በቤንሻንጉል ክልል በሽፍቶች በደረሰ ጥቃት ከ30 በላይ ሰዎች መገደላቸው ተገለፀ

ርዕሰ መስተዳድር አሻዲል ሀሰን

የፎቶው ባለመብት, Benishangul Communication

በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ዳንጉር ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች ባደረሱት ጥቃት ሕጻናትን ጨምሮ ከ30 ሰዎች በላይ መሞታቸውን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻዲል ሀሰን ለቢቢሲ ገለፁ።

ጥቃቱ የደረሰው እሁድ ለሰኞ አጥቢያ 11 ሰዓት ላይ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ በጥቃቱ ወደ 16 ሰዎች መቁሰላቸውን ገልፀው ወደ 66 ቤቶች በቃጠሎ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውን ተናግረዋል።

ከዚህ በፊት በአማራ ክልል የሚኖሩ የጉሙዝ ተወላጆች ላይ ተመሳሳይ ጥቃት መድረሱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ ያኔም ለቁጥር መግለፅ ከባድ ያሉት ሰው መሞቱን ተናግረዋል።

ጥቃት አድራሾቹ 'ከአማራ ክልል መምጣታቸውን' የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ በቁጥጥር የዋለ መሳሪያና ሰው ቢኖርም ምን ያህል እንደሆነ ግን የተጠናከረ መረጃ እንደሌላቸው ገልፀዋል።

በስፍራው አሁንም ስጋት መኖሩን የተናገሩት አቶ አሻድሊ ሀሰን ጉዳዩን ለመፍታት ከመከላከያና ከፌደራል የፀጥታ ኃይሎች ጋር እየሰሩ መሆኑን ጨምረው አስረድተዋል።

በጉዳቱ የቆሰሉ ሰዎች በፓዊ ሆስፒታል ህክምና እየተደረገላቸው መሆኑን ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው ገልፀዋል።