አሜሪካ ሲንጋፖራዊው ተማሪ የቻይና ሰላይ እንደሆነ እንዴት ደረሰችበት?

የፎቶው ባለመብት, DICKSON YEO/FACEBOOK
ጁን ዊ ዩ ተወዳጅ ተማሪ ነበር። ጎበዝ የፒኤች ዲ ተማሪ። ትምህርቱን ይከታተል የነበረው ሲንጋፖር ውስጥ ነበር። እርሱም ዜግነቱ የሲንጋፖር ነው።
እንዴት ሕይወቱ አቅጣጫ ቀይሮ ራሱን የቻይና ሰላይ ሆኖ እንዳገኘው ለእራሱም ይገርመዋል።
የሆነ ቀን ይፋ ትምህርታዊ ገለጻ (ሌክቸር) ሰጥቶ ሲጨርስ ከታዳሚዎቹ መካከል የሆኑ ሰዎች መጥተው ተዋወቁት።
"ድንቅ ነበር 'ሌክቸርህ'" ሲሉ እንትፍ እንትፍ አሉበት።
"ለምን ቤይጂንግ መጥተህ ጥናትህን አታቀርብም?" ሲሉም ጋበዙት። ደስም አለው። ከሲንጋፖር ቤጂንግ በረረ።
ጁን ዊ ሦስተኛ ዲግሪውን ይሰራ የነበረው በቻይና የውጭ ጉዳይ ፖሊሲና ተያያዥ ርዕሰ ጉዳዮች ላይ ነበረ።
የቤይጂንግ ገለጻውን አቅርቦ ሲጨርስ ደግሞ ሌሎች ሁለት ሰዎች መጡና ተዋወቁት።
"ገለጻህ ማለፍያ ነው! በዚያ ላይ ብሩህ ጭንቅላት ነው ያለህ!" አሉት።
". . . እኛ የምንሰራው ቻይና ውስጥ ለሚገኝ አንድ የምርምርና የጥናት ቡድን (ቲንክ ታንክ) ነው፤ አብረን ብንሠራ ደስ ይለናል. . . ."
አላቅማማም።
መጀመሪያ ከዚያው ከሲንጋፖር ሆኖ አካዳሚያዊ ወረቀቶችን ይልክላቸው ጀመር። ቀስ በቀስ ለምን ከአሜሪካ ሆነህ ትንንሽ መረጃዎችን አታቀብለንም፤ እኛ ደግሞ ትልልቅ ክፍያ እናስብልሃለን አሉት።
የተወሰነ ጊዜ እንደሰራላቸው ሰዎቹ በትክክል ማን እንደሆኑ ተረዳ፤ ጁን ዊ የቻይና የደኅንነት ሰዎች መረብ ውስጥ ነበር ሰተት ብሎ የገባው።
ብዙም አልከፋውም። አብሯቸው መሥራት ቀጠለ። መጀመሪያ ከደቡብ ምሥራቅ እሲያ አገሮች የሚያገኘውን መረጃ ይልክላቸው ነበር። ቀጥሎ ግን "በአሜሪካ ዙሪያ ብቻ እንድታተኩር እንፈልጋለን" አሉት።
ከዕለታት አንድ ቀን ሲንጋፖራዊው ወጣት የለየለት የቻይና ሰላይ ሆኖ ራሱን አገኘው። ስለላ ደግሞ የኋላ ማርሽ አያውቅም። ሥራውን ገፋበት።
መረጃ የሚያቀብሉትን ሰዎች ያጠምዳቸው የነበረው ታዲያ ሊንክዲን (Linkdin) በተሰኘው የሙያና የሥራ መተሳሰሪያ ድራምባ ነበር። አንዴት?
ሊንክድኢንን (LinkdIn) ለስለላ?
