ትግራይ ፡ የቀድሞው ርዕሰ መስተዳደርና ምክትል ሚኒስትር በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተነገረ

አቶ አባይ ወልዱ እና አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)

የፎቶው ባለመብት, ETHIOPIA OBSERVER/WORLD BANK

የምስሉ መግለጫ, አቶ አባይ ወልዱ እና አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)

የቀድሞው የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር፣ የገንዘብ ምክትል ሚኒስትርና ምክትል ርዕሰ መስተዳደርን ጨምሮ በርካታ የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸው እንዲሁም መገደላቸውን የመከላከያ ሚኒስቴር አስታወቀ።

የሠራዊቱ ከፍተኛ ባለስልጣን የሆኑት ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው እንደገለጹት በጸጥታ አካላት ከተያዙት ውስጥ ሰባት የህወሓት ፖለቲካዊ አመራሮች እንዲሁም "ከአገር መከላከያ ሠራዊት ከድተው ቡድኑን የተቀላቀሉ" ወታደራዊ መኮንኖች እንደሚገኙበት አመልክተዋል።

የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝደንት አቶ አባይ ወልዱ እና ቀደም ሲል የፌደራል የገንዘብ ምክትል ሚኒስትር በኋላ ደግሞ የትግራይ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ከተያዙት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች መካከል ይገኙበታል።

በተጨማሪም ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ከአገር መከላከያ ሠራዊት ከድተው ከህወሓት ጋር ተሰልፈው ነበር ያሏቸው ጄኔራል መኮንኖች፣ ከፍተኛ መኮንኖች፣ መስመራዊ መኮንኖች እንዲሁም የግል ጥበቃዎቻቸው ላይ እርምጃ መወሰዱን ገልጸዋል።

መገደላቸው ከተነገረው ከፍተኛ መኮንኖች መካከል የቀደሞው የአገር መከላከያ የሎጂስቲክስ ኃላፊ ሜጀር ጄኔራል ኢብራሂም አብዱልጀሊል እና የመከላከያ ሠራዊት የኢንዶክትሪኔሽን የቀድሞ ኃላፊ የነበሩት ብርጋዲየር ጄኔራል ገብረኪዳን ገብረማርያም እንደሚገኙበት ተጠቅሷል።

በክልሉ የተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከነበሩ ውስጥም የትግራይ ኦዲተር ቢሮ ኃላፊ ረዳኢ በርሄ (ዶ/ር)፣ የክልሉ ስታትስቲክስ ኤጀንሲ ኃላፊ ሙሉጌታ ይርጋ (ዶ/ር)፣የኃይማኖት ጉዳይ ክትትል ኃላፊ አቶ ዕቁባይ በርሄ፣ የክልሉ ፕሬዚዳንት ጽህፈት ቤትና የሠላምና ደኅንነት ኃሃላፊ አቶ ጌታቸው ተፈሪ እንዲሁም የክልሉ ማኅበራዊ ጉዳይ ኃላፊ ወ/ሮ ኪሮስ ሐጎስ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተገልጿል።

የመከላከያ ሠራዊቱ የስምሪት መምሪያ ኃላፊው ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ጨምረው እንደተናገሩት እርምጃ እንደተወሰደባቸው ከተገለጹት ሁለት ጄነራል መኮንኖች በተጨማሪ ከፍተኛ መኮንኖች፣ መስመራዊ መኮንኖችና የግል ጥበቃዎቻቸው እንዲሁም አንድ የክልሉ ረዳት ኮሚሽነር የነበረና ከፖሊስ የከዳ ግለሰብ መገደላቸውን አመልክተዋል።

በተጨማሪም ከመከላከያ ሠራዊት ከድተው ከህወሓት ጋር ተቀላቅለው ነበር ያሏቸው ኮሎኔል ገብረእግዚአብሔር አምባዬና ኮሎኔል ትርፏ አሰፋ የተባሉ ሁለት ከፍተኛ መኮንኖች በቁጥጥር ስር የዋሉ መሆናቸውን ገልጸዋል።

እየተፈለጉ ያሉትን የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ የአገር መከላከያ ሠራዊት፣ የፌዴራል ፖሊስና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት በጥምረት አሰሳና ፍተሻ እያደረጉ መሆናቸውን ብርጋዲየር ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው አመልክተዋል።

ቀደም ሲል የተያዙ

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ በቁጥጥር ስር የዋሉት የቀድሞ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ወደ አዲስ አበባ መወሰዳቸውን የአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን ዘግበዋል።

ከእነዚህም መካከል በሰማኒያዎቹ የዕድሜ ክልል ውስጥ የሚገኙትና የህወሓት መስራች የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ የሚገኙበት ሲሆን አብረዋቸውም ሌሎች በክልሉና በቡድኑ ውስጥ በሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ የነበሩ ግለሰቦች ይገኙበታል።

ከዚህ በፊትም በተመሳሳይ የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው አሰሳ የተገደሉና በቁጥጥር ስር የዋሉ የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮች የስም ዝርዝር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ፤ የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርና በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች መማረካቸውን እንዲሁም በርካቶች መደምሰሳቸውን አስታወቆ ነበር።

እስካሁን መገደላቸው እንዲሁም መያዛቸው ከተገለፁ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሌላ የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አዲስዓለም ባሌማንና የቀድሞዋን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬርያ ኢብራሂም ጨምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ይገኛሉ።

የመከላከያ ሠራዊት ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ

የፎቶው ባለመብት, EBC

እየተፈለጉ ያሉ አመራሮች

እስካሁን ድረስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ያሉበት ሁኔታ በዚህ መግለጫ ላይ አልተጠቀሰም።

ከጥቂት ሳምንት በፊት የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል።

መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ተገድለዋል ያላቸውን የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮችን በተመለከተ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን የተሰማ ነገር የለም።

የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን መወገዱ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ አድርገው ነበር።

ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።