋሳኝ አካባቢዎች ያሉ ነዋሪዎች ደኅንነትና ከመኖሪያ አካባቢያቸው የተፈናቀሉ ሰዎች ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑንና የሰብአዊ ቀውስን ሊያስከትል እንደሚችል የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ገልጿል።

ከሰሞኑም እንዲሁ በክልሉ ምግብ፣ ምግብ ነክ ያልሆኑ ቁሳቁሶችና የሕክም አቅርቦቶች የሰብዓዊ ድጋፍ ለ1.8 ሚሊዮን ሰዎች መድረሱን የሠላም ሚኒስቴር ገልጿል።

ሚኒስቴሩ ድጋፍ ለሚፈልጉ ሰዎች እየቀረበ ያለውን እርዳታ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ ከተጠቀሱት ሰዎች በተጨማሪ በክልሉ 2.5 ሚሊዮን ተጠቃሚዎችን ለማስተናገድ የሚያስችል ዝግጅት መደረጉን አመልክቷል።