የጁን ዊ ሌላኛው ስሙ ዲከንስ ይባላል። ሐሰተኛ የአማካሪ ኩባንያ ስም በማውጣት ሰዎችን ያማልል ነበር። አምስት ዓመታት በዚህ መንገድ ከሰራ በኋላ ነው ባለፈው አርብ አሜሪካና ቻይና ግንኙነታቸው በሻከረ ማግስት በቁጥጥር ሥር የዋለው።
እርሱ በተማረበት የሲንጋፖር ሊ ኩዋን ዪ ዩኒቨርስቲ የሚማሩ የነበሩ ጓደኞቹ ዜናውን ሲሰሙ ማመን ነው ያቃታቸው።
ይህ የሲንጋፖር ዩኒቨርስቲ በፐብሊክ ፖሊሲ ዘርፍ እውቅ ነው። በእሲያ አህጉር በርካታ የመንግሥት ባለሥልጣናትና ፖሊሲ አውጪዎችን ያስመረቀ ነው።
"በጣም ንቁ ተማሪ ነበር። እንዴት ያለ ድንቅ ልጅ! ይገርማል" ስትል ለቢቢሲ አስተያየቷን የሰጠች፣ ስሟን መጥቀስ ያልወደደች አንድ አብራው የተማረች ሴት፤ የሊን ስም በበጎ ብቻ እንደምታስታውስ ገልጻለች።
". . . ብዙውን ጊዜ እርሱ ስለ እኩልነት ነበር የሚያወራው፣ በልጅነቱ ቤተሰቡ እርሱን ለማሳደግ ያዩትን ፍዳ ይነግረን ነበር። አሁን ለቻይና ሲሰልል ነበር መባሉ ሊዋጥልኝ አልቻለም" ብላለች።
ሌላ አንድ የዩኒቨርስቲው መምህር ግን ከእርሷ የተለየ ትዝታ ነው ያላቸው። ". . . ልጁ ስለእራሱ ትንሽ የተጋነነ አመለካከት ነበረው።"
ጁን ዊን ለሦስተኛ ዲግሪው ሲያማክሩት የነበሩት ሰው በአካባቢው አገራት ዕውቅ ፕሮፌሰር ናቸው። ኋንግ ጂንግ ይባላሉ። ዩኒቨርስቲው በኋላ ላይ አባሯቸዋል። የተባረሩት ታዲያ አንዲት ስሟ ያልተጠቀሰን የአካባቢውን አገር የውጭ ፖሊሲዋን ለመጠምዘዝ ሞክረዋል በሚል ነበር።
ፕሮፌሰሩ ከዩኒቨርስቲው ከተባረሩ በኋላ ሲንጋፖርን ለቀው ዋሺንግተን ዲሲ ሥራ ጀመሩ። አሁን ቤይጂንግ ገብተዋል። እኚህ ፕሮፌሰር ከተማሪያቸው ጁን ዊ ጋር የስለላ ግንኙነት ነበራቸው የሚል መረጃ ግን እስካሁን አልወጣም።
አሁን የምርመራ ሰነዶች ይፋ እንዳደረጉት ሲንጋፖራዊው ጁን ዊ ከቻይና የደኅንነት መኮንኖች ጋር በተለያዩ የቻይና ከተሞች ለዓመታት ሲገናኝና መረጃ ሲያሾልክ ነበረ።
በአንድ የግንኙነታቸው ወቅት ታዲያ ጁን ዊ በቻይና አለቆቹ ሦስት መረጃዎችን እንዲያቀርብ ተጠየቀ። እነሱም በአርቴፊሻል ኢንተለጀንስ ዙርያ አሜሪካ እየሰራች ስላለው ጉዳይ፣ በአሜሪካ የንግድ ዲፓርትመንትን በተመለከተ ያሉ ነገሮች እንዲሁም አሜሪካ ከቻይና ጋር የንግድ ጦርነት ለማድረግ ያላት ዝግጁነት ምን እንደሚመስል. . .።
ለሰላዩ ጁን ዊ አንዲህ ያሉ መረጃዎችን እንዲቃርም እገዛ ያደረገለት ሊንክዲን (Linkdin) የሙያ ትስስር መድረክ ነው። ሊንክዲን በተመሳሳይ ሙያ ዘርፍ ያሉ ሰዎችን ያስተሳስራል። በዓለም 700 ሚሊዮን ሰዎች በዚህ መንገድ ተጋምደዋል።
