በቤኒሻንጉል ጉሙዝ 14 ሰዎችን የገደሉ ታጣቂዎች አየተፈለጉ ነው

የኢትዮጵያ ካርታ

ሐምሌ 20/2012 በቤኒሻንጉ ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን ጉባ ወረዳ የታጠቁ ኃይሎች በፈጸሙት ጥቃት የ14 ሰዎች ህይወት ሲያልፍ በርካቶች መቁሰላቸው ታውቋል።

ሰኞ ማታ 2 ሰዓት ገደማ በጉባ ወረዳ አቡጃር ቀበሌ ላይ ታጣቂዎች በተፈጸመው ጥቃት 14 ሰዎች መገደላቸውን እነሱም "የአማራ ተወላጆች ሲሆኑ ብዙዎቹም ከሰከላ አካባቢ የሄዱ ናቸው" ሲሉ የአማራ ክልል የመንግሥት ኮሙዩኒኬሽን ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ግዛቸው ሙሉነህ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ህይወታቸው ካለፈው ሰዎች በተጨማሪ ስድስት ሰዎች መቁሰላቸውን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።

"የታጠቀ የሽፍታ ቡድን ነው ጥቃቱን ያደረሰው። . . . በተቃደ መንገድ ነው የተገደሉት" በማለት ጥቃቱ የታሰበበትና "የብሔር ግጭት ለማስነሳት" ታስቦ የተፈጸመ እንደሆነም ተናግረዋል።

ከጥቃቱ ፈጻሚዎች መካከል አንዳንዶቹ ከመከላከያ ሠራዊት ጋር ጭምር ተኩስ መግጠማቸውን የጠቆሙት አቶ ግዛቸው፤ ገዳዮቹ ሳይያዙ ጫካ መግባተቻውን አስታውቀዋል።

"አካባቢው ጫካ የበዛበት አካባቢ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ለመያዝ ትንሽ የሚያስቸግር ሁኔታ አለ" በማለት ጥቃት ፈጻሚዎቹን ለመያዝ ጥረት እየተደረገ መሆኑን አመልክተዋል።

ከጥቃቱ በኋላ የመከላከያ ሠራዊት ወደ አካባቢው መሰማራቱን አቶ ግዛቸው ጠቁመው፣ የቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መንግሥትም አስፈላጊውን ሥራ እያከናወነ በመሆኑ አሁን ላይ ስፍራው ከሞላ ጎደል ሠላም እየሆነ ነው ብለዋል።

የአማራ እና የቤንሻንጉል ጉሙዝ የክልላዊ መንግሥታት ከአሁን ቀደም የነበሩ መፈናቀሎችን በውይይት እና በመመካከከር "የአማራ ከልል ዋጋ ጭምር እየከፈለ የተፈናቀሉትን መልሰን እያቋቋምን ሠላም እና መረጋጋት በአካባቢው ነበር" ብለዋል።

የአማራ መገናኛ ብዙህን ድርጅት በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልል መተከል ዞን የጉባ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አሕመድ ኩምሳሪን ጠቅሶ እንደዘገበው ጥቃት የፈጸሙት የታጠቁ ሽፍቶች ናቸው።

በጥቃቱም የ14 ሰዎች ሕይወት ማለፉንም አረጋግጠዋል፤ የቆሰሉት ከስድስት በላይ ሰዎችም ወደ ፓዌ ሆስፒታል ለሕክምና እንደተወሰዱም ዋና አስተዳዳሪው አረጋግጠዋል።

ሽፍቶቹን ለመያዝም የክልሉ ፀረ ሽምቅ ኃይል ክትትል እያደረገ መሆኑን አስተዳዳሪው ጨምረው አስረድረተዋል። ሽፍቶቹ ከዚህ ቀደምም መኖሪያቸውን ጫካ ውስጥ በማድረግ ሚሊሻ እና የአካባቢ ሽማግሌዎችን ሲያፍኑ፣ ሲያንገላቱ እና መሣሪያም ሲነጥቁ የነበሩና በፀጥታ ኃይሎች የሚፈለጉ መሆናቸውን አቶ አሕመድ አስታውቀዋል፡፡

ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የአካባቢው ነዋሪ እንደተናገሩት "ወደ 100 የሚጠጉ እና ከሁለት ቀበሌ የተወጣጡ ናቸው" ጥቃቱን የፈጸሙት ይላሉ።

ግለሰቡ እንደሚሉት ከክልል የመጡ ኃላፊዎች ወደ ቦታው ቢያቀኑም ጥቃት አድራሾቹ ከቦታ ቦታ ስለሚንቀሳቀሱ ማግኘት አልተቻለም ብለዋል።

