የሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ፡ ከሰኞ ሰኔ 22/2012 እስከ ዛሬ ድረስ

ሃጫሉ ሁንዴሳ

በበርካታ አድናቂዎቹ ዘንድ የሚወደደው ድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ፣ ለመጨረሻ ጊዜ በቴሌቪዥን መስኮት ቀርቦ ቃለ ምልልስ ያደረገው ሰኔ 15/2012 ኦኤምኤን የቴሌቪዥን ጣቢያ ላይ ነበር።

ከሳምንት በኋላም ሰኔ 22/2012 ምሽት የሞቱ ዜና ተሰማ። ሰኔ 24/ 2012 ዓ.ም ደግሞ ግብዓተ መሬቱ በተወለደባት አምቦ ከተማ ተፈጽሟል።

የሃጫሉ ህልፈት ሚሊዮኖችን አስደንግጧል፤ በርካቶችን አስቆጥቷል። አሳዝኗል። ግድያውን ተከትሎም በተነሳ አለመረጋጋት ከ167 በላይ ሰዎች ህይወታቸውን ሲያጡ በሺህዎች የሚቆጠሩ ደግሞ ቤት ንብረታቸው ዶግ አመድ ሆኗል።

ከ7000 በላይ ሰዎችም ከተከሰተው ሁከት ጋር በተያያዘ መታሰራቸውን የመንግሥት ባለስልጣናት ከሰጡት መግለጫ መረዳት ይቻላል።

የኦኤምኤን ቃለ መጠይቅ

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ከመገደሉ ከአንድ ሳምንት በፊት ከኦሮሞ ሚዲያ ኔትዎርክ (ኦኤምኤን) ጋር ያደረገው ቃለ መጠይቅ አየር ላይ ውሎ ነበር። ሃጫሉ ለመጨረሻ ጊዜ ለሕዝብ የታየውም በዚያ ቃለ መጠይቅ ላይ ነው።

ሃጫሉ ከኦኤምኤን ጋር በነበረው ቆይታ በሰጣቸው አስተያየቶች መነጋገሪያ ሆኖ ነበር።

ሃጫሉ ከተገደለ በኋላ ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ከሰጣቸው መግለጫዎች በአንዱ፤ በኦኤምኤን ላይ የተደረገው ቃለ መጠይቅ፣ ድምጻዊው ከሌሎች ማኅበረሰቦች ጋር እንዲጋጭ የሚያደርጉ ሌሎች አመለካከቶቹን እንዲያጸባርቅ በጠያቂው በኩል ተደርጓል ሲሉ በጠቅላይ አቃቤ ሕግ የተደራጁ እና ድንበር ተሻጋሪ ወንጀሎች ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ፍቃዱ ጸጋ ተናግረዋል።

ሰኔ 23 ረፋዱ ላይም በአዲስ አበባ የሚገኘው የኦኤምኤን ቢሮ በፌደራል ፖሊስ ብርበራ ተካሂዶበት እንዲዘጋ ተደርጓል። ሃጫሉ ሁኔዴሳን ያነጋገረው ጋዜጠኛም ቆየት ብሎ በቁጥጥር ሥር ውሏል።

ሃጫሉ ለመጨረሻ ጊዜ ለህዝብ የታየውም በኦኤምኤን ቃለ መጠይቅ ላይ ነበር

የፎቶው ባለመብት, OMN

የምስሉ መግለጫ, ሃጫሉ ለመጨረሻ ጊዜ ለህዝብ የታየውም በኦኤምኤን ቃለ መጠይቅ ላይ ነበር

የመገደሉ ዜና

ሰኔ 22 ከምሽቱ 3፡30 አካባቢ አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ማንነታቸው ባልታወቁ ሰዎች ገላን ኮንዶሚኒየም ተብሎ በሚጠራው ስፍራ በጥይት ተመትቶ መገደሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ከእኩለ ለሊት በኋላ ይፋ አደረገ።

የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር ጌቱ አርጋው በብሔራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው በተናገሩበት ወቅት በግድያው ወንጀል የተጠረጠሩ የተወሰኑ ሰዎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ገልጸዋል።