በዚህ ዘርፍ ሰዎች ቀድሞ ስለሰሩበት ዘርፍ እንዲሁም መሥሪያ ቤት ይጽፋሉ። ለምሳሌ በርካታ በአሜሪካ መንግሥት የሲቪልና ወታደራዊ ተቋም ውስጥ የሰሩ ሰዎች ይህንኑ ልምዳቸውን በሊንክዲን ገጻቸው ያሰፍራሉ። ይህን የሚያደርጉት ታዲያ የተሻለ ጥቅም የሚያስገኝ ሥራ ካገኘን በሚል ነው።

ይህን ማድረጋቸው ታዲያ እንደ ጁን ዊ ላሉ ለውጪ የሰለላ ተቋማት መኮንኖች መልካም አጋጣሚን ፈጥሯል።
ለምሳሌ የቀድሞው የሲአይኤ መኮንን ኬቪን ማሎሪ ለቻይና መረጃዎችን በማቀበል ተጠርጥሮ 20 ዓመት እስር የተፈረደበት ሰው ነው።
መጀመሪያ የቻይና ሰላዮች ያገኙት ታዲያ በሊንክዲን አማካኝነት ነበር።
ይህ የአሜሪካ ብቻ ራስ ምታት አልሆነም። አንዳንድ የአውሮፓ አገራትም ቢሆኑ ዜጎቻቸው በሰላዮች ኢላማ መደረጋቸውን ደርሰውበታል።
የጀርመን ደኅንነት መሥሪያ ቤት በ2017 ባወጣው አንድ ጥናት የቻይና ሰላዮች 10 ሺህ ጀርመናውያንን ኢላማ ማድረግ የቻሉት ሊንክዲን የሙያ የትስስር መድረክን በመጠቀም ነበር።
ቢቢሲ ሊንክዲን ኩባንያ በጉዳዩ ዙርያ አስተያየት እንዲሰጠው ጠይቆ ምላሽ አላገኘም።
ነገር ግን ከዚህ በፊት ለተመሳሳይ ቅሬታዎች በሰጠው አስተያየት እንዲህ ዓይነት ሕገወጥ አሰራሮችን እንደሚከታተል አስታውቆ ነበር።
ጁን ዊ ኢላማ ያደረጋቸው ሰዎችን በሊንክዲን ካገኛቸው በኋላ መጀመሪያ በሐሰት ከመሰረተው የአማካሪ ኩባንያ ጋር ያፈራርማቸውና ሪፖርት አንዲጽፉለት ያደርጋል። ባለሙያዎቹ የሰሩትን ሪፖርት ካጠናቀረ በኋላ ደግሞ ወደ ቻይና ይልከዋል።
ጥርጣሬ እንዳይፈጥር በሚል የአማካሪ ድርጅቱን ስም የቀዳው አሜሪካ ውስጥ ካለ አንድ ሌላ እውቅ አማካሪ ቡድን ስምና የንግድ ምልክት ላይ ነበር።
በዚህ መንገድ ተታለው ለጁን ዊ ጥናት ከሰሩለት ሰዎች መካከል አንዱ በአሜሪካ አየር ኃይል ውስጥ የኤፍ-35 ጄት አብራሪ የነበረ አሜሪካዊ ነው። ሰውዬው ለፍርድ ቤት እንዳመነው ለቻይናው ሰላይ የጥናት ወረቀት ያቀበለው የገንዘብ ችግር ስለገጠመው ነበር።
ሌላው አሜሪካዊ ፔንታገን ውስጥ የሚሰራ የመረጃ መኮንን ነበር። ቻይናዊው ጁን ዊ ለዚህ ሰው አሜሪካ ከአፍጋኒስታን ጦሯን ብታስወጣ ቻይና ላይ የሚደርሰው የእጅ አዙር ተጽእኖ ምን ሊሆን ይችላል የሚል የጥናት ወረቀት እንዲጽፍ ነበር ያዘዘው። ጥናቱን ሲያጠናቀቅ 2 ሺህ ዶላር ከፍሎታል።
ጁን ዊ አንድ በአገር ደኅንነት አልያም በንግድና ወታደራዊ ደኅንነት ላይ የተሰማራ ሰው በሊንክዲን ሲያገኝ ሊንክዲን በበኩሉ ሌሎች ተያያዥ ልምድ ያላቸው ሰዎችን ስም ዝርዝር ይዘረዝርለታል። ይህ ነበር የጁን ዊን ልፋት ያቀለለው።
ቀድሞ በሊ ኩዋን ዩው ዩኒቨርስቲ ተማሪ የነበረው ዊሊያም ንጉየን አሜሪካዊ ነው። በ2018 በቬትናም ተቃውሞ ላይ ሳለ በቁጥጥር ሥር ውሎ ከአገር ተባሯል። ከዚያ በኋላ ዝነኛ ሆኖ ቆይቷል። ዊሊያም ታዲያ ሰሞኑን በፌስቡክ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው ሰላዩ ጁን ዊ ከዚህ ቀደም በተደጋጋሚ ሊያገኘው ሞክሯል።
