በቤንሻንጉል ክልል መተከል ዞን ዘላቂ ሰላም ማምጣት ለምን አልተቻለም?

የኢትዮጵያ ካርታ

በመተከል ዞን በተከሰተው የፀጥታ ችግር ውስጥ እጃቸው አለበት የተባሉ እና ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣት የተጠረጠሩ ከክልል እስከ ወረዳ ያሉ አመራሮች ላይ ፖለቲካዊ እርምጃ መወሰዱን የክልሉ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ይስሃቅ አብዱልቃድር ለቢቢሲ ተናገሩ።

የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በመተከል ዞን የተለያዩ ወረዳዎች አመራር የነበሩ 45 ግለሰቦች ሙሉ በሙሉ ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ መደረጉን የተናገሩት ኃላፊው እጃቸው አለበት በሚል ጥቆማ የቀረበባቸው በሕግ እንዲጠየቁ እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አጠቃላይ በተደረገው በወረዳ አመራር ግምገማ "በተለያየ መንገድ ከፀረሰላም ኃይሎች ጋር እጃቸው አለበት" ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች ላይም እርምጃው መወሰዱን ተናግረዋል።

ስራቸውን በአግባቡ አልተወጡም፣ የሕዝብን ደህንነት ማስጠበቅ አልቻሉም፣ መረጃ እያላቸው ቸልተኛ ሆነዋል በሚል ተገምግመው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ከተደረጉ 45 አመራሮች መካከል በወንጀል ውስጥ በመሳተፍ እጃቸው አለበት የሚል ጥቆማ የቀረበባቸው አስር የወረዳ አመራሮች በህግ ቁጥጥር ስር መዋላቸውን ተናግረዋል

ከኃላፊነታቸው ከተነሱ የክልል አመራሮች መካከል የክልሉን ፖሊስ በምክትል ኮሚሽነርነት እየመሩ የነበሩ ሁለት ግለሰቦች ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን አቶ ይስኃቅ ተናግረዋል።

በዞን ደረጃ ስድስት አመራሮች፣ በዳንጉር፣ ቡለን፣ ወንበራ ወረዳ ዋና እና ምክትል አስተዳዳሪዎች እንዲሁም ቁልፍ አመራሮችም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ ባለመወጣታቸው የተነሳ ከኃላፊነታቸው መነሳታቸውን ጨምረው ገልፀዋል።

እነዚህ ኃላፊዎች ላይ በወንጀል መሳተፋቸውን የሚያሳይ መረጃ ከተገኘ በሕግ ቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እንደሚደረግ አክለው ተናግረዋል።

ግምገማው እስከ ታችኛው መዋቅር ድረስ እንደሚቀጥል የተናገሩት አቶ ይስኃቅ፣ ኅብረተሰቡን የማረጋጋትና የተፈናቀሉትን ወደ ቀያቸው የመመለስ ስራ እየተሰራ ከኃላፊነት የተነሱት አመራሮች የነበራቸው ተሳትፎ ላይ መረጃ ከተገኘ በሕግ የመጠየቁ ስራ እንዲቀጥል መወሰኑን ተናግረዋል።

በክልልና በዞን ደረጃ የሚገኙ አመራሮች የተሰጣቸውን ኃላፊነት በአግባቡ ባለመወጣታቸው ሲገመገሙ፣ በወረዳ ደረጃ በቀጥታ ተሳትፎ አላቸው ተብለው የተጠረጠሩ አመራሮች መገኘታቸውንም ገልፀዋል።

በወረዳ ደረጃ አመራር የነበሩና ቀጥታ ተሳትፎ ኖሯቸው በሕግ ቁጥጥር ስር ከመዋላቸው በፊት የሸሹ መኖራቸውን ኃላፊው አስረድተዋል።

በቀበሌ ደረጃ በቀጣይ ቀናት ግምገማው እንደሚቀጥል አስረድተዋል።

ዘላቂ ሰላም በዞኖቹ ማምጣት ለምን አልተቻለም?

ጥቃቱን እያደረሱ የሚገኙት ታጣቂዎች ከሌላ ቦታ የመጡ አለመሆናቸውን የሚገልፁት አቶ ይስሃቅ፣ በአብዛኛው ባለፈው ዓመት ጃዊ አካባቢ በነበረው ጥቃት "መንግሥት ሊከላከለን አልቻለም" በሚል ቅሬታ የገባቸው ወጣቶች ሸፍተው ጫካ መግባታቸውን ይናገራሉ።