በጥቃቱ ከሞቱት ሰዎች መካከል በትላንትናው እለት ብር ተዋጥቶ የ11ዱ አስከሬን ወደ ሰከላ መሸኘቱንም ግለሰቡ ለቢቢሲ ተናግረው፤ የመቁሰል ጉዳት የደረሰባቸው ሰዎች ደግሞ የህክምና ክትትል እየተደረገላቸው መሆኑን እንደሰሙ ገልፈዋል።

ከጉባ ከተማ 54 ኪሎ ሜትር አካባቢ ርቆ በሚገኝ ቦታ ደረሰ በተባለው ጥቃት ምክንያት ከ50 በላይ የሚሆኑ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማው መግባታቸውም ተሰምቷል።

ግለሰቡ ጨምረውም ጫካ ውስጥ አድረው በእግር የሚጓዙ ሰዎች መኖራቸውን ጠቅሰው በዚህም የተፈናቃዮች ቁጥር ሊጨምር ይችላል ብለዋል።

ሕዝቡ ለተፈናቃዮች ከሚያደርገው ድጋፍ በተጨማሪ የክልሉ መንግስትም 30 ኩንታል ስንዴ መስጠቱን ነግረውናል።

"ጥቃት አድራሾቹ ከነገ ዛሬ ይመጣሉ እየተባለ ሰዉ ስጋት አለበት እንጂ እስካሁን ሠላም ነው" ያሉት ነዋሪው በጉባ ከተማ የተወሰኑ የመከላከያ ሠራዊት አባላት መግባታቸውንም ጠቁመዋል።

በአካባቢው ከአንድ ዓመት በፊት የዘጠኝ ሰዎች ህይወት በበተመሳሳይ ጥቃት ካለፈ በኋላ፤ የአሁኑ ጥቃት ሲደርስ ለአራተኛ ጊዜ እንደሆነ አስታውቀሰዋል።

የህዳሴው ግድብ ከከተማው 42 ኪሎ ሜትር ብቻ የሚርቅ መሆኑን ጠቁመው መከላከያ ሠራዊት ወደ ቦታው ገብቶ ሊቆጣጠር ይገባል ብለዋል። "በቁጥጥር ስር የማይውሉ ከሆነ ለወደፊትም አስቸጋሪ ነው" ሲሉ ስጋታቸውን ገልፈዋል።

ከአማራ ክልል ውጭ ስለሚገኙ የክልሉ ተወላጆች የተጠየቁት አቶ ግዛቸው "ከ11 ሚሊዮን በላይ የአማራ ተወላጅ ከክልሉ ውጪ እንደሚኖሩ ይታመናል" ያሉ ሲሆን አብዛኛዎቹ በሚኖሩበት አካባቢ ለዘመናት ከመኖር ባለፈ በትዳር ጭምር ተሳስረው እንደሚኖሩ ጠቅሰዋል።

ከእነዚህ ዜጎች ደኅንነት ጋር በተያያዘ "ዋናውን ኃላፊነት የሚወስዱት የክልል መንግሥታት ናቸው" ያሉት ዳይሬክተሩ ችግር ሲገጥም ከሚለከታቸው ክልሎች ቀድመን "ልንደርስ" አንችለም ብለዋል።

ሌሎቹ ክልሎች ኃላፊነት ያለባቸው ቢሆንም "የአማራ ክልል ግን ዝም ይላል ማለት አይደለም" ያሉት አቶ ግዛቸው "በኦሮሚያም ሆነ በቤኔሻንጉል እንዲሁም በሌላ ቦታ ያሉ የአማራ ተወላጆች ችግር እንዳይደርስባቸው ከክልል እና ከፌደራል መንግሥት ጋር በጋራ እተሰራ ነው" ብለዋል።

ስለጥቃቱና አሁን ስላለው ሁኔታ ከቤንሻንጉል ጉምዝ ክልል በኩል ማብራሪያ ለማግኘት ከትናንት ጀምሮ ያደረግነው ተደጋጋሚ ጥረት አልተሳካም።

ከሁለት ወራት በፊት የአማራ ክልል አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትናና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ኮሚሽን ከ81 ሺህ በላይ ተፈናቃዮች ወደ ቀያቸው መመለሳቸውን አስታውቆ ነበር።

በወቅቱ ኮሚሽነሩ አቶ ዘለዓለም ልጃለም "ከቤንሻንጉል ክልል ተፈናቅለው ያልተመለሱ 49720 ዜጎች አሉ። ከክልሉ መንግሥት ጋር በተደረገ ውይይት ሙሉ ለሙሉ ለመመለስ ፍላጎት አለ። ቻግኒ አካባቢ የነበሩ እና 4 ሺህ የሚያህሉ ሰዎች ተመልሰዋል። ክልሉ ሁኔታዎችን አመቻችቶ ለመመለስ እየሰራ ነው። በሚመጡት ጥቂት ቀናት ቀሪዎቹ እንዲመለሱ እየተሠራ ነው" ማለታቸው ይታወሳል።