የጀርመን ባለስልጣናት የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መባባስ "በጣም አሳስቧቸዋል"

የፎቶው ባለመብት, Reuters
የጀርመን ማኅበረሰብ ጤና ተቋም ኃላፊ በአገሪቱ የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ እየተባባሰ መምጣት "በጣም እንዳሳሰባቸው" ገለፁ።
የሮበርት ኮች ተቋም ኃላፊ ሎተር ዌይለር "ያለነው በፍጥነት እያተስፋፋ በሚሄድ ወረርሽኝ መካከል ነው" በማለት ለሮይተርስ ተናግረዋል።
ዌይለር አክለው ጀርመናውያን "ቸልተኛ" እየሆኑ መምጣታቸውን በመግለጽ አፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ እና ማኅበራዊ ርቀታቸውን እንዲሁም ንጽህናቸውን እንዲጠብቁ አሳስበዋል።
ባለፉት ሳምንታት በጀርመን 3,611 ሰዎች በኮቪድ-19 መያዛቸው በምርመራ ተረጋግጧል።
ይህ ማስጠንቀቂያ የተሰማው በአውሮፓ ባሉ አገራት የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ዳግም እየተስፋፋ በመጣበት ወቅት እና በፈረንጆች የበጋ ወር የተነሳ ጎብኚዎች ከአገር አገር መንቀሳቀስ በጀመሩበት ጊዜ ነው።
ማክሰኞ ዕለት ጀርመን ከስፔን ሦስት አካባቢዎች የሚመጡ መንገደኞችን በሚመለከት ማስጠንቀቂያ አውጥታለች።
በቅርብ ጊዜያት በስፔን ሦስት ዛቶች፣ በአራጎን፣ ካታሎኒያ እና ናቫራ ቫይረሱ በስፋት እየተሰራጨ መሆኑ ተገልጾ ነበር።
ዩናይትድ ኪንግደምም ከስፔን ለሚመጡ መንገደኞች ለ14 ቀን ያህል ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ የወሰነች ሲሆን የስፔኑ ጠቅላይ ሚኒስትር እርምጃውን "ኢፍትሃዊ" ብለውታል።
ጀርመን ሰኞ የቫይረሱ ስርጭት ከተስፋፋባቸው አገራት የሚመጡ መንገደኞች በነጻ አስገዳጅ የኮሮናቫይረስ ምርመራ እንዲያደርጉ ጥሪ አስተላልፋለች።
እነዚህ አገራት ብራዚል፣ ቱርክ እና አሜሪካ ሲሆን ባለስልጣናት በየእለቱ መረጃው ሊሻሻል ይችላል ብለዋል።
ማክሰኞ እለት ዌለር ዜጎች ከቤታቸው ውጪ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት 1.5 ሜትር አካላዊ ርቀት መጠበቅ የማይችሉ ከሆነ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ እንዲያደርጉ አሳስበዋል።
ከዚህ ቀደም የነበረው መመሪያ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሕዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች፣ ቤት ውስጥም እንዲደረግ የሚያዝ ነበር።
ኃላፊው አክለውም ጀርመኖች "በፍጥነትና ከቁጥጥር ውጪ በሆነ መልኩ" ቫይረሱ ዳግም እንዳይስፋፋ አካላዊ ርቀታቸውንና ንጽህናቸውን በመጠበቅ ሊያስቆሙት ይገባል ብለዋል።
"ይህ የሁለተኛው ዙር ወረርሽኝ መሆንና አለመሆኑን የምናውቀው ነገር የለም ነገር ግን ሊሆን ይችላል" ያሉት ዌለር "ነገር ግን የኮቪድ-19 ወረርሽኝ መከላከል መመሪያዎችን ከተከተልን መከላከልና ማስቆም እንደምንችል ተስፋ አለኝ" ብለዋል።
በጀርመን እስካሁን ድረስ ቫይረሱ እንዳለባቸው በምርመራ የተረጋገጠ ሰዎች ቁጥር 206,242 ሲሆን 9,122 ሰዎች ደግሞ ሞተዋል።
በጀርመን የተከሰተው ሞት ከሌሎች የአውሮፓ አገራት አንጻር ሲታይ በጣም አነስተኛ ሲሆን፣ በዚህም በአገር ውስጥና በዓለም አቀፍ ደረጃ ወርሽኙን በፍጥነት በቁጥጥር ስር በማዋሏና ሰፊ ምርመራ በማካሄዷ አድናቆት ተቸሯት ነበር።
ነገር ግን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሰው በቫይረሱ መያዙ ታውቋል።














