በካንሰር ትሞታለህ ተብሎ ብዙ ያየው ታዳጊ ህይወትና ምኞት

ጄፍ የአንጎል ቀዶ ጥገና ከተደረገለት በኋላ ሆስፒታል ውስጥ

የፎቶው ባለመብት, Jeff Henigson

የካሊፎርኒያው ታዳጊ ጄፍ ሄኒግሰን የጭንቅላት ካንሰር እንዳለበት ሲታወቅ ቢበዛ በሕይወት ሊቆይ የሚችለው ለሁለት ዓመታት እንደሆነ ተነግሮታል።

ይሄኔ ነው አንድ ድርጅት የሚመኘው ነገር ካለ እውን ሊያደርግለት ቃል የገባው። ነገር ግን ጄፍ እንደ እኩዮቹ ዲዝኒላንድ [የሕፃናት መጫወቻ ስፍራ] ውሰዱኝ አሊያም የምወደውን እግር ኳስ ተጫዋች አገናኙኝ አላለም።

ይልቁንም ጄፍ እንዲህ አለ "እኔ የምመኘው ዓለም ሰላም እንድትሆን ነው።"

በአውሮፓውያኑ በ1986፤ የ15 ዓመቱ ጄፍ ብስክሌት እየነዳ ወደ አንድ ሱቅ እየሄደ ሳለ ነበር በመኪና የተገጨው። ጄፍ በወቅቱ ምንም ዓይነት የአደጋ ጊዜ መከላከያ አላደረገም ነበር።

በደረሰበት አደጋ ወዲያው ራሱን የሳተው ጄፍ። ከሰዓታት በኋላ ራሱን በአንድ ሆስፒታል አልጋ ላይ አገኘው። ነገር ግን አደጋው ብዙም ስላልጎዳው የዚያኑ ዕለት ከሆስፒታል እንዲወጣ ተደረገ።

ነገር ግን ከጥቂት ሳምንታት በኋላ ጄፍ ራሱን እየሳተ ይወድቅ ጀመር። ይሄን ጊዜ በድጋሚ ወደ ሆስፒታል ተወስዶ የጭንቅላት ሲቲ ስካን እንዲነሳ ተደረገ።

ጭንቅላቱ ውስጥ በአደጋው ምክንያት የደረሰ አደጋ ቢኖር ጄፍ አይደነቅም ነበር። ነገር ግን የምርመራው ውጤት የከፋ ውጤት ይዞ መጣ - የጭንቅላት ዕጢ።

በወቅቱ "ሁለት ነገሮች በአእምሮዬ ውስጥ ተመላለሱ" ይላል ጄፍ። አንደኛው ትምህርት ቤት ሲዘጋ ከሴት ጓደኛው ጋር ጥሩ የፍቅር ጊዜ ማሳለፍ፤ ሁለተኛው ደግሞ የጀመረውን የፈጠራ ሥራ ማጠናቀቅ።

Short presentational grey line

ጄፍ ተስፋ ያለው ታዳጊ ነበር። ሕልሙ ደግሞ ለአሜሪካው የህዋ ምርመር ተቋም ናሳ መሥራት ነበር። ጄፍ ለናሳ መሥራት ብቻ ሳይሆን ተቋሙ ከሩሲያ አቻው ጋር ከመቀናቀን ይልቅ አብሮ መሥራት ቢቻል ብሎ ይመኝ ነበር።

"ታዳጊ ብሆን እንኳ ሁለቱ አገራት አብረው ቢሠሩ ትልቅ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል አምን ነበር" ይላል ጄፍ። "የኒውክሌር ጦር መሣሪያን አንዳችን በአንዳችን ላይ መደገን ትርጉሙ ምን እንደሆነ አይገባኝም ነበር። ከዚህ ይልቅ ህዋ ላይ ወጥተን አብረን መሥራት እንችላለን።"