የሃጫሉ ሁንዴሳ በጥይት ተመቶ የመገደል ዜና ከፖሊስ መግለጫ በፊት በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መዘዋወር የጀመረው ከምሽቱ 5፡30 አካባቢ ጀምሮ ነው።

ሌሊቱን በፌስቡክ አማካኝነት ሲሰራጩ በነበሩ የቀጥታ ስርጭቶች፤ በርካቶች መንገድ ላይ በመውጣት ሲያለቅሱ ታይተዋል።

ሃጫሉ በጥይት ከተመታ በኋላ ወደ ጥሩነሽ ቤጂንግ ሆስፒታል ተወስዶ ነበር። ከዚያም የሃጫሉ አስክሬን ለምርመራ ወደ ጳውሎስ ሆስፒታል ተላከ።

ቁጣ፣ አለመረጋጋት እና ጥቃት

የሃጫሉን ግድያ ተከትሎ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች ቁጣ ተሰምቷል፣ አለመረጋጋት ተከስቷል፤ በንጹሃን ዜጎች ህይወት እና ንብረት ላይም ጥቃቶች ተፈጽሟል።

ንጋት ላይ እንደ አዳማ፣ ጅማ እና ጭሮ ባሉ ከተሞች የተቃውሞ ሰልፎች ተካሄዱ። በምሥራቅ እና ምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኙ ከተሞች ደግሞ መንገዶች ዝግ ተደረጉ።

በሌሎች አከባቢዎች ደግሞ ማክሰኞ አጥቢያ ላይ ጥቃቶች ተፈጽመዋል። በተለይ በባሌ እና አርሲ አካባቢዎች ብሔር እና ሐይማኖትን መሠረት ያደረጉ ጥቃቶች በንጹሃን ዜጎች ላይ ተፈጽመዋል። በዚህም በርካቶች ተገድለዋል። የንብረት ውድመትም አጋጥሟል።

የተለያዩ ሰዎች የሃዘን መልዕክት

የሃጫሉን ሞት ተከትሎ ከማክሰኞ ሰኔ 23 ጀምሮ የተለያዩ ሰዎች ሃዘናቸውን መግለጽ ጀመሩ። ጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ አሕመድ በድምጻዊው ሞት የተሰማቸውን ሀዘን "ውድ ህይወት አጥተናል" ካሉ በኋላ "የዚህ ድንቅና አንፀባራቂ ወጣት አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ህይወት መቀጠፍ ከተሰማ ጀምሮ በከባድ ሃዘን ውስጥ ለምንገኝ ሁሉ መፅናናትን እመኛለሁም" በማለት ሃዘናቸውን ገልጸዋል።

የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ሕግ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በድምጻዊው ግድያ ከባድ ሐዘን እንደተሰማቸው ገልጸው "ሃጫሉን የገደለው ማንም ይሁን ማን ከህግ ማምለጥ አይችልም" ሲሉ ተናግረው ነበር።

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማ፣ የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ እና ሌሎች የመንግሥት ባለስልጣናትም የተሰማቸውን ጥልቅ ሃዘን ገልጸዋል።

የአስክሬን ሽኝት

የአርቲስቱን አስክሬን ለማጀብና ለመሸኘት በሺህዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ከአዲስ አበባ ዙሪያ ወደ መዲናዋ መትመም የጀመሩት ከሰኔ 23 ንጋት በፊት ነበር።

ብዙም ሳይቆይ የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስክሬን ግብዓተ መሬት መፈጸም ባለበት ስፍራ ላይ አለመግባባቶች ተፈጠሩ።

የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝደንት ሽመልስ አብዲሳ እና የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ኢ/ር ታከለ ኡማን ጨምሮ የመንግሥት ባለስልጣናት የአርቲስቱ ቤተሰቦች ቀብሩ እንዲፈጸም የሚፈልጉት በአምቦ ነው ብለው ነበር።

የሃጫሉ ወንድም ሃብታሙ ሁንዴሳ፤ "ቤተሰብ ሃጫሉ እንዲቀበር የሚፈልገው በአምቦ ከተማ ውስጥ ነው" ሲል በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግሯል።

