ትግራይ ፡ አቶ ስዩም መስፍንና አቶ አባይ ፀሐዬ መገደላቸው ተገለጸ

የቀድሞ የአገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩትን አቶ ስዩም መስፍንን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መገደላቸውን የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና አምባሳደር የነበሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ በተለያዩ የሥልጣን ቦታ ላይ የነበሩት አቶ አባይ ጸሐዬ፣ የፓርላማ አባል የነበሩት አቶ አስመላሽ ወልደ ሥላሴ እንዲሁም ከመከላከያ ሠራዊቱ ከድተዋል የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስ መገደላቸው ተነግሯል።
ሠራዊቱ በትግራይ ክልል ከተከሰተው ወታደራዊ ግጭት በኋላ የመያዣ ትዕዛዝ የወጣባቸውን የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ አሰሳና ፍተሻ እያካሄደ መሆኑን ተከትሎ ጥቂት የማይባሉት መያዛቸውንና መገደላቸውን ባለፉት ሳምንታት ውስጥ ማሳወቁ ይታወሳል።
የሠራዊቱ ኃይል ስምሪት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዲየር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለፁት የህወሓት ቀደምት ታጋዮችና በፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም በትግራይ ክልል አስተዳደር ውስጥ ከሁለት አስርት ዓመታት በላይ በከፍተኛ የሥልጣን ቦታ ላይ ከነበሩት አመራሮች መገደላቸውን ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት ገልጸዋል።
ኃላፊው እንዳሉት እርምጃ ከተወሰደባቸው መካከል ከሃያ ዓመታት በላይ የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትርና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር በመሆን የሰሩት አቶ ስዩም መስፍን፣ ሠራዊቱ ከቦታ ቦታ እንዳይንቀሳቀስ ማዘዛቸውን፣ ትግራይ ውስጥ የተካሄደውን ውጊያ እንዲጀመር ትዕዛዝ መስጠታቸውንና መምራታቸውን ገልጸዋል።
ከቀደምት የህወሓት ታጋዮችና አመራሮች መካከል አንዱ የነበሩት አቶ አባይ ፀሐዬ ተገድለዋል ከተባሉት አመራር ውስጥ ሲሆኑ፤ በፌደራል መንግሥቱ ውስጥ የፌደራል ጉዳዮች ሚኒስትር፣ የጠቅላይ ሚኒስትር አማካሪ እንዲሁም የስኳር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ሆነው ሰርተዋል።
ሌላኛው እርምጃ እንደተወሰደባቸው የተነገረው አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ ቀደምት የህወሓት ታጋይ ሲሆኑ ለረጅም ዓመታት የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል በመሆን ያገለገሉና በምክር ቤቱም የሕግ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ሆነው አገልግለዋል።
አቶ ስዩም መስፍን፣ አቶ አባይ ፀሐዬና አቶ አስመላሽ ወልደሥላሴ በህወሓት እና በኢህአዴግ ውስጥ የሥራ አስፈጻሚና የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በመሆን ለረጅም ጊዜ አገልግለዋል።
ብርጋዲየር ጄነራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለጹት የአገር መከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል የፀጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ በተከዜ ወንዝ ዳርቻ ከአመራሮቹና በዙሪያቸው ከነበሩ ጥበቃዎቻቸው ጋር በተደረገ ተኩስ ልውውጥ እንደተገደሉ ተናግረዋል።
ኃላፊው ጨምረውም ቀደም ሲል በተደጋጋሚ እጅ እንዲሰጡ የጊዜ ገደብ ተቀምጦላቸው እንደነበር እንዲሁም "የአገር መከላከያ ሠራዊት የአገር ሽማግሌ ጭምር በመላክ እጅ እንዲሰጡ፣ ትጥቅ እንዲፈቱና ጉዳያቸው በሕግ እንዲታይ ተጠይቀው ነበር" ብለዋል።
ከሦስቱ ከፍተኛ አመራሮችና ጠባቂዎቻቸው በተጨማሪ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል የነበሩና ኋላ ላይ በመክዳት ከህወሓት ኃይል ጋር ተሰልፈው ነበር የተባሉት ኮሎኔል ኪሮስ ሐጎስም እንደተገደሉ ተጠቅሷል።
ከዚህ ባሻገር ሠራዊቱና የጸጥታ ኃይሎች ባካሄዱት ዘመቻ ከተገደሉት ሰዎች በተጨማሪ አራት ወታደራዊ መኮንኖችና አንድ ሲቪል እጃቸውን መስጠታቸው ተገልጿል።
በዚህም መሠረት ከመከላከያ ሠራዊት ከድተው ነበር የተባሉት ኮሎኔል ገብረመስቀል ገብረ ኪዳን፣ ኮሎኔል ፍስሃ ብርሃኔ፣ ኮሎኔል ዘረአብሩክ ታደሰ እንዲሁም ኮማንደር ገብረኪዳን አስገዶም የልዩ ኃይል የክፍለ ጦር አዛዥ የነበሩ እና አቶ መብራህቶም ክንዴ የተባሉ ግለሰብ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነግሯል።
አስካሁን በርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ዛሬ ይፋ ከተደረጉት ሦሰት ከፍተኛ አመራሮች በተጨማሪም ሌሎችም መገደላቸው ከዚህ በፊት ተገልጿል።
እስካሁን ድረስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮንም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ያሉበት ሁኔታ በዚህ መግለጫ ላይ አልተጠቀሰም።
መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ተገድለዋል ያላቸውን የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮችን በተመለከተ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን የተሰማ ነገር የለም።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት ፈፅመዋል መባሉን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን ከተወገደ በኋላ የቡድኑ አመራሮች እየተፈለጉ ይገኛሉ።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ ማድረጋቸው ይታወሳል።
ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው መሆኑንም መንግሥት ገልጿል።
በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክህደትና በሠራዊት አባላት ላይ ወንጀል ፈፅመዋል በሚል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመንግሥት እየተፈለጉ ያሉትን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ጠቁሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚያስችል መረጃዎችን ለሚሰጡ ሰዎች የአስር ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወሳል።