ጄፍ በዚያ ዓመት ክረምት ላይ ሊያደርግ ያሰባቸው ሁለት ነገሮች አልተሳኩለትም። እንዲያውም በፍጥነት ቀዶ ጥገና እንዲደረግለት ታዘዘ።

ስድስት ሰዓታት ከፈጀ ቀዶ ጥገና በኋላ ዶክተሮች ዕጢውን ማውጣት እንደተሳናቸው አመኑ። ከዚያ በኋላ ዕጢው ወደ ካንሰር ሊያድግ ይችላል፣ አይችልም የሚለውን ለመለየት ሰባት ቀናት መቆየት ግዴታ ሆነ።

"ዶክተሯን ወደእኔ ስትመጣ ፊቷን አይቼ መልካም ዜና ነው ወይስ መጥፎ የሚለውን መለየት አልቻልኩም። ከዚያ እንዲህ አለችኝ 'ይህንን ስነግርህ እያዘንኩ ነው፤ የጭንቅላት ካንሰር አለብህ። በጣም በፍጥነት እያደገ ነው።'

"ከዚህ በኋላ ምን ያህል ጊዜ አለኝ ስል ጠይቅኳት።"

"ምናልባት ሁለት ዓመታት።"

ጄፍ ከወላጆቹ ጋር

የፎቶው ባለመብት, Jeff Henigson

የምስሉ መግለጫ, ጄፍ ከወላጆቹ ጋር

ጄፍ የጨረር ሕክምና ጀመረ። ኪሞቴራፒም ይከታተል ገባ። በተቻለው መጠን ትምህርቱን መከታተል ያዘ። ካንሰር ያለባቸው ወጣቶች የተሰባሰቡበት ቡድን አባልም ሆነ።

"ስላደረጓቸው ነገሮች ይነግሩኛል። በጣም የምንወደውን አትሌት ተዋወቅን፤ ዲዝኒላንድ ሄድን ይሉኛል። እኔ ይሄ የሕፃናት ምኞት ይመስለኝ ነበር ስላቸው እኛ እኮ ሕፃናት ነን ይሉኛል። የእኔ ምኞት ግን ይህ አልነበረም።"

የጄፍ እናት ሞት አፋፍ ላይ ያሉ ሕፃናት የመጨረሻ ምኞት እውን የሚያደርግ አንድ ድርጅት አግኝታ መፃፃፍ ጀመረች።

ከዚያም ከድርጅቱ ሁለት ሰዎች መጥተው "ጄፍ ምኞትህ ምንድነው?" ሲሉ ጠየቁት። ጄፍ መጀመሪያ እንዲህ አለ። "እውነቱን ንገሩኝና በቀጣዩ የህዋ ጉዞ ላይ አሳፍሩኝ ብላችሁ ታሳፍሩኛላችሁ?"

ሰዎቹ ጄፍን በምስኪን ዓይን እያዩት "ኧረ በፍፁም" አሉት። ባይሆን ሊሆን የሚችል ምኞት ተመኝ በሚል ዓይን ያዩት ጀመር።

"ሶቪየት ሕብረት ሄጄ ሚካይል ጎርባቼቭን ማግኘት እፈልጋለሁ። የኒውክሌር ጦር መሣሪያ ፉክክር እና የቀዝቃዛው ጦርነት እንዲቆም ላማክራቸው እፈልጋለሁ።"

ጄፍ ይሄንን ሲል በክፍሉ ውስጥ ዝምታ ሰፈነ።

ሰዎቹ ግን "ሦስተኛ ምኞት የለህም እንደው ቀለል ያለ ዓይነት መልክ ያለው?" ፊታቸውን ጄፍ ላይ ተከሉ። ጄፍ ግን ከዚህ ውጪ ምኞት እንደሌለው ፈርጠም ባለ አተያዩ ይነግራቸው ጀመር።