የአርቲስት ሃጫሉ አስክሬን ከጰውሎስ ሆስፒታል ወደ አምቦ እያመራ ቡራዩ ከደረሰ በኋላ፣ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በአዲስ አበባ ነው መፈጸም ያለበት በሚል ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ ተደርጎ ለተወሰኑ ሰዓታት በኦሮሞ ባህል ማዕከል ውስጥ ቆይቶ ነበር።

ከዚያም አስክሬኑ አዲስ አበባ ስታዲም አቅራቢያ ከሚገኘው የኦሮሞ ባህል ማዕከል በሄሊኮፕተር ተጭኖ ከአምቦ ከተማ በቅርብ ርቀት ወደ ሚገኘው ሆሚቾ አሙኔሽን ኢንጂነሪንግ ኢንዱስትሪ ተወሰደ።

ጃዋር መሃመድ

የፎቶው ባለመብት, AFP

የእነ ጃዋር መሐመድ እስርና የተርኔት መቋረጥ

ማክሰኞ ሰኔ 23 ጃዋር መሐመድ እና በቀለ ገርባን ጨምሮ 35 ሰዎች በቁጥጥር እንዲውሉ መደረጉን የፌደራል ፖሊስና የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሸን በጋራ በሰጡት መግለጫ ይፋ አደረጉ።

በወቅቱ እነ ጃዋር ላይ ከቀረበው ክስ መካከል "በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን የአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ አስከሬን ወደ አምቦ እንዳይሄድ አድርጓል" የሚለው ይገኘበታል።

የኦሮሚያ ፖሊስ ኮሚሽን ኮሚሽነር አራርሳ መርዳሳ በበኩላቸው "በጃዋር መሐመድ የሚመራው ቡድን አስክሬኑ በቤተሰቡ ጥያቄ መሰረት ከጳውሎስ ሆስፒታል ወጥቶ ወደ አምቦ እየተሸኘ ሳለ፤ ከቤተሰቡ ፍቃድ ውጪ ቡራዩ ሲደርስ ወደ አዲስ አበባ እንዲመለስ አደርጓል" ብለው ነበር።

የኢትንተርኔት አገልገሎት በመላው አገሪቱ ለሦስት ሳምንታት ያህል የተቋረጠው በአርቲስቱ ግድያ ማግስት ማክሰኞ ሰኔ 23 ጀምሮ ነበር።

በቅድሚያ የሞባይል ዳታ ከዚያም ብሮድባንድ ኢንተርኔት አገልግሎት መቋረጡን በወቅቱ ተጠቃሚዎች ለቢቢሲ ተናግረው ነበር።

ግድያ በአምቦ

ሰኔ 24 የሃጫሉ አስክሬን አምቦ በደረሰበት ዕለት የቀብር ሥነ ሥርዓቱ ከሚፈጸምበት ቦታ ጋር ተያይዞ በተከሰቱ ግጭቶች የሃጫሉን አጎት ጨምሮ 5 ሰዎች ተገደሉ።

ከሃጫሉ አጎት በተጨማሪ ሦስት የቤተሰብ አባላት በጥይት ተመትተው የተለያየ ጉዳት እንደደረሰባቸው የሃጫሉ ወንድም ሃብታሙ ሁንዴሳ ለቢቢሲ ተናግሯል።

ቀብር

የፎቶው ባለመብት, ETV

የሃጫሉ የቀብር ሥነ ሥርዓት

ሰኔ 25 የድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ የቀብር ሥነ ሥርዓት በአምቦ ከተማ በሚገኘው የገዳመ ኢየሱስ ቤተ ክርስቲያን ውስጥ ተፈጸመ።

በአምቦ ዩኒቨርሲቲ ስታዲየም በተካሄደው የሽኝት ፕሮግራምም ሆነ የቀብር ሥነ ሥርዓቱ በተፈጸመበት ቤተ-ክርስቲያን በደኅንነት ስጋት ምክንያት የተገኘው ሰው ቁጥር ዝቅተኛ ነበር።

የአርቲስት ሃጫሉ የቅርብ ጓደኞች እና የቤተሰብ አባላት ሳይቀሩ በቀብር ሥነ ሥርዓቱ ላይ መገኘት ባለመቻላቸው ሥርዓቱን በኦቢኤን ቴሌቪዥን ለመከታተል ተገደለዋል።

