ኢኮኖሚ፡ ኢትዮጵያ ለመጀመሪያ ጊዜ የ200 ብር ኖት ይፋ አደረገች

200 ብር

የፎቶው ባለመብት, PMO

ኢትዮጵያ በገበያ ላይ ባሉት የወረቀት ገንዘቦቿ ላይ ለውጥ ስታደርግ፤ ለመጀመሪያ ጊዜ በወረቀት ገንዘቧ ውስጥ ባለ 200 ብር ኖቶችን መጠቀም ጀመረች።

ይህ ይፋ የሆነው ዛሬ [ሰኞ መስከረም 04/2013] ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ በትዊተር ገጻቸው በኩል ባስተላለፉት መልዕክትና የብር ኖቶቹ ምሰል ነው።

በዚህም መሠረተው ከዛሬ ጀምሮ አገሪቱ የ10፣ 50 እና 100 ብር ኖቶቿን ስትቀይር ከዚህ በፊት ያልነበረው የ200 ብር ኖትን ደግሞ መጠቀም ጀምራለች።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንዳሉት አዲሶቹን የገንዘብ ኖቶች ይፋ መድረግ ያስፈለገው ለሕገ ወጥ እንቅስቃሴዎች የሚደረግን ድጋፍ፣ ሙስናንና የኮንትሮባንድ ሥራዎችን ለመቆጣጠር ያግዛሉ።በተጨማሪም አዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች እንዲኖራቸው የተደረጉት የደኅንነት ገጽታዎች አመሳስሎ ሐሰተኛ የገንዘብ ኖቶችን ለማተም የሚደረጉ ሕገ ወጥ ጥረቶችንም ለማስቀረት እንደሚግዙ ተጠቁሟል።

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ የሚገኙት የብር ኖቶች ወደ ዝውውር እንዲገቡ የተደረጉት ከ23 ዓመት በፊት በ1990 ዓ.ም ከኢትