ምጣኔ ሐብት ፡ ከብር ለውጡ በኋላ የወርቅ ዋጋ ለምን ጨመረ?

የፎቶው ባለመብት, NurPhoto
ከቅርብ ሳምንታት ወዲህ አዲስ አበባ ውስጥ በሚገኙ መደብሮች የወርቅ ዋጋ ጭማሪ ማሳየቱን ነጋዴዎችና ገዢዎች ለቢቢሲ ገለጹ።
ቢቢሲ በመሐል አዲስ አበባ ፒያሳ አካባቢ በሚገኙ የወርቅ መሸጫ መደብሮች ተዘዋውሮ እንደተረዳው የወርቅ መግዣ እና የመሸጫ ዋጋዎች ላይ ጭማሪዎች ታይተዋል።
በተለይ ኢትዮጵያ የብር ኖቶቿን መቀየሯን ይፋ ካደረገችበት ከመስከረም ወር መጀመሪያ አንስቶ ጭማሪው በተለይ ከፍ ማለቱን በአዲስ አበባ ከተማ በወርቅ ንግድ ላይ የተሰማሩ ነጋዴዎች እና ሠራተኞች ለቢቢሲ ተናግረዋል።
ቢቢሲ አዲስ አበባ ውስጥ ዋነኛ የወርቅ መሸጫ መደብሮች በሚገኙበት በፒያሳ አካባቢ ቅኝት ባደረገበት በባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ 21 ካራት ወርቅ በግራም ከሦስት ሺህ ሰባት መቶ ብር እስከ አራት ሺህ ብር ይሸጣል መባሉን ከነጋዴዎቹ ለማረጋገጥ ችሏል።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መስከረም አስራ ሰባት ቀን ያስቀመጠው የወርቅ የመግዣ ዋጋ ለሃያ አንድ ካራት 2012 ብር ከስድሳ አራት ሳንቲም ሲሆን፤ የጥራት ደረጃው ላቅ ላለው የሃያ አራት ካራት ወርቅ ደግሞ 2300 ብር ከአስራ ስድስት ሳንቲም ዋጋ ሆኖ ተቀምጦለታል።
ባለፉት ጥቂት ወራት የወርቅ ዋጋ ጭማሪ ሲያሳይ መቆየቱን ቢቢሲ አግኝቶ ካናገራቸው የወርቅ መሸጫ መደብሮቹ ባለቤቶች እና ሠራተኞች ተረድቷል።
ይሁንና የወርቅ ዋጋ ጭማሪው በተለይ የብር ኖቶች መቀየር ይፋ ከተደረገበት ጊዜ አንስቶ የበለጠ ከፍ ማለቱን በወርቅ ንግድ ላይ የተሰማሩት ነጋዴዎች ጨምረው ተናግረዋል።
"ባለፉት ሁለት ሳምንታት ብቻ በግራም እስከ አምስት መቶ ብር ድረስ ጨምሯል" ስትል በአንድ የጌጣጌጥ መሸጫ መደብር ውስጥ የምትሰራ እንስት ለቢቢሲ ተናግራለች።
ከግለሰቦች ቀለበት፣ ሃብል፣ የጆሮ ጉትቻና የመሳሰሉ የወርቅ ጌጣጌጦችን በመግዛት አትርፎ በመሸጥ የሚተዳደርና ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገ አንድ ወጣት ደግሞ ጭማሪው ከሽያጭ በተጨማሪም በግዢም ላይ እየተስተዋለ እንደሚገኝ ተናግሯል። "ከአንድ ወር በፊት አንድ ግራም የሃያ አንድ ካራት ወርቅ አንድ ሺህ ብር፤ ከፍ ሲል ደግሞ አንድ ሺህ አምስት መቶ ብር ከሰው ላይ እገዛ ነበር" የሚለው ወጣት "ባለፈው አስራ አምስት ቀን ውስጥ ግን ብዙ ጭማሪ አሳይቷል" በማለት ባለፈው አርብ አንድ ግራም ወርቅ ሁለት ሺህ አንድ መቶ ሃምሳ ብር መግዛቱን ተናግሯል።
ከሌላው ጊዜ በተለየ ወርቅ የሚገዙ ሰዎች ፍላጎት መጨመር ዋጋውን ማናሩን የሚናገረው ይህ ወጣት፤ ከብር ኖቶች ቅያሪው ጋር ተያይዞ የተከማቸ ገንዘብን ወደአስተማማኝ ውድ ዕቃ መቀየር የሚፈልጉ ሰዎች ሳይኖሩ እንደማይቀሩ ግምቱን አስቀምጧል።
"የገንዘብ ኖቶች ለውጡ ሳይጠበቅ ዱብ ያለ በመሆኑ ውዥንብር እና እርግጠኛ ያለመሆን ስሜቶች ፈጥሯል" የሚሉት የምጣኔ ሐብት ጉዳዮች ተንታኙ አብዱልመናን መሃመድ ናቸው።
ከዚህም ጋር ተያይዞ ገንዘብ በእጃቸው ላይ ያላቸው ሰዎች ደኅንነታቸው አስተማማኝ በሆኑ ንብረቶች ላይ ብራቸውን ለማዋል መፈለጋቸውን በወርቅ ግብይቱ ላይ የታየውን የዋጋ ለውጥ እንደምሳሌ በማንሳት ይገልፃሉ፤ "ይህም በእነዚህ ንብረቶች ዋጋ ላይ የመናር ምክንያት ሊሆን ይችላል" ባይ ናቸው።
"መኪና እና ቤትን የመሳሰሉ ቋሚ ንብረቶችን እንዲሁም ወርቅን የመሳሰሉ ሌሎች ንብረቶች ላይ ገንዘብን ማዋል እንደአማራጭ ስለሚወሰድ ተፈላጊነታቸው መጨመሩ የሚጠበቅ ነው" ሲሉ ለቢቢሲ የተናገሩት አብዱልመናን፤ በሕገ ወጥ መልኩ የተገኘ ገንዘብን ለመሸሸግም ወርቅ ቀላል መንገድ ነው ይላሉ። "ስለዚህም የወርቅ የዋጋ ጭማሪን የፈጠረው የገንዘብ ኖት ለውጡ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም" ሲሉ እምነታቸውን ይገልጻሉ።
ባለፈው ዓመት ወርሃ ግንቦት ላይ ብሔራዊ ባንክ ከ63 ሚሊዮን ዶላር በላይ የሚገመት ወርቅ ወደ ገበያ መቅረቡን ገልፆ እንደነበር ይታወሳል።
በወቅቱ የባንኩ ገዥ የሆኑት ይናገር ደሴ (ዶ/ር) ይህ የተጠቀሰው የወርቅ መጠን ከፍተኛ እንደነበርና ለመንፈቅ ዓመት ያህል የቁልቁል ይጓዝ የነበረው የወርቅ አቅርቦትን መጠን የቀየረ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ለወትሮውም ብሔራዊ ባንክ ወርቅን በሚገዛበት እና በነጋዴዎች ገበያ ላይ በሚሸጥበት ዋጋ መካከል ልዩነት መኖሩን የጠቀሱት ባለሞያው፤ ይህም ጌጣጌጥ ቤቶች ለንድፍ ሥራዎች፣ ለአገልግሎት ወጪዎች እና ለትርፍ በሚጨምሩት ገንዘብ ምክንያት ይመጣ እንደነበር ያስረዳሉ።
በሁለቱ መካከል ያለው ልዩነት ወደ ውጭ በሚላክ ወርቅ መጠን ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ነበረው የሚሉት አብዱልመናን ይህንን ከግምንት ውስጥ በማስገባት በወርሃ ሐምሌ በብሔራዊ ባንክ የዋጋ ሽግሽግ ተደርጓል ብለዋል።