ለቀብር ከአምቦ ዙሪያ የሚመጡ ሰዎች ወደ ከተማው እንዳይገቡም ተከልክለው ነበር። የመንግሥት የጸጥታ ኃይል ሃዘንተኞች ወደ ከተማው እንዳይገቡ እና ወደ መጡበት እንዲመለሱ ለማድረግ አስለቃሽ ጭስ ሲተኩስ ነበር ሲሉ አንዳንድ የከተማው ነዋሪዎች በወቅቱ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በሃጫሉ ግድያ የተጠረጠሩ

ሐምሌ 3 ላይ ጠቅላይ አቃቤ ዐቃቤ ሕግ ወይዘሮ አዳነች አቤቤ፣ በድምጻዊ ሃጫሉ ሁንዴሳ ግድያ ቀጥተኛ ተሳታፊ ናቸው ብለው በስም የጠቀሷቸው ሦስት ግለሰቦችን ይፋ አደረጉ።

እነዚህ ግለሰቦች ጥላሁን ያሚ፣ አብዲ አለማየሁና ከበደ ገመቹ የሚባሉ ሲሆኑ በወቅቱ እንደተገለፀው፤ ሃጫሉ ሁንዴሳን በጥይት ተኩሶ በመግደል የተጠረጠረው ጥላሁን ያሚ የተባለው ግለሰብ ነው።

ጨምረውም ሦስቱ ግለሰቦች የግድያውን ተልዕኮ ኦነግ-ሸኔ ከተባለው ቡድን ተቀብለው ማስፈጸማቸውን በመግለጽ፤ ቡድኑ ከግድያው ጀርባ እጁ እንዳለበት ዐቃቤ ሕጓ ተናግረዋል።

ሐምሌ 1 በአሜሪካው ሴንት ፖል ሚኒሶታ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ

የፎቶው ባለመብት, Brandon Bell

የምስሉ መግለጫ, ሐምሌ 1 በአሜሪካው ሴንት ፖል ሚኒሶታ በተደረገው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ

በዲያስፖራው መካከል ልዩነት መፈጠር

የአርቲስት ሃጫሉን ግድያ ተከትሎ የተቃውሞ ሰልፎች የታዩት በአገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን፤ በአሜሪካ፣ አውሮፓ፣ በመካከለኛው ምሥራቅ እና አውስትራሊያም ጭምር ነበር።

የጠቅላይ ሚንስትር ዐብይ መንግሥትን የሚቃወም እና ለአርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ፍትህ የሚጠይቁ ሰልፎች ተካሂደዋል። በሌላ በኩል ለጠቅላይ ሚንሰትሩ ድጋፋቸውን የሚገልጹ እና የሃጫሉን ግድያና ተከትለው የተፈጸሙ ጥቃቶችን የሚያወግዙ ሰልፈኞችም በተለያዩ የውጪ አገራት ከተሞች ታይተዋል።

አርቲስት ሃጫሉ ለህዝብ ጆሮ ያልደረሱ ከ7 ያላነሱ የሙዚቃ ስራዎች አሉት
የምስሉ መግለጫ, አርቲስት ሃጫሉ ለህዝብ ጆሮ ያልደረሱ ከ7 ያላነሱ የሙዚቃ ስራዎች አሉት

"ልጄ ጀግና ነው። ለእውነት ይሞታል"

አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ ልጃቸውን ሲያስታውሱ "ልጄ ጀግና ነው። ለእውነት ይሞታል" ይላሉ።

"ሃጫሉ ከልጅነቱ ጀምሮ ጀግና እና ደፋር ነበረ። ውሸት አይወድም። እውነት ነው የሚወደው፤ የሚሞተውም ለእውነት ነው" የሚሉት የሃጫሉ ወላጅ አባት አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ፤ ሃጫሉ ለሞት የተዳረገው ለወገኑ በመቆርቆሩ እና "ያገባኛል" በማለቱ ነው ሲሉ ተናግረዋል።

"እኔ የሚያበሳጨኝ ነገር ሃጫሉ እንደእሱ ጀግና በሆነ ሰው ሳይሆን በገንዘብ በተገዙ ፈሪዎች መንገድ ላይ መቅረቱ ነው" ሲሉም ያክላሉ።

የሃጫሉ አባት አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ
የምስሉ መግለጫ, የሃጫሉ አባት አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ

ሃጫሉ ማን ነበር?

