በአውስትራሊያ ገንዘብ ለማግኘት ካንሰር ታምሜያለሁ ብላ ያጭበረበረችው ክስ ተመሰረተባት

የ27 ዓመቷ ሉሲ ዊይላንድ በኢንስታግራም የለጠፈችው ፎቶ

የፎቶው ባለመብት, Lucy Wieland/Instagram

በአውስትራሊያ የምትገኝ አንዲት ሴት ካንሰር ታምሜያለሁ ብላ በማጭበርበር እርዳታ ከሚያሰባስብ ድረገፅ 55 ሺ ዶላር በመቀበሏ ክስ ተመስርቶባታል።

የ27 ዓመቷ ሉሲ ዊይላንድ የማህበራዊ ሚዲያንም በመጠቀም የማህፀን ካንሰር በሽታ ጋር እንዴት እየታገለች እንዳለችም በተደጋጋሚ ትፅፍ እንደነበር ፍርድ ቤቱ ገልጿል።

ፖሊስ ጨምሮ እንደገለፀውም የገንዘብ እርዳታንም ለመጠየቅ የህዝቡን ዕምነትም ጥያቄ ውስጥ ከታዋለች ብሏል።

ለእስር የበቃችውም በአንድ ግለሰብ ጥቆማም እንደሆነ ተገልጿል።

በኢንስታግራም ላይ በለጠፈችው ፎቶ ሉሲ ዊይላንድ የኦክስጅን ጭምብልን ጨምሮ በተለያዩ የህክምና ቁሳቁስ ተከባ ታይታለች።

በሌሎች ፎቶዎችም ላይ በህክምና ቦታ ላይ ፀጉሯ ሙሉ በሙሉ ተላጭቶ የሚሰሟትን ስሜቶችም አጋርታለች።

"ከመጠን ያለፈ ድካም ይሰማኛል፤ እንደተለመደው ድጋፋችሁን ለምትሰጡኝ ሁሉ አመሰግናለሁ" ብላለች።

በአንዳንድ ፎቶዎቿ ላይ የሚታየው የህይወት አጋሯ ስለማጭበርበሯ ይወቅ አይወቅ ግልፅ አይደለም ተብሏል።

ጉዳዩን በዋነኝነት የያዘው መርማሪ ክሪስ ላውሰን ለሪፖርተሮች ሐሙስ እለት እንደተናገረው " በጣም አሳዛኝ ነው። በማህበረሰባችን የሚገኙ ትክክለኛ ታማሚዎችና እሷን የረዷት ናቸው በዚህ ወንጀል ተጠቂ የሆኑት" ብለዋል።

ጥርጣሬዎች የተነሱት የማህበረሰቡ አባላት እርስ በርስ የሚጣረሱ ነገሮችን ከሰሙ በኋላ መሆኑን ኤቢሲ የተባለው የሚዲያ ወኪል ዘግቧል።

ሉሲ ዊይላንድ ዋስትናዋን ባትከለከልም ፓስፖርቷ እንደተወሰደባት ተገልጿል። ፍርድ ቤቱ ለታህሳስ ቀጠሮ ሰጥቷታል።

ጎ ፈንድ ሚ ተብሎ የሚታወቀው ድረ ገፅ ምርመራውን እንደሚያግዙ ገልፀው ገንዘቡም ለለጋሾቹ እንደሚመለስ ገልፀዋል።