ትግራይ፡ መከላከያ ተጨማሪ የህወሓት አመራሮችን መማረካቸውንና መገደላቸውን ገለጸ

ብርጋዲየር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው

የፎቶው ባለመብት, ENA

የምስሉ መግለጫ, ብርጋዲየር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው

በሕግ ከሚፈለጉ ከፍተኛ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አራቱ መገደላቸውንና ዘጠኙ ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አንድ የኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊት ባለስልጣን ትናንት፣ ሐሙስ ፣ማታ አስታወቁ።

የስምሪት መምሪያ ኃላፊ የሆኑት ብርጋዲየር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ለኢትዮጵያ ዜና አገልግሎት እንደገለጹት ሠራዊቱ ከፍተኛ የህወሓት የፖለቲካና የወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ እያደርገ ባለው ዘመቻ ነው እርምጃው የተወሰደው።

በእርምጃው ከተገደሉት መካከል ጥቅምት 24 /2013 ዓ.ም በትግራይ ክልል ውስጥ ለተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት ምክንያት የሆነውን በሠሜን ዕዝ ላይ የተፈጸመውን ጥቃት "እራስን ለመከላከል የተወሰደ ቀድሞ የማጥቃት መብረቃዊ እርምጃ" መሆኑን በቴሌቪዥን ላይ ቀርበው የተናገሩት አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው ይገኙበታል ተብሏል።

በተጨማሪም የህወሓት ቀደምት ታጋይና የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም፣ የህወሓት የመገናኛ ብዙሃን ተቋም የሆነው ድምጺ ወያኔ ኃላፊ አቶ አበበ ገብረመድኅን፣ የትግራይ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ ከተገደሉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል እንደሆኑ ተገልጿል።

ከከፍተኛ አመራሮቹ በተጨማሪም አብረዋቸው ነበሩ የተባሉ የግለሰቦቹ ሹፌሮችና ጥበቃዎቻቸው ጭምር የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል የጸጥታ ተቋማት ከሕዝቡ ጋር ባካሄዱት የተቀናጀ ዘመቻ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ብርጋዲየር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው ገልጸዋል።

በተወሰደባቸው እርምጃ ከተገደሉት አራት ሰዎች ባሻገር ሌሎች ዘጠኝ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጀነራሉ ተናግረዋል።

የይፋ የሆነው የስም ዝርዝር እንደሚያሳየው የቀድሞ የትግራይ ክልል አፈጉባኤና የህወሓት መስራችና ከሚፈለጉት ግለሰቦች መካከል አንዷ የሆኑት የአቶ ስብሐት ነጋ እህት ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ፣ ዶክተር ሰለሞን ኪዳኔ የቀድሞ የትግራይ ክልል ከተማ ልማት ቢሮ ኃላፊና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ፣ አቶ ተክለወይኒ አሰፋ በህወሓት ሥር የነበረው የእርዳታ ድርጅት (ማረት) ሥራ አስፈጻሚ፣ አቶ ገብረመድህን ተወልደ የክልሉ ንግድ ቢሮ ኃላፊ እንዲሁም አቶ ወልደጊዮርጊስ ደስታ የክልሉ መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ ይገኙበታል።

በተጨማሪም አምባሳደር አባዲ ዘሙ በሱዳን የኢትዮጵያ የቀድሞ አምባሳደር፣ አቶ ቴዎድሮስ ሐጎስ የመለስ አመራር አካዳሚ ፕሬዚዳንትና የኤፈርት ቦርድ ኃላፊ ሰብሳቢ፣ ወይዘሮ ምህረት ተክላይ የትግራይ ምክር ቤት ሕግ አማካሪና አቶ ብርሃነ አደም መሃመድ የክልሉ የንብረትና ግዢ ሥራ ሂደት ኃላፊ የነበሩ በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገልጿል።

ብርጋዲየር ጀኔራል ተስፋዬ አያሌው እንደተናገሩት የተጠቀሱት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች የተገደሉትና በቁጥጥር ስር የዋሉት በተለያዩ በክልሉ ውስጥ ባሉ ጫካዎችና ዋሻ ውስጥ በመከላከያ ሠራዊትና በፌደራል ፖሊስ በተደረገ ክትትልና አሰሳ መሆኑን ገልጸዋል።

ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይም በተመሳሳይ የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው አሰሳ የተገደሉና በቁጥጥር ስር የዋሉ የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮች የስም ዝርዝር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።

እስካሁን ድረስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮንም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ያሉበት ሁኔታ በዚህ መግለጫ ላይ አልተጠቀሰም።

ከጥቂት ሳምንት በፊት የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል።

በዚህ ምለጫም የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዓርብ ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ.ም. በሰጠው መግለጫ፣ የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔርና በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች መማረካቸውን፣ እንዲሁም በርካቶች መደምሰሳቸውን አስታወቆ ነበር።

መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ተገድለዋል ያላቸውን የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮችን በተመለከተ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን የተሰማ ነገር የለም።

የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።

እስካሁን መገደላቸው እንዲሁም መያዛቸው ከተገለፁ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሌላ የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አዲስዓለም ባሌማንና የቀድሞዋን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬርያ ኢብራሂም ጨምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ይገኛሉ።

ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን መወገዱ ይታወሳል።

በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ አደረገው ነበር።

ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።

በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።

የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በመንግሥት እየተፈለጉ ያሉትን የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችን ጠቁሞ በመንግሥት ቁጥጥር ስር እንዲውሉ የሚያስችል መረጃዎችን ለሚሰጡ ሰዎች የአስር ሚሊዮን ብር ሽልማት እንደሚሰጥ ቃል መግባቱ ይታወሳል።