በቤንሻንጉል ጉሙዙ ጥቃት የተጠረጠሩ 20 ታጣቂዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ሐምሌ 20/2012 በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ ጥቃት የፈጸሙ 20 ታጣቂዎች በቁጥጥር ሥር ዋሉ።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱላዚዝ መሃመድ በተለይ ለቢቢሲ እንደገለጹት ግለሰቦቹ በቁጥጥር ሥር የዋሉት ትናንት ነው።
እንደ ምክትል ቢሮ ኃላፊው ከሆነ ታጣቂዎቹ ጥቃቱን ከመፈጸማቸው በፊት የመንግሥት የጸጥታ ኃይል እርምጃ እየወሰደባቸው ነበር።
እርምጃውን ተከትሎ ተበታትነው በመንቀሳቀስ 13 ሰዎች ላይ ግድያ መፈጸማቸውን ጠቁመዋል።
ከጥቃቱ በኋላ በተደረገ የክትትልና የቁጥጥር ሥራ 20 ሰዎች ትናንት መያዛቸውን አቶ አብዱላዚዝ አስታውቀዋል።
ግለሰቦቹ ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 12 መሣሪያዎችም መያዙን ነው የተናገሩት።
በአሁኑ ጊዜ አካባቢው ወደ ሠላማዊ ሁኔታ መመለሱን የገለጹት አቶ አብዱላዚዝ የክልሉን የሠላም ግንባታ እና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊን እና የክልሉን የፖሊስ ኮሚሽነር ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ አመራሮችም ወደ ቦታው በማቅናት ሕዝብን የማራጋጋት እና ችግር ፈጣሪዎቸን በቁጥጥር ስር እያዋሉ ነው ብለዋል።
በጥቃቱ ላይ የተሳተፉ ሁሉም ተጠርጣሪዎች ስለመያዘቸው በተመለከተም፤ የምርመራ ቡድን ተቋቁሞ እየሠራ መሆኑን ተናግረው በውጤቱ መሠረት ተጨማሪ ሰዎች በቁጥጥር ስር ሊውሉ ይችላሉ ብለዋል።
ቢቢሲ ያነጋገራቸው እና ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ በበኩላቸው፤ ጥቃቱን ተከትሎ ከሁለት ቀበሌዎች 200 የሚጠጉ ሰዎች ከመኖሪያ ቀያቸው መሸሻቸውን አስታውቀዋል።
ለተፈናቃዮቹ የአካባቢው ነዋሪ እና መንግሥት ድጋፍ እያደረገላቸው መሆኑንም ተናግረዋል። አንዳንድ ቤታቸው ዘግተው የሸሹ ግለሰቦች ቤት ተሰብሮ ንብረታቸው እንደተዘረፈም ግለሰቡ ጠቁመዋል።
ከጥቃቱ ጋር በተያያዘም በቁጥጥር ስር የዋሉ ግለሰቦች መኖራቸውን እንደሰሙ የገለጹት ነዋሪው፤ ኅብረተሰቡ ውስጥ ሆነው ታጣቂዎችን ሲረዱ የነበሩ ሰዎች አሁንም አለመያዛቸውንም ገልጸዋል።
በአሁኑ ጊዜ የጉባ ከተማ ሠላማዊ ቢሆንም ወጣ ብለው በሚገኙ ቀበሌዎች ስጋት መኖሩን አልሸሸጉም።
ከፌደራል እና ከክልል የመጡ ከፍተኛ አመራሮች ትናንት እና ዛሬ ከአካባቢው የአገር ሽማግሌዎችና ወጣቶች ጋር በመወያየት ላይ ናቸውም ብለዋል።
የቤንሻንልጉ ጉሙዝ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አሻድሌ ሀሰን ትላንት ምሽት ከብሔራዊው ቴሌቪዝን ኢቢሲ ጋር በነበራቸው ቆይታ ድርጊቱን የፈጸሙት "በክልሉ እና ሱዳን ድንበር አካባቢ ስልጠና ሲወስዱ የነበሩ ቡድኖች ናቸው" ሲሉ ተናግረዋል።
ቡድኖቹ ላይ ባለፉት ሁለት ሳምንታት በተከታታይ በተወሰዱ እርምጃዎች 12ቱ መገደላቸውን እና 30 የሚጠጉት መያዛቸውንም ጠቁመዋል።
በአካባቢው ቀደም ሲል የተፈጠረውን ዓይነት ችግር ለመፍጠር ቢታቀድም ከአማራ ክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር በመሆን እንደከዚህ ቀደሙ የማስተካከያ እርምጃ እንንደሚወሰድ ገልጸዋል።
በአሁን ሰዓት አካባቢው ወደ ቀድሞ ሠላሙ መመለሱን ተናግረው የሕግ በላይነትን ለማስከበር በሚደረገው ሥራ ውስጥ ኃላፊነታቸውን ያልተወጡ አመራሮች ላይ ጭምር ሕጋዊና አስተዳደራዊ እርምጃ ይወሰዳል ብለዋል።