በወቅቱ ጥቃቱ ሲደርስ በአመራርነት ቦታ ላይ የነበሩ ግለሰቦች አልተጠየቁም የሚል ቅሬታ በወጣቶቹ ዘንድ መፈጠሩን ያነሱት አቶ ይስሃቅ፣ ነገር ግን የክልሉንና የአገሪቱን ሰላም የማይፈልጉ ኃይሎች በተለይ "ከሕዳሴ ግድቡ ጋር በተያያዘ" ወጣቶቹን በሱዳን ጠረፍ አካባቢ አስታጥቀው አሰልጥነው ወደ አካባቢው እንዲገቡ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀንም "መተከል የኛ ነው" የሚል ቅስቀሳ መኖሩ እና ይህም የአካባቢዎቹን ወጣቶች ላይ 'የእኛ እጣ ፈንታ ምንድን ነው?' የሚል ቅሬታ መፈጠሩን ተናግረዋል።

በቡለንና ወንበራ ወረዳዎች ላይ በደረሱ ጥቃቶች ሕይወታቸውን ያጡ ግለሰቦች የአንድ ብሔር ብቻ ተወላጆች እንደሆኑ ተደርጎ በማህበራዊ መገናኛ ብዙኀን የሚደረግ ቅስቀሳም አካባቢው እንዳይረጋጋ ማድረጉን ተናግረዋል።

ክልሉ መሬት ወስደው ሳያለሙ በተቀመጡ ባለሃብቶች ላይ በወሰደው እርምጃ ቅሬታ የገባቸው የተለያዩ ኃይሎችም የሚነሱ ግጭቶችን በመደገፍ ተሳትፎ ማድረጋቸውን ገልፀዋል።

ጥቃቱን ከፈፀሙ እና በተወሰደው እርምጃ በቁጥጥር ስር ከዋሉት በተገኘው መረጃ መሰረት በክልሉ የሚንቀሳቀስ አንድ ተፎካካሪ ፓርቲ ተልዕኮ እንደሰጣቸው የተናገሩ ወጣቶች መኖራቸውንም ጨምረው ተናግርዋል።

ይህ አቶ ይስሃቅ በስም የሚጠቅሱት ተቃዋሚ ፓርቲ፣ ግልጽ ቅስቀሳ የሚያደርግ እንደነበር አንስተው፣ በተጨማሪ ደግሞ የአካባቢው መልከአምድር፣ እንዲሁም መሰረተ ልማቶች አለመሟላታቸው ለታጣቂ ኃይሎች እንቅስቃሴ ምቹ ሁኔታ መፍጠሩን ገልፀዋል።

ክልሉ ምን እርምጃ እየወሰደ ነው?

የክልሉ ልዩ ኃይል እና መከላከያ ከአካባቢው ማህበረሰብ ጋር በመሆን በተለያየ ወቅት ርምጃ እንደሚወሰድ ኃላፊው ተናግረዋል።

በአጠቃላይ ክልሉ በወሰደው ሰላም የማስከበር እርምጃ እስከ እሁድ ድረስ በጥቃቱ ላይ በቀጥታ የተሳተፉ 391 ሰዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል ያሉት አቶ ይስሃቅ፣ በቁጥጥር ስር የዋሉት ታጣቂዎቹን በመቀለብ ሲረዱ የነበሩ፣ የተለያየ ግንኙነት የነበራቸውና በቀጥታ ታጣቀው ጥቃት የፈፀሙ መሆናቸውን ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በመተከል ዞን በተለያየ ወቅት በደረሱ ጥቃቶች እጃቸው አለበት ወይንም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አልተወጡም በሚል ኃላፊዎችና ታጣቂዎች ተጠርጥረው በቁጥጥር ሲውሉ አዲስ አለመሆኑን ያነሱት አቶ ይስሃቅ፣አሁንም በዞኑ ማረሚያ ቤት የሚገኙ እና ሁለት ዓመት ሙሉ ክስ ያልተመሰረተባቸው ግለሰቦች እንደሚገኙ አስረድተዋል።

ይህም ቅሬታን ፈጥሯል የሚሉት አቶ ይስሃቅ ይህ የሆነበት ምክንያትን ሲያስረዱ የእነዚህ ተጠርጣሪዎች ጉዳይ የተያዘው በፌደራል መርማሪ ቡድን በመሆኑ እንደሆነ ይገልፃሉ።

የፌደራል መርማሪ ቡድኑ በየጊዜው በተዘዋዋሪ ችሎት በመምጣት ጉዳዩን እንደሚመለከት የሚናገሩት ኃላፊው የተፋጠነ ፍትህ አለማግኘት ቅሬታዎችን መፍጠሩን ይናገራሉ።

ይህ በመተከል ዞን ብቻ የሚታይ ሳይሆን ካማሼ ዞንም አንድ አመት እና ከዚያ በላይ ክስ ሳይመሰረትባቸው በማረሚያ ቤት የሚገኙ ተጠርጣሪዎች መኖራቸውን ገልፀዋል።

እነዚህ ሰዎች የተፋጠነ ፍርድ እንዲያገኙ ክልሉ ከአቃቤ ሕግ ጋር እየተነጋገሩ መሆኑን ጨምረው ገልፀዋል።