በሕንድ ሙምባይ የድሃ ሰፈሮች የሚኖሩ ከግማሽ በላይ ነዋሪዎች በኮቪድ-19 ተይዘዋል

ሙምባይ

የፎቶው ባለመብት, BBC Sport

በሕንድ ሙምባይ በድሆች መንደር ውስጥ በሚገኙ ሦስት አካባቢዎች በሚኖሩ ሰዎች ላይ በተደረገ ምርመራ በርካቶች በኮቪድ-19 መያዛቸውን መረጋገጡ ተገለፀ።

በዚሁ አካባቢ በድህነት ከተጎሳቆሉ መንደሮች ውጪ በሚኖሩ ሰዎች መካከል ደግሞ ለቫይረሱ የተጋለጡት 16 በመቶዎቹ ብቻ ናቸው ተብሏል።

ይህ ውጤት የተገኘው ከተወሰደው የ7000 ሰዎች ናሙና መሆኑ ሲገለጽ ቦታዎቹም በጣም ጥግግት ከሚበዛባቸው ሦስት የተለያዩ አካባቢዎች ነው ተብሏል።

በሙምባይ እስከ ትናንት ማክሰኞ ድረስ በኮሮናቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 110 ሺህ ሰዎች ሲሆኑ ከእነዚህም መካከል 6187 ሰዎች ሞተዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ የተሰራው በከተማ አስተዳደሩ እንዲሁም በመንግሥት አማካሪዎች ቡድንና በታታ መሰረታዊ ምርምር ተቋም በኩል ነው።

ጥናቱ ይፋ እንዳደረገው ናሙናቸው ከተወሰዱባቸው ሰዎች መካከል 57 በመቶ ያህሉ ለኮቪድ-19 የተጋለጡ ናቸው።

በከተማዋ ምዕራብ፣ ምሥራቅና ማዕከላዊ አካባቢ የሚኖሩ 1.5 ሚሊዮን ሰዎች ይኖራሉ ተብሎ ይገመታል።

በጥናቱ ላይ የተሳተፉ ተመራማሪዎች ለቢቢሲ እንደተናገሩት በቫይረሱ ክፉኛ የተጎዳችው በዚህች ከተማ ላይ የተሰራው ጥናት ስለቫይረሱ ስርጭት የሚናገረው ነገር አለ ሲሉ ገልፀዋል።

መጀመሪያ ቫይረሱ ቀድሞ ከታሰበው በላይ በከተማዋ 12.5 ሚሊየን ሰዎች በሚኖሩበት የምንዱባኖች መንደር ውስጥ በሰፊው መሰራጨቱን ነው።

ከፍተኛ ሆነው ስርጭት የሚያሳየው በእነዚህ አካባቢዎች የሚኖሩ ሕንዳውያን በጋራ በሚጠቀሟቸው መጸዳጃ ቤቶችን የመሳሰሉ በመኖራቸው ነው ተብሏል።

"ውጤቱ የሚያሳየው ከፍተኛ ጥግግት ያለበት ኑሮ እንዴት ለቫይረሱ እንደሚያጋልጥ ነው" ያሉት በታታ የምርምር ተቋም ውስጥ የሚሰሩት ሳንዲፕ ጁኔጃ ናቸው።

የሙቀት ልኬት ሲካሄድ

የፎቶው ባለመብት, 1 RUPEE CLINIC

ጥናቱ ሌላው ያሳየው ነገር በርካታ ቁጥር ያላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው ምንም ምልክት ሳያሳዩ መዳናቸውን ነው። ይህም በአካባቢው የተከሰተውን የሞት ቁጥር አነስተኛ ያደረገው ሲሆን ይህ ደግሞ በከተማ ደረጃ በኮቪድ-19 ምክንያት የሚሞቱ ሰዎች ቁጥርን ዝቅተኛ አድርጎት ቆይቷል ተብሏል።

በዚህ ጥናት ሌላው የተረጋገጠው ነገር በድሆች መንደር የሚኖሩም ሆነ ከዚያ ውጪ መኖሪያቸው የሆነ በርካታ ሴቶች ለቫይረሱ ተጋላጭ ሆነው መገኘታቸውን ነው።

ተመራማሪ ዶ/ር ኡላስ ኤስ ኮልቱር ለቢቢሲ እንደገለፁት "ምክንያቱን አላወቅነውም። ከማኅበራዊ ጠባይ እስከ አካላዊ ልዩነት ድረስ ሊሆን ይችላል" ብለው ለቢቢሲ አስረድተዋል።

በሙምባይ ያለው አዳዲስ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየቀነሰ መምጣት ሌላ ጥያቄ አጭሯል።

ምናልባት በከተማዋ ስርጭቱ ተስፋፍቶ ሰዎች የመከላከል አቅማቸውን አዳብረው ይሆን? ወይስ የወል ተፈጥሯዊ መከላከያ [ኽርድ ኢሚዩኒቲ ]ተገንብቶ ለሚለው ከጥርጣሬ ውጪ ምላሽ አልተገኘም።

ሙምባይ ማክሰኞ እለት ብቻ 717 አዲስ በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን የመዘገበች ሲሆን ከባለፉት ሦስት ወራት ወዲህ ትንሹ ነው ተብሏል።

የተመራማሪዎቹ ቡድን ጥርት ያለ መልስ ላይ ያልደረሰ ሲሆን ድጋሚ የዳሰሳ ጥናቱ እስካልተደረገ ድረስ ማኅበረሰቡ ውስጥ የወል ተፈጥሯዊ መከላከያ ዳብሯል የሚለውን መናገር እንደማይቻል ዶ/ር ኮልቱር ገልፀዋል።

የዳሰሳ ጥናቱ ከሦስት ወር በኋላ የሚደገም መሆኑ የተገለፀ ሲሆን በዚህም ወቅት ስርጭቱ መስፋፋቱ አልያም መቀነሱ የሚታይ ይሆናል። ይህም በከተማዋ የቫይረሱ ስርጭት ያለበት ሁኔታን ማወቅ ያስችላል ተብሏል።

"የመረጥናቸው ሦስት አካባቢዎች ላይ የተገኘው የኮሮናቫይረስ መጠን ይለያያል፤ አንዳንድ አካባቢዎች በድህነት ተጠጋግተው የሚኖሩ ሲሆኑ የተወሰኑ አካባቢዎች ደግሞ ለብቻቸው የሚኖሩ አካባቢዎች ነው፤ ሃሳቡ በአንድ አካባቢ መኖር ለስርጭቱ መስፋፋት አስተዋጽኦ አድርጓል? የሚለውን ለማየት ነው" ያሉት ደግሞ ዶ/ር ኮልቱር ናቸው።

ተመራማሪዎች የዳሰሳ ጥናቱ የመላ ከተማዋን ሁኔታ እንደማያሳይም ተናግረዋል። "ነገር ግን የስርጭቱ መጠን ከዚህ እጅግ በጣም የራቀ ነው ብለን አናምንም" ያሉት ደግሞ ዶ/ር ጁንጃ ናቸው።

በዚህ ወር መጀመሪያ ላይ መንግሥት በደልሂ ከአራት ነዋሪዎች መካከል አንዱ ለኮሮናቫይረስ የተጋለጠ መሆኑን ገልጿል።

ኮሮና
Banner