ዶናልድ ትራምፕ የወባ መድኃኒት ለኮሮናቫይረስ ፈውስ ነው አሉ

ዶናልድ ትራምፕ

የፎቶው ባለመብት, EPA

የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃይድሮክሲሎሮኩዊን ፍቱን መድኃኒት ነው ሲሉ በድጋሚ ተናገሩ።

ይህ የወባ መድኃኒት ለኮሮናቫይረስ ታማሚዎች ፈውስ እንደማይሰጥ የዓለም ጤና ድርጅትም ሆነ የእርሳቸው የጤና አማካሪዎች በተደጋጋሚ የመሰከሩ ቢሆንም ትራምፕ ግን ወይ ፍንክች በማለት በአቋማቸው ጸንተዋል።

እንዲያውም "ሃይድሮክሲክሎሮኩዊን እያጣጣላችሁት ያላችሁት እኔ ጥሩ ነው ስላልኩ ነው" ብለዋል በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ።

ትዊተር የዶናልድ ትራምፕ ልጅ ከዚሁ ጋር የተያያዘ ይዘት ያለው አሳሳች ተንቀሳቃሽ ምስልን አጋርቷል በሚል ሰሌዳውን አጥፍቶበት ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ይህን አወዛጋቢ አስተያየት የሰጡት የልጃቸው የትዊተር ሰሌዳ ለጊዜው እንዲዘጋ መደረጉን ተከትሎ ነው።

በጤና ባለሞያዎች ዘንድ ሀይድሮክሲክሎሪን ኮቪድ-19ን ይዋጋል የሚል አስተማማኝ ማስረጃ እስካሁን አልተገኘም። ከዚያ ይልቅ እንዲያውም መድኃኒቱ ለልብ ህመም ስለሚዳርግ ጥንቃቄ አድርጉ የሚሉ መረጃዎች ናቸው ተጠናክረው እየወጡ ያሉት።

ለምሳሌ ባለፉት ወራት የአሜሪካ የምግብና መድኃኒት ቁጥጥር ባለሥልጣን ባወጣው ማስጠንቀቂያ ይህ የወባ መድኃኒት ለአደገኛ የልብ ህመም ስለሚዳርግ አስፈላጊው ጥንቃቄ እንዲደረግ ትዕዛዝ ሰጥቶ ነበር።

ዶናልድ ትራምፕ ይህን መግለጫ በሚሰጡበት ሰዓት በበሽታው የሚሞቱ ዜጎች ቁጥር አሻቅቦ ታይቷል። በ24 ሰዓት ብቻ 1ሺህ 600 ሰዎች በመላው አሜሪካ መሞታቸው በወራት ውስጥ ያልተሰማ ክፉ ዜና ነው።

ይህን ተከትሎ መድኃኒት ከተገኘ በሚል ካሜራ በመፈብረክ የሚታወቀው ኮዳክ ኩባንያ ወደ መድኃኒት ምርት የገባ ሲሆን ከመንግሥት 765 ሚሊዮን ዶላር ብድር አግኝቷል። ይህ በካሜራ ማምረት ሥራ ለዘመናት የቆየው ኮዳክ ኩባንያ ለቫይረሱ አዲስ መድኃኒት ሲገኝ ያንን ቶሎ አምርቶ ለገበያ ለማቅረብ ነው ዝግጅት እያደረገ ያለው።

ሀይድሮክሲክሎሮኩዊንን ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ላይ ዝናና እውቅና እንዲያገኝ ያደረጉት የ74 ዓመቱ ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሲሆኑ ይህም በመጋቢት ወር ነበር የሆነው። ያን ከተናገሩ ከሁለት ወራት በኋላ ደግሞ ትራምፕ መድኃኒቱን ራሳቸው እየወሰዱት እንደሆነ በመናገር የጋዜጠኞችን አፍ አስከፍተዋል።

አሁን ደግሞ ዶናልድ ትራምፕ በዚህ መድኃኒት ዙርያ እጅግ ጥልቅ ንባብ ስለማድረጋቸውና መድኃኒቱ በሽታውን እንደሚፈውስ እንደደረሱበት ያለ ምንም ሀፍረት አብራርተዋል።