ሃጫሉ ሁንዴሳ ተወልዶ ያደገው ከአዲስ አበባ በስተምዕራብ አንድ መቶ ኪሎ ሜትሮች ርቃ በምተገኘው አምቦ ከተማ ውስጥ ነው።

እናቱ ወይዘሮ ጉደቱ ሆራ፣ ሃጫሉ ከልጅነቱ ታሪክን መስማትና የመንገርና ዝንባሌውንና ችሎታውን ጠንቅቀው ተረድተውት ስለነበር ከመጀመሪያው አንስቶ ያበረታቱት እንደነበር በተደጋጋሚ ሃጫሉ ያስታውሳል።

አባቱ አቶ ሁንዴሳ ቦንሳ ደግሞ ልጃቸው ሃጫሉ በትምህርቱ ዓለም ገፍቶ ዶክተር ወይም የዩኒቨርሲቲ መምህር እንዲሆንላቸው ከፍተኛ ፍላጎት ነበራቸው።

ሃጫሉ ግን ገና ከልጅነቱ ጀምሮ በፍቅሯ ለወደቀላት ሙዚቃ ነበር መላው ትኩረቱ።

ሃጫሉ የሁለተኛ ደረጃ ተማሪ ሳለ በ1995 ዓ.ም የ17 ዓመት ታዳጊ እንዳለ ታስሮ ለአምስት ዓመታት በተለምዶ "ከርቸሌ" ተብሎ በሚጠራው አምቦ በሚገኘው እስር ቤት አሳልፏል።

ሃጫሉ ሁንዴሳ ከባለቤቱ ፋንቱ ደምሰው ጋር፤ በትዳር ከመጣመራቸው በፊት ለበርካታ ዓመታት በፍቅር ጓደኝነት አብረው ቆይተዋል

የፎቶው ባለመብት, Family

የምስሉ መግለጫ, ሃጫሉ እና ፋንቱ በትዳር ከመጣመራቸው በፊት ለበርካታ ዓመታት በፍቅር ጓደኝነት አብረው ቆይተዋል

መታሰሩ በይበልጥ በሰዎች ላይ የሚደርሰውን ግፍ እና ጭቆና እንዲገባው ማድረጉን በአንድ ወቅት ተናግሮ ነበር።

የሙዚቃ ግጥሞችን ዜማዎችን መጻፍ የጀመረውም በእስር ላይ እያለ ነበር። ከአምስት ዓመታት በኋላ ሲለቀቅ የደረሰበትን በደል ለመቃወምና ለሚሊየኖች ድምጽ ለመሆን ወስኖ እንደወጣ ይናገራል፤ ሃጫሉ።

በአጭር ጊዜም በኦሮምኛ ተናጋሪው ሕዝብ ዘንድ ብቻ ሳይሆን በመላዋ አገሪቱ ተወዳጅ የሆነለትን 'ሳኚ ሞቲ' የተሰኘውን አልበሙን አቀረበ። የዚህ የሙዚቃ ስብስብ አብዛኛዎቹ ግጥሞችና ዜማዎች ሃጫሉ በእስር ላይ እያለ የሰራቸው እንደነበሩ ይነገራል።

የ36 ዓመቱ ሃጫሉ የሦስት ልጆች አባት ነበር።

የሃጫሉ ለዝብ ጆሮ ያልደረሱ የሙዚቃ ራዎች

አርቲስት ሃጫሉ ሁንዴሳ ለሕዝብ ጆሮ ያልደረሱ ከ7 ያላነሱ የሙዚቃ ሥራዎች በተለያዩ ስቱዲዮች ውስጥ እንደሚገኙ ከቅርብ ጓደኞቹ ሰምተናል።

የቤተሰብ አባላት እና ጓደኞቹ ከሚመለከታቸው ጋር ተወያየተው በአልበም መልክ ለአድናቂዎቹ ለማቅረብ ሃሳብ እንዳላቸውም ቢቢሲ መረዳት ችሏል።