ሰዎቹ የሚቻላቸውን እንደሚያደርጉ ነገር ግን ሁሉም ይሳካል ብለው ቃል እንደማይገቡ ነግረውት ሄዱ።

ጄፍ ወደ ሞስኮ በሄደበት ጊዜ

የፎቶው ባለመብት, Jeff Henigson

የምስሉ መግለጫ, ጄፍ ወደ ሞስኮ በሄደበት ጊዜ

ድርጅቱ፤ ጄፍ ከሌሎች አሜሪካውያን ወጣቶች ጋር ሶቪዬት ሕብረትን እንዲጎበኝ አመቻቸ። በዚህ ጉዞ ላይ ከተቻለ ጎርባቾቭ ለማግኘት ነበር የድርጅቱ ዓላማ።

ወጣቶቹ ሞስኮ ሲደርሱ ሰላይ እንደሚያጋጥማቸው ጠርጥረው ነበር። ዓላማቸውም እሱ ነበር። ነገር ግን ሌኒንጋርድ ውስጥ ምንም ዓይነት ሰላይ እየተከተላቸው እንዳልሆነ ሲያውቁ እንደመብሸቅ አደረጋቸው።

ነገር አንድ ወጣት የሆነ ሰው እየተከተላቸው እንደሆነ አስተዋለ። ሰውዬው ወጣቶቹ የገቡበት ይገባል፤ ሲወጡ ይወጣል።

ሰላዩ ብቻውን አልነበረም። ጄፍና ወጣቶቹ ያረፉበት ሆቴል ግድግዳው ተበስቶ ማደመጫ ገመድ እንደተዘረጋ አወቁ። አልፎም አንዷ ወጣት ወደ ክፍሏ ስትገባ ሁለት ወንዶች ቦርሳዋን ሲበረብሩ አገኘቻቸው።

"ይሄን ስናውቅ በጣም ደንግጠን ነበር። እኔ ቦርሳዬ ውስጥ ለጎርባቾቭ ስጦታ ይዤ ነበር። እሱን እንዲወስዱብኝ አልፈልግኩም" ይላል ጄፍ።

የድርጅቱ ሰዎች ሕልሙን እውን ለማድረግ እየሠሩ እንደሆነ ደጋግመው ይነግሩታል።

ነገር ግን ሕልሙ እውን ሊሆን ትንሽ ሲቃረብ የሆነ ደንቃራ ያጋጥመዋል።

የሆቴሉ መጠባበቂያ ሶፋ ላይ ቁጭ ብሎ ሳለ የጎርባቾቭ መልዕክኛ መጥቶ የሶቪዬት ሕብረቱ መሪ ጄፍን ሊያገኙት እንደማይችሉ ነገረው። ነገር ግን ሌላ በአገሪቱ መንግሥት ውስጥ ኃያል ሰው ሊያስተዋውቁት ስላሰቡ ሻንጣውን ሸክፎ እንዲከተላቸው ነገሩት።

ጄፍ ሻንጣውን በጉልበቱ እንደታቀፈ በሽንጠ ረዥም መኪና ከሞስኮ ከተማ ወጣ ብላ ወደምትገኝ ከተማ ተወሰደ። ስለሚተዋወቀው ሰው ምንም የሚያውቀው ነገር የለም።

"የሄድንበት ቦታ ከሚኖሩ ጥንዶች ጋር መልካም ጊዜ አሳለፍኩ። እራት በላን፤ ስለምንኖርባት ዓለም ብዙ ተጫወትን።"

ጄፍ ስለጥንዶቹ ያወቀው ወደ ሞስኮ ከተመለሰ በኋላ ነው። እራት የበላው ከኤቭጌኒ ቬሊኮቭ ጋር ነበር። ሰውዬው በኒውክሌር መሣሪያዎች ዙሪያ የሶቪዬት ሕብረት ቀኝ እጅ የሆኑ ሰው ናቸው።