ጁን ዊ ለፍርድ ቤት እንዳመነው በ2018 በሐሰት ላቋቋመው የአማካሪ ድርጅቱ ክፍት የሥራ ማስታወቂያ ሲያወጣ 400 ሰዎች ያመለከቱ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 90 ከመቶ የሚሆኑት በአሜሪካ ወታደራዊና የመንግሥት መዋቅር ውስጥ የሠሩ ነበሩ። የእነርሱንም ዝርዝር መረጃ ዊ ለቻይና አሳልፎ ሰጥቷል።
ሰላዩ ጁን ዊ ሰዎች በሊንክዲን በተሻለ ደመወዝ እንዲማልሉ ካደረጋቸው በኋላ የሚሰጡትን መረጃና የሚያጠናቅሩትን ሪፖርት ይመረምራል።
በዚህ ደረጃ የሚሰጡት መረጃና የሚያጠናቅሩለት ሪፖርት አካዳሚያዊ መልክ ነው የሚይዘው። ይህ ግን ለጊዜው ነው። የኋላ ኋላ ከእነርሱ ውስጥ እጅግ ጥቂቶቹ የመንግሥትን ምስጢር እንዲያሾልኩ የማግባባትና የመመልመል ሥራ ይከናወንባቸዋል።
ቻይና ቻይናዊ ያልሆኑ ዜጎችን እየመለመለች ለስለላ ተግባር ስታሰማራ ይህ የጁን ዊ ጉዳይ የመጀመሪያዋ አይደለም።
ሲንጋፖር የበርካታ ማኅበረሰቦች አገር ናት። ወደ 6 ሚሊዮን ሕዝብ አላት። ከእነዚህ ውስጥ ዝርያቸው ከቻይና የሚመዘዙ ጎሳዎች ቁጥራቸው ላቅ ይላል። ሲንጋፖር ከአሜሪካ ጋር ወዳጅ ናት። የአየርና ሌሎች ወታደራዊ ማሪፍያዎች ለአሜሪካ ታቀርባለች።
ሲንጋፖር ከቻይናም ጋር ጠብ የላትም። ከሁለቱ ተቀናቃኝ አገራት ጋር ያላት ግንኙነት ሚዛናዊ መሆኑ ዜጎቿ ለስለላ የተመቹ ሳያደርጋቸው አልቀረም። የሰላዩ ጆን ዊ ጉዳይም ከዚህ የሚመነጭ ነው።
አሁን በቻይናና በአሜሪካ መካከል ያለው ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት እየሻከረ መጥቶ አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል። ይህ የሲንጋፖራዊው ወጣት ሰላይ ጉዳይ ምናልባት ሁለቱን አገራት ሌላ ጡዘት ውስጥ ሊከታቸው እንደሚችል ተሰግቷል።
ሲንጋፖራዊ ሆኖ ለቻይና ሲሰልል የተገኘው ጁን ዊ ፒኤችዲውን የሚሰራበት ዩኒቨርስቲ ከዚህ በኋላ አላውቅህም ብሎታል። ዊ ገና ሦስተኛ ዲግሪውን በማጠናቀቅ ላይ ነበር።
ነገር ግን ጁን ዊ የቻይና ሰላይ አለቆቹ በሚፈልጉት ደረጃ መረጃ አቀብሏቸዋል ማለት አይደለም። በቅርቡ ቻይና ደርሶ ሲመለስ አለቆቹ አንድ አሜሪካው የጦር መኮንን ለስለላ ተግባር እንዲያስፈርመው የቤት ሥራ ተሰጥቶት ነበር።
ይህንን ተልዕኮውን ሊያሳካ ጥቂት እርምጃዎች ሲቀሩት ነበር አሜሪካኖች በቁጥጥር ሥር ያዋሉት።
የ39 ዓመቱ ጁን ዊ በትንሹ አስር ዓመት እስር ይከናነባል ተብሎ ይጠበቃል።















