በቤኒሻንጉል ጉሙዝ መተከል ዞን ማብቂያ ያላገኘው ጥቃት

ታኅሣሥ 13 ቀን 2013 ዓ.ም በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል፣ መተከል ዞን፣ ቡለን ወረዳ፣ በኩጂ ቀበሌ ከለሊቱ 10፡00 ሰዓት አካባቢ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ከ100 በላይ ሰዎች በአሰቃቂ ሁኔታ መገደላቸውን የተለያዩ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች ድርጅቶች ይፋ አድርገዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው የቡለን መጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ባለሙያዎች በበኩላቸው በዚህ ጥቃት ብቻ ከ30 በላይ ሰዎች በጥይትና በቀስት ተመትተው፣ በስለት ተወግተው የሕክምና እርዳታ ለማግኘት መጥተዋል።
የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ የሆኑት አቶ መለሰ በየነ የሟቾችን ቁጥር "እጅግ በጣም ከፍተኛ" ከማለት ውጪ ትክክለኛውን ቁጥር ከመግለጽ ተቆጥበዋል።
አክለውም በዞኑ የሰላም መደፍረስ እጃቸው አለበት የተባሉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ የክልሉ ሰባት አመራሮች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ተናግረዋል።
ረቡዕ ማለዳ ጥቃት ከተፈፀመባት በኩጂ ቀበሌ አቅራብያ በምትገኝ ዶቢ ቀበሌ ማምሻውን በነበረ ጥቃትም አምስት ሰዎች መገደላቸውን ቢቢሲ ከነዋሪዎች መረጃ ያገኘ ሲሆን፤ የክልሉ ኮሙኑኬሽን ኃላፊ ስለጥቃቱ "መስማታቸውን ነገር ግን የተጣራ መረጃ እንደሌላቸው" ገልፀዋል።
የመተከል ዞን አራት ወረዳዎች የፀጥታ ኃላፊነት ከመስከረም 14 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በኮማንድ ፖስት ስር እንዲሆን በተሰጠ ውሳኔ መሰረት የጸጥታ ማስከበሩን ሥራ የፌደራሉ መንግሥት ተረክቧል።
በኮማንድ ፖስቱ ስር የሆኑት የዳንጉር፣ የወምበራ፣ ቡለን እና ጉባ ወረዳዎች ናቸው።
የታኅሣስ 13 ጥቃት የተፈፀመባት በኩጂ
በኩጂ ቀበሌ ከወረዳው መቀመጫ ከሆነችው ቡለን ከተማ 90 ኪሎ ሜትር ርቃ የምትገኝ ሲሆን የሺናሻ፣ የኦሮሞና የአማራ ተወላጆች ይኖሩባታል።
በቀበሌዋ ይህ ጥቃት የደረሰው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድና ከፍተኛ የፌደራል መንግሥቱ እንዲሁም የክልሉ ባለስልጣናት ወደ አካባቢው ሄደው ከተለያዩ የማኅበረሰብ ክፍሎች ጋር በመገናኘት በክልሉ ስላለው የሰላም መደፍረስ ከተወያዩና የመፍትሔ አቅጣጫዎች ካስቀመጡ በኋላ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ ወደ መተከል ያመሩት ታኅሣስ 13/2013 ማለዳ ሲሆን ጥቃቱ የተፈፀመው ደግሞ የዛኑ ዕለት ምሽት ላይ ነበር።
እንደ አካባቢው ነዋሪዎች ከሆነ እንዲህ አይነት ጥቃት መድረስ የጀመረው ካለፈው ዓመት ጳጉሜን 2012 ዓ.ም ጀምሮ ሲሆን እስካሁን ድረስ በእነዚህ ጊዜያቶች ውስጥ ሦስት ትላልቅ ጥቃቶች ተፈጽመዋል።
በዚህም የበርካታ ንፁሃን ዜጎች ሕይወት አልፏል። ንብረት ወድሟል። እንዲሁም ቤት ንብረታቸውን ጥለው እንዲሰደዱ ምክንያት ሆኗል።
በተለያየ ጊዜ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል በአንዳንድ አካባቢዎች እየታዩ ያሉ የፀጥታ መደፍረሶችን ተከትሎ ያጋጠሙ ክስተቶች እጅግ እንዳሳሰቡት ሲገልጽ ነበር።
ኮሚሽኑ በጳጉሜ 1/2012 ዓ.ም እንዲሁም ከጳጉሜ 2 አስከ መስከረም 3/2013 ዓ.ም መካከል ቢያንስ ሁለት ጥቃቶች ማጋጠማቸውን ከክልሉ መንግሥት ማረጋገጡን ገልጾ ነበር።
መስከረም 15 ቀን 2013 ዓ.ም ከንጋቱ 11 ሰዓት ገደማ በመተከል ዞን፣ ዳንጉር ወረዳ፣ ማንቡክ ከተማ በንገዝ ወንዝ አካባቢ በሚገኝ መንደር ላይ በታጠቁ ሰዎች በተከፈተ ተኩስ የ15 ሰዎች ሕይወት ማለፉን በወቅቱ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ያወጣው መግለጫ ያሳያል።
ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም ደግሞ ሌሊት፣ በደባጤ ወረዳ ከወንበራ ወደ ቻግኒ በመጓዝ ላይ በነበረ የሕዝብ ማመላሻ አውቶብስ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መሞታቸው በወቅቱ በክልሉና በሰብዓዊ በብቶች ኮሚሽን ተገልጾ ነበር።
በወቅቱ የኢሰመኮ ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ "ይህ ጥቃት ሁላችንም በጋራ የተሸከምነውን የሰው ሕይወት ክፍያ ዛሬም በአሳዛኝ ሁኔታ የሚያሻቅብ ነው። የመንግሥት የፀጥታ ኃይሎች በፍጥነት ጥቃቱ የበለጠ እንዳይባባስ እርምጃ መውሰዳቸው አበረታች ነው" ብለው ነበር።
ሦስተኛው ጥቃት ታኅሣስ 13 የተፈፀመውና ቢቢሲ ከነዋሪዎችና ከአይን እማኞች ባደረገው ማጣራት 120 ሰዎች ሕይታቸውን ያጡበት የአሁኑ ጥቃት ነው።
ከዚህ ውጪ ግን ቢቢሲ ባደረጋቸው የተለያዩ ማጣራቶች በክልሉ ከመስከረም ወር ወዲህ ተለያየ መጠን ያላቸውን ጉዳቶች ያስከተሉ ወደ 20 የሚጠጉ ጥቃቶች ተፈፅመዋል።
በመተከል ዘላቂ ሰላም ማምጣት ለምን አልተቻለም?
የክልሉ መንግሥት በመተከል ዞን ከተፈጠረው የጸጥታ ችግር ጋር በተያያዘ እጃቸው አለበት የተባሉ አመራሮችን በሕግ ቁጥጥር ሥር እያዋለ መሆኑን ተናግሯል።
የክልሉ የኮሙኑኬሽን ኃላፊ አቶ መለሰ በየነ እስካሁን ድረስ ሰባት ሰዎች በቁጥጥር ስር መዋላቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።
በተፈጠረው የጸጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው ያለበትን፣ ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ያልተወጡ አመራሮችን በሚል በቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ መካከል አቶ ቶማስ ኩዊ የኢፌዴሪ ሠራተኛና ማኅበራዊ ጉዳይ ሚኒስቴር የማኅበራዊ ዘርፍ ሚኒስትር ዲኤታ፣ አቶ አድጎ አምሳያ የቀድሞው የክልሉ ምክትል ርዕሰ-መስተዳድር፣ አቶ ሽፈራው ጨሊቦ የቀድሞ የክልሉ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ኤጀንሲ ዳይሬክተር፣ አቶ ባንዲንግ ማራ የመተከል ዞን ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ፣ አቶ አረጋ ባልቢድ የመተከል ዞን የቀድሞ አመራር የነበሩ ይገኙበታል።
ዛሬ በተጨማሪ ሁለት የክልሉ ከፍተኛ አመራሮች እጃቸው አለበት በሚል ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን አቶ መለስ በየነ ለቢቢሲ ተናግረዋል።
እነዚህ ግለሰቦች አቶ ገመቹ አመንቲ፣ የክልሉ የግዢና ንብረት ማስወገድ ኤጀንሲ ዋና ዳይሬክተር እንዲሁም አቶ አድማሱ መልካ የገጠር መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ምክትል ዳይሬክተር መሆናቸውን ገልፀዋል።
እነዚህ አመራሮች ከመተከል ዞን የጸጥታ ችግር ጋር እጃቸው እንዳለበት በመረጋገጡ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለዋል ይባል እንጂ ከዚህ ቀደምም በዚሁ ዞን ኅዳር 5 ቀን 2013 ዓ.ም በተከሰተ የጸጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት የተጠረጠሩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር ለቢቢሲ ተናገረው ነበር።
እነዚህ በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች አመራር የነበሩ 45 ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን በወቅቱ አቶ ይስሐቅ ገልፀዋል።
በዚያ ጊዜ ከኃላፊነታቸው ከተነሱ የክልል አመራሮች መካከል የክልሉን ፖሊስ በምክትል ኮሚሽነርነት እየመሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች እንደሚገኙበት የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ ተናግረዋል።