"ይህን መድኃኒት ብትወስዱት ምንም አትጎዱም። እኔ አንድ ነገር ጥሩ ነው ስል ሁላችሁም በተቃራኒው ስለምትቆሙ ነው እንጂ መድኃኒቱ ፍቱን ነው" ብለዋል።

ትራምፕ ሰኞ ማታ 'አሜሪካ ፍሮንትላይን ዶክተርስ' የሚባል አንድ የሐኪሞች ቡድን ስለ ሀይድሮክሲክሎሮኩዊን የተናገረውን ቪዲዮ አጋርተው መነጋገሪያ ሆነው ቆይተዋል።

ፌስቡክም ሆነ ትዊተር ግን ፕሬዝዳንቱ ያጋሩትን ቪዲዮ ከሰሌዳቸው አንስቶባቸዋል። ምክንያቱ ደግሞ ሐሰተኛ መረጃ ነው በሚል ነው። ሆኖም ፌስቡክና ትዊተር እርምጃውን ከመውሰዳቸው በፊት ቪዲዮዉን 17 ሚሊዮን ሰዎች ተመልክተውታል።

ትዊተር እንዲያውም ይህንኑ ቪዲዮ የፕሬዝዳንቱ የበኩር ልጅ በማጋራቱ ልጁን ለ12 ሰዓታት ከትዊተር አግዶ አቆይቶታል።

በዚህ ቪዲዮ ላይ የምትታየው ዶ/ር ስቴላ ኢማኑኤል የተባለች ሴት በርካታ ስሜት የማይሰጡ ንግግሮችን ከተናገረች በኋላ ሀይድሮክሲክሎሮኩዊንን በመጠቀም 350 ሰዎችን እንደፈወሰች ስትናገር ትታያለች።

ዶናልድ ትራምፕ በምሽቱ መግለጫቸው ይህቺን ሴት ዶክተር መድኃኒቱን በማድነቋ እጅግ አድርገው አሞካሽተዋታል።

ትራምፕ ሰኞ ዕለት ከከፍተኛ የጤና አማካሪያቸው ከዶ/ር አንተኒ ፋውቺ አቋም የሚጻረሩ በርካታ አስተያየቶችን የሰጡ ሲሆን ጋዜጠኞች ይህን ተከትሎ ከዶ/ር ፋውቺ ጋር ቅያሜ ይኖራቸው እንደሁ ፕሬዝዳንቱን ጠይቀዋቸዋል።

ትራምፕ በሰጡት ምላሽ ከዶ/ር አንተኒ ፋውቺ ጋር በተደጋጋሚ የሐሳብ ልዩነት እንደሚያሳዩ አልካዱም። ሆኖም ግን ይህ ተፈጥሯዊ ነው ብለዋል።

"ቫይረሱ የተቀሰቀሰ ሰሞን እኔ ድንበራችንን ለቻይና እንዝጋ ስል ዶ/ር ፋውቺ ተቃውሞኝ ነበር። አሁን ያን ውሳኔ በመወሰኔ ዶ/ር ፋውቺ ያደንቀኛል። . . . እርሱ በአሜሪካዊያን ዘንድ ከፍተኛ ተቀባይነት አለው፤ ያ ለእኔና እኔ ለምመራው አስተዳደር መጥፎ ነገር አይደለም" ብለዋል ትራምፕ።

ዝነኛው የጸረ ተላላፊ በሽታዎች ጠቢብ ዶ/ር ፋውቺ ዶናልድ ትራምፕ ስለሚያሞካሹት ሀይድሮክሲክሎሮኩዊን መድኃኒት ከዚህ ቀደም በኤቢሲ ቴሌቪዥን ተጠይቀው መድኃኒቱ ለኮሮናቫይረስ ምንም እርባና እንደሌለው በማያሻማ ሁኔታ ተናግረዋል።

ትራምፕ ስለምን ዶ/ር ፋውቺና ሌሎች አማካሪዎቻቸው በአሜሪካዊያን ዘንድ ከርሳቸው ይልቅ ተቀባይነት እንዳላቸው ተጠይቀው ነበር።

ትራምፕ ሲመልሱ "ባህሪዬ ሊሆን ይችላል" ብለዋል።

አሜሪካ በአሁኑ ሰዓት 4.3 ሚሊዮን ሰዎች በቫይረሱ ተይዘውባል። የሟቾች ቁጥርም መቶ ሺህ ተኩል አልፏል።

ኮሮና
Banner