ዝነኛውን ጎሬላ የገደለው ግለሰብ የ11 ዓመት እስር ተፈረደበት

ራፊኪ

የፎቶው ባለመብት, Uganda Wildlife Authority

የምስሉ መግለጫ, ራፊኪ የተሰኘው ጎሬላ በተገደለበት ወቅት 25 ዓመት ይሆነው ነበር ተብሏል

በኡጋንዳ ዝነኛ የነበረውና 'ራፊኪ' በመባል የሚታወቀውን ጎሬላ የገደለው አዳኝ የ11 ዓመት እስር ተፈረደበት።

ፌሊክስ ቢያሙካማ የተሰኘው ግለሰብ ጥፋተኛ ነው ተብሎ የተፈረደበት ጥብቅ ወደ ሆነ ስፍራ በሕገወጥ መልኩ በመግባትና ጎሬላውን በመግደል ነው።

ቢያሙካማ ጎሬላው ጥቃት እንዳደረሰበት እናም ራሱን ለመከላከል ሲል እንደገደለው መግለፁን የኡጋንዳ ዱር እንስሳት ባለስልጣን ገልጿል።

የኡጋንዳ ዱር አራዊት ባለስልጣን የተራራ ላይ ጎሬላዎች ለመጥፋት የተቃረቡመሆናቸውንናበአሁን ሰዓት ከ1000 በላይ የሚሆኑ ብቻ እንደሚገኙ ገልጾ፣"ራፊኪ ፍትህ አግኝቷል" ብሏል።

ቢያሙካማ ዱእከር የተሰኘች አነስተኛ ሚዳቋ እና የዱር አሳማ በመግደል እና የሁለቱንም ሥጋ እዞ በመገኘትም ተከስሷል።

ለዱር እንስሳት ባለስልጣናቱ ከዚህ ቀደም እንዳመነው እንስሳቶቹን የገደለው አነስተኛ እንስሳትን ለማደን በሚል መሆኑን በመግለጽ ራፊኪን ግን ሊያጠቃው ስለነበር ራሱን ለመከላከል መግደሉን አስረድቷል።

የጎሬላውን ግድያ የመረመሩ አካላት በስለታማ ነገር ተወግቶ መሞቱን አረጋግጠዋል።

ጎሬላው ሰኔ ወር የመጀመሪያ ሳምንት ላይ መጥፋቱ ከተረጋገጠ በኋላ በማግስቱ ሬሳው ተገኝቷል።

የኡጋንዳ ዱር እንስሳት ባለስልጣን አባላት ቢያሙካማን በፓርኩ አቅራቢያ በሚገኝ መንደር ውስጥ አስሰው ሲያገኙት አብሮት የአደን መሳሪያዎች ተይዘዋል።

ከቢያማካማ ጋር አብረው ነበሩ የተባሉ ሌሎች ሦስት ሰዎችም ውሳኔ እስኪሰጣቸው ድረስ በእስር ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል።

ቢያሙካማ ለተለያዩ ጥፋቶቹ የተወሰነበት አንድ ላይ ተደምሮ 11 ዓመት በወህኒ ቤት እንደሚያሳልፍ ለማወቅ ተችሏል።

ከዚህ ቀደም እድሜ ይፍታህ ሊፈረድበት ይችላል ተብሎ የተገመተ ቢሆንም፤ ይህ ግን ያልሆነው በዱር እንስሳት ልዩ ችሎት ባለመዳኘቱ መሆኑን የዱር እንስሳት ባለስልጣን መስሪያ ቤት ቃል አቀባይ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

ራፊኪ እየተመገበ

የፎቶው ባለመብት, Uganda Wildlife Authority

የምስሉ መግለጫ, ከ1000 በላይ የተራራ ጎሬላዎች በህይወት መኖራቸው ይነገራል

ራፊኪ ህይወቱ ባለፈበት ወቅት 25 ዓመት እንደሚሆነው የተገመተ ሲሆን፤ የ17 የተራራ ጎሬላዎች ቡድን መሪም ነበር።

ኡጋንዳ ከቱሪዝም በምታገኘው ከፍተኛ ገቢ ኢኮኖሚዋ የሚደጎም ሲሆን የተራራ ጎሬላዎችም በጎብኚዎች ዘንድ ዝነኛ ናቸው።

ራፊኪ ወደ ብዌንዲ ጥብቅ ብሔራዊ ፓርክ በሚመጡ ጎብኚዎች ዘንድ በጣም ዝነኛ እንደነበር ተነግሯል።

ይህ ፓርክ በአሁኑ ጊዜ በኮሮናቫይረስ ምክንያት ዝግ ሲሆን በዚሁ ወቅትም የአደን ቁጥር መጨመሩን የዱር እንስሳት ባለስልጣናት ተናግረዋል።

የእንቅስቃሴ ገደብ ተጥሎ በነበረበት ወር ብቻ 300 ሕገወጥ አደኖች መመዝገባቸውን ፔሸንስ አቱሃይቲ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የተራራ ላይ ጎሬላዎች በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ ሩዋንዳ እና ኡጋንዳ ብቻ የሚገኙ ናቸው።

በ2018 የተራራ ላይ ጎሬላዎች ሕገወጥ አደንን ማስቆም ጨምሮ፣ ከፍተኛ ጥበቃ እና እንክብካቤ ከተደረገላቸው በኋላ ለመጥፋት ከተቃረቡ እንስሳት መዝገብ ላይ ስማቸው ተፍቋል።