በዞን ደረጃ ስድስት አመራሮች፣ የዳንጉር፣ ቡለን፣ ወንበራ ወረዳ ዋና እና ምክትል አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ቁልፍ አመራሮችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የተነሳ ከቦታቸው መነሳታቸውን ጨምረው ተናግረው ነበር።
በመተከል ዞን በተለያየ ወቅት በደረሱ ጥቃቶች እጃቸው አለበት ወይንም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ኃላፊዎችና ታጣቂዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሲውሉ አዲስ አለመሆኑን ያነሱት አቶ ይስሃቅ፤ አሁንም በዞኑ ማረሚያ ቤት የሚገኙና ሁለት ዓመት ሙሉ ክስ ያልተመሰረተባቸው ግለሰቦች እንደሚገኙ አስረድተዋል።
ይህም ቅሬታን ፈጥሯል የሚሉት አቶ ይስሃቅ ይህ የሆነበት ምክንያትን ሲያስረዱ የእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የተያዘው በፌደራል መርማሪ ቡድን በመሆኑ እንደሆነ ይገልፃሉ።
የፌደራል መርማሪ ቡድኑ በየጊዜው በተዘዋዋሪ ችሎት በመምጣት ጉዳዩን እንደሚመለከት የተናገሩት ኃላፊው የተፋጠነ ፍትህ አለማግኘት ቅሬታዎችን መፍጠሩን ይናገራሉ።
ይህ በመተከል ዞን ብቻ የሚታይ ሳይሆን ካማሼ ዞንም አንድ ዓመት እና ከዚያ በላይ ክስ ሳይመሰረትባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውንም ገልፀዋል።
እነዚህ ሰዎች የተፋጠነ ፍርድ እንዲያገኙ ክልሉ ከዐቃቤ ሕግ ጋር እየተነጋገረ መሆኑን ጨምረው ገልፀው ነበር።
ጥቃቶቹ ለምን ይፈጸማሉ?
ጥቃቱን እያደረሱ የሚገኙት ታጣቂዎች ከሌላ ቦታ የመጡ አለመሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ይስሃቅ፣ በአብዛኛው ባለፈው ዓመት ጃዊ አካባቢ በነበረው ጥቃት "መንግሥት ሊከላከለን አልቻለም" በሚል ቅሬታ የገባቸው ወጣቶች ሸፍተው ጫካ መግባታቸውን ተናግረው ነበር።
በወቅቱ ጥቃቱ ሲደርስ በአመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ ግለሰቦች አልተጠየቁም የሚል ቅሬታ በወጣቶቹ ዘንድ መፈጠሩን ያነሱት አቶ ይስሃቅ፣ ነገር ግን የክልሉንና የአገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች በተለይ "ከሕዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ" ወጣቶቹን በሱዳን ጠረፍ አካባቢ አስታጥቀው አሰልጥነው ወደ አካባቢው እንዲገቡ ማድረጋቸውን ለቢቢሲ ገልፀዋል።
በማኅበራዊ መገናኛ ብዙሃንም "መተከል የኛ ነው" የሚል ቅስቀሳ መኖሩ እና ይህም የአካባቢዎቹን ወጣቶች ላይ 'የእኛ እጣ ፈንታ ምንድን ነው?' የሚል ስጋት መፈጠሩን ተናግረዋል።
ይህ ግን የአማራ ክልልም ሆነ የሕዝቡ አቋም አለመሆኑን የሚገልፁት አቶ መለስ "ጥቂት ኃይሎች የሚያራምዱት ሃሳብ" መሆኑን ይናገራሉ።
ክልሉ መሬት ወስደው ሳያለሙ በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ በወሰደው እርምጃ ቅሬታ የገባቸው የተለያዩ ኃይሎችም የሚነሱትን ግጭቶች በመደገፍ ተሳትፎ ማድረጋቸውን አቶ ይስሐቅ ለቢቢሲ ገልፀው ነበር።
ጥቃቱን ከፈፀሙ እና በተወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር ከዋሉት በተገኘው መረጃ መሰረት በክልሉ የሚንቀሳቀስ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ተልዕኮ እንደሰጣቸው የተናገሩ ወጣቶች መኖራቸውንም ጨምረው ተናግርዋል።
ይህ አቶ ይስሃቅ በስም የሚጠቅሱት ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ግልጽ ቅስቀሳ የሚያደርግ እንደነበር አንስተው፣ በተጨማሪ ደግሞ የአካባቢው መልከአምድር፣ እንዲሁም መሰረተ ልማቶች አለመሟላታቸው ለታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀዋል።