ጄፍ ጎርባቾቭን ማግኘት ባይችልም በሶቪዬት ሕብረት የኒውክሌር ውሳኔ ከፍተኛ ሚና ካላቸው ሰው ጋር እራት መብላትና መጫወት ችሏል። ለጎርባቾች የያዘውን ስጦት ለመልዕክተኛቸው አስረክቦ በቀጣዩ ቀን ወደ ትውልድ አገሩ አሜሪካ ተመለሰ።

"አባቴ፤ ጎርባቾቭን አገኘኸው ብሎ ሲጠይቀኝ አላገኙሁትም ብዬ መለስኩለት። ጉዞዬ የከሰረ ሆኖ የተሰማኝ በዚህ ጊዜ ነው።"

እንደተፈራው የጄፍ ዕጢ ወደ ሞት አፋፍ ይገፋዋል ቢባልም ከሕክምናው በኋላ እየተሻለው መጣ። እሱም ትምህርቱን ይገፋበት ጀመር።

ጄፍ አሁን

የፎቶው ባለመብት, Jeff Henigson

የምስሉ መግለጫ, ጄፍ አሁን

ወደ ለንደን ተዛውሮ ኢኮኖሚክስ ካጠና በኋላ ወደ አሜሪካ ተመልሶ ኮሎምቢያ ዩኒቨርሲቲ ገባ። ከዚያም ተመርቆ ሲወጣ በተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ተቀጥሮ ይሠራ ጀመር። ዕጢውም አልታይ አለ።

በታዳጊነቱ 'ትሞታለህ' ተብሎ የተነገረው ጄፍ 37ኛ ዓመቱን ደፈነ። በዚህ ጊዜ ሚስቱን ይዞ ወዳደገበት መኖሪያ ቤት ሄደ።

"በወቅቱ አስከፊ ሕይወት እያሳለፍኩ ነበር" ይላል ጄፍ። በተደጋጋሚ ራሱን እየሳተ ሥራ መሥራት ባለመቻሉ ከተባበሩት መንግሥታት ሥራው እንዲቀነስ ሆነ። ትዳሩም የተቃና አልነበረም።

በልጅነቱ ክፍሉ ያገኛቸውን ዕቃዎች ሲበረብር አንድ በጥሩ እንግሊዝኛ የተፃፈ ደብዳቤ አገኘ። ደብዳቤው ላይ ያገኘውን ስልክ ቁጥር ሲመታ ሩሲያኛ ከምትናገር ሴት ጋር ተገናኘ።

ጄፍ ያገኘው ደብዳቤ ከዓመታት በፊት የተጻጻፈው ነበር። ይህን ጊዜ በዚያ ወቅት ይሰማኝ የነበረው ሁሉ ተመልሶ መጣ ይላል ጄፍ። ይህ ክስተት ሕይወቱን እንደ አዲስ እንዲቃኝ እንዳደረገው ይናገራል።

ጄፍ አሁን 49 ዓመቱ ነው። ፀሐፊ ነው። የመጀመሪያ መፅሐፉ 'ዋርሄድ' የተሰኘ ሲሆን ስለእራሱ የሕይወት ጉዞ የፃፈው ነው።

በቅርቡም ጤና ምርመራ ለማድረግ ወደ ሆስፒታል ሄዶ ዕጢው ሙሉ በሙሉ እንደጠፋ የሚያመላክት ማስረጃ አግኝቷል። ቢሆንም ዶክተሮች የሚጥል በሽታ ሊያጋጥመው እንደሚችል ነግረውታል።

ጄፍ፤ ሩሲያና አሜሪካ አሁንም በዓይነ ቁራኛ መተያየታቸው ቁጭት ያሳድረበታል። ሁለቱም አገራት የኒውክሌር መሣሪያ ክምችት እንዳላቸው ሲያስብ ደግሞ ስጋት ይገባዋል።

የነገር ግን ሁለቱ አገራት ብቻ ሳይሆን የሌሎችም አገራት የኒውክሌር መሣሪያ ክምችት አሁን ድረስ የጄፍ ጭንቀት አካል ናቸው።