በቤንሻንጉል በተፈጸሙ ጥቃቶች ሰበብ 100 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸው ተገለጸ

በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተፈጸሙ ጥቃቶች ለደኅንነታቸው በመስጋት ቤት ንብረታቸውን ጥለው የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር 100 ሺህ መድረሱን የክልሉ መንግሥት ለቢቢሲ አስታወቀ።
የቤንሻንጉል ከልል አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ታረቀኝ ታሲሳ እንዳሉት በቅርቡ በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ከተፈጸመውና ጥቃት በኋላ ቀያቸውን ጥለው የሸሹትን ጨምሮ 100 ሺህ ሰዎች መፈናቀላቸውን አረጋግጠዋል።
በክልሉ መተከል ዞን አምስት ወረዳዎች ከሐምሌ ወር 2012 ዓ.ም ወዲህ ዳግም መፈናቀል መከሰቱን የተናገሩት አቶ ታረቀኝ፤ እነሱም ማንኩሽ፣ ድባጢ፣ ቡለን፣ ወንበራ እና ማንዱራ ወረዳዎች መሆናቸውን አመልክተዋል።
በዳንጉራ፣ በኩጂ እና አዲስ ዓለም ወረዳዎች ተፈናቃዮች መኖራቸውን የተናገሩት ኃላፊው፤ ከእነዚህ መካከል ስድስ ሺህ የሚሆኑት ጉባ የሚባል አካባቢ፣ 6 ሺህ 800 የሚሆኑት ደግሞ ወንበራ፣ ማንዱራ 12 ሺህ፣ በድባጤ 14 ሺህ፣ በቡለን ደግሞ 51 ሺህ የሚጠጉ ተፈናቃዮች እንደሚገኙ አብራርተዋል።
በመተከል ዞን ቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ ታኅሳስ 13/2013 ዓ. ም ንጋት ላይ በታጣቂዎች በተጸፈመ ጥቃት 207 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውን በወቅቱ የአካባቢው ባለስልጣን ለቢቢሲ አረጋግጠው ነበር።
የኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽንም በጥቃቱ ስለተገደሉት ሰዎች ዝርዝር ሲገልጽ ከሟቾቹ መካከል አዋቂዎቹ 133 ወንዶችና 35 ሴቶች ሲሆኑ፤ አንድ የስድስት ወር ሕጻንን ጨምሮ 17 ሕጻናት ተገድለዋል ብሎ ነበር። አክሎም የቀሩት 20 ሰዎች ደግሞ አዛውንቶች መሆናቸው ገልጾ ነበር።
የቤንሻንጉል ክልል ከ2010 ዓ.ም ጀምሮ በነበሩ ግጭቶች የተነሳ መፈናቀል እንደነበር የገለፁት አቶ ታረቀኝ፣ ነገር ግን እነዚህን ሰዎች እስከ 2012 ድረስ ሙሉ በሙሉ ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስታውሰዋል።
አሁን ግን ከሐምሌ ወር ጀምሮ በተፈጸሙ ተከታታይ ጥቃቶች በክልሉ የተለያዩ ስፍራዎች ሰዎች ተፈናቅለው የዕለት እርዳታ ጠባቂ መሆናቸውን ተናግረዋል።
በክልሉ አምስት ወረዳዎች ተፈናቅለው የመንግሥትን እርዳታ ከሚጠብቁ ግለሰቦች በተጨማሪ፣ ወደ አጎራባች ክልሎች የተሰደዱ መኖራችን ገልፀው ቻግኒ ከተማ ላይ፣ ማንጡራ ቀበሌ እንዲሁም ራንች በሚባል ስፍራ በርካታ ተፈናቃዮች መኖራቸውን መረጃ እንዳላቸው ተናግረዋል።
ከተፈናቃዮቹ ውስጥ ሕጻናት፣ ሴቶች እና አረጋውያን እንዳሉበት የሚገልፁት አቶ ታረቀኝ፤ ለሕጻናት እና ለሚያጠቡ እናቶች አልሚ ምግብ እንዲሆን ለተፈናቃይ በነፍስ ወከፍ በወር 15 ኪሎ የእርዳታ እህል እንደሚሰጥ ገልፀዋል።
የተፈናቃይ ቁጥር ከፍተኛ መሆኑን የሚናገሩት ኃላፊው ይህንንም ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ ለፌደራል አደጋ ሥራ አመራር ኮሚሽን ማሳወቃቸውን ተናግረዋል።
የእርዳታ ሥርጭቱን በተለያዩ አካባቢዎች ለማዳረስ ከስፋቱ እንጻር አስቸጋሪ የነበረ ቢሆንም አሁን ግን በተቻለ መጠን ለማዳረስ ጥረት እና ርብርብ እየተደረገ መሆኑንም አክለዋል።
በመጠለያ ጣቢያ ውስጥ የሚገኙ የተወሰኑ ተፈናቃዮች አሁንም የደኅንነት ስጋት እንዳለባቸው እና በሚሊሻ ብቻ መጠበቃቸው ስጋት ውስጥ እንደጣላቸው የተጠየቁት ኮሚሽነሩ፣ ስጋቱ መኖሩን ገልፀው ነገር ግን ኮማንድ ፖስቱ በቅርብ ርቀት ሆኖ እየጠበቀ ነው ብለዋል።
ከክልሉ በተጨማሪ ከፌደራል፣ ከበጎ አድራጎት ድርጅቶች እንዲሁም ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የመጣን የምግብ እና አልባሳት እርዳታን በፍጥነት ወደ መጠለያ ጣብያዎቹ ለማድረስ መኪኖች መዘጋጀታቸውን ተናግረዋል።
በዞኑ በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ተፈናቅለው ድጋፍ ለሚፈልጉ ከ100 ሺህ በላይ ዜጎች ክልል አቀፍ የገቢ አሰባሳቢ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ ሥራ እንደጀመረ መገለፁ ይታወሳል።
አቶ ታረቀኝ በዘላቂነት ተፈናቃዮቹ ወደ መጡበት አካባቢ እንዲመለሱ እና እንደሚቋቋሙ ለማድረግም እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልፀዋል።
ለበርካታ ሰዎች መፈናቀል ምክንያት የሆነውን በቅርቡ የተጸፈመውን ጥቃት ተከትሎ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች በወሰዱት እርምጃ ከ40 በላይ ታጣቂዎችን መግደላቸው ተገልጾ የነበረ ሲሆን፤ ከቀናት በፊትም በነዋሪዎች ላይ ጥቃት ሲፈጽሙ ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል 17ቱ በቁጥጥር ስር መዋላቸውን የክልሉ ኮማንድ ፖስት ማስታወቁ ይታወሳል።
ከዚህ በተጨማሪ በክልሉ በመተከል ዞን በተለይ በቡለን ወረዳ በኩጂ ቀበሌ በተፈፀመው አሰቃቂ ግድያ ጋር በተያያዘ ተጠርጥረው ዘጠኝ የክልልና የዞን አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የክልሉ ኮምዩኒኬሽን ቢሮ ለቢቢሲ ገልጾ ነበር።














