ትግራይ፡ አቶ ስብሐት ነጋና ሌሎችም በመከላከያ ሠራዊት በቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ

በፌደራል መንግሥቱ ሲፈለጉ ከቆዩት ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች መካከል አቶ ስብሐት ነጋ (አቦይ ስብሐት) እና ሌሎች ወታደራዊ መኮንኖች በአገሪቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር መዋላቸው ተገለጸ።
የህወሓት መስራች ከሆኑት ሰባት ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ስብሐት ነጋ ተደብቀውበት ነበር በተባለው ቦታ ላይ ሠራዊቱ ባካሄደው ዘመቻ ከሌሎች ተፈላጊ ሰዎች ጋር በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የመከላከያ ሠራዊት የስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ለኢዜአ ገልጸዋል።
ኃላፊው ጨምረው እንደገለጹት አቶ ስብሐት ነጋ ለመንቀሳቀስ እጅግ አስቸጋሪ በሆነ ስፍራ ውስጥ ተደብቀው ቆይተው በሠራዊቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን አመልክተዋል።
የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸው የሚፈለጉትን ከፍተኛ የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮችን ለመያዝ የመከላከያ ሠራዊቱና የፌዴራል የፀጥታ አካላት በጋራ ባደረጉት ፍተሻና አሰሳ አቶ ስብሐትና ሌሎች ተፈላጊዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉና ሌሎች ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው ብርጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ ገልጸዋል።
በዚህም ከአቶ ስብሐት በተጨማሪ የቀድሞ የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩና የከዱ ሌሎች የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችም በቁጥጥር ስር ውለዋል ተብሏል።
በቁጥጥር ስር የዋሉት ወታደራዊ መኮንኖች የቡድኑን ኃይል በማሰልጠንና በማዋጋት ሚና የነበራቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በመጨረሻም የአመራር ጥበቃ ሲያስተባብሩ ቆይተው በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ከፍተኛ ኃላፊው ገልጸዋል።
በቁጥጥር ስር መዋላቸው ከተገለጹት ከአቶ ስብሐት ነጋ በተጨማሪ ባለቤታቸው ሌተናል ኮሎኔል ፀአዱ ሪች፣ ኮሎኔል ክንፈ ታደሰ፣ ኮሎኔል የማነ ካህሳይ የተባሉ የቀድሞ የመከላከያ ሠራዊት አባላት የነበሩ ናቸው ተብሏል።
ከተጠቀሱት በተጨማሪ ሎችም ሰዎች በቁጥጥር ስር የዋሉ ሲሆን ከዚህ ባሻገር ደግሞ በዙሪያቸው የነበረ ታጣቂ ኃይል ላይ እርምጃ እንደተወሰደበት ብርጋዲየር ጀነራል ተስፋዬ አያሌው ገልፀዋል።
ሐሙስ ዕለት መከላከያ ሠራዊቱ በሕግ ከሚፈለጉ ከፍተኛ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አራቱ መገደላቸውንና ዘጠኙ ደግሞ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ማሳወቁ ይታወሳል።
ከእነዚህም የህወሓት አመራሮች መካከል የአቶ ስብሐት ነጋ እህት የሆኑትና የቀድሞ የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ ይገኙበታል።
በእርምጃው ከተገደሉት መካከል አቶ ሴኩቱሬ ጌታቸው፣ የህወሓት ቀደምት ታጋይና የቀድሞው የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ዋና ሥራ አስኪያጅ እንዲሁም የብሮድካስት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ ዘርዓይ አስገዶም፣ የህወሓት የመገናኛ ብዙሃን ተቋም የሆነው ድምጺ ወያኔ ኃላፊ አቶ አበበ ገብረመድኅን፣ የትግራይ ክልል ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳንኤል አሰፋ ከተገደሉት ከፍተኛ አመራሮች መካከል እንደሆኑ ተገልጿል።
ከተገደሉት አራት ሰዎች ባሻገር ሌሎች ዘጠኝ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች በጸጥታ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ጀነራሉ ተናግረዋል።
ቀደም ሲል የተያዙ
ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይም በተመሳሳይ የጸጥታ ኃይሉ ባደረገው አሰሳ የተገደሉና በቁጥጥር ስር የዋሉ የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮች የስም ዝርዝር ይፋ መደረጉ ይታወሳል።
እስካሁን ድረስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮን ገብረሚካኤልም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ያሉበት ሁኔታ በዚህ መግለጫ ላይ አልተጠቀሰም።
ከጥቂት ሳምንት በፊት የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል።
በዚህ መግለጫ የአገር መከላከያ ሚኒስቴር ዓርብ ታኅሳስ 23 ቀን 2013 ዓ. ም. በሰጠው መግለጫ፤ የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ሙሉ ገብረእግዚአብሔርና በርካታ ወታደራዊ መኮንኖች መማረካቸውን እንዲሁም በርካቶች መደምሰሳቸውን አስታወቆ ነበር።
መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ተገድለዋል ያላቸውን የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮችን በተመለከተ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን የተሰማ ነገር የለም።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።
እስካሁን መገደላቸው እንዲሁም መያዛቸው ከተገለፁ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች ሌላ የቀድሞው የትግራይ ክልል ፕሬዝዳንትና በቻይና የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩት አዲስዓለም ባሌማንና የቀድሞዋን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬርያ ኢብራሂም ጨምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ይገኛሉ።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን መወገዱ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ወታደራዊና ፖለቲካዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይፋ አደረገው ነበር።
ለእስር ማዘዣውም ዋነኛ ምክንያቶቹ ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል በሚል ተጠርጥረው ነው።
በተጨማሪም የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮችም በአገር ክደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ተጠርጥረው የመያዣ ትዕዛዝ ወጥቶባቸዋል።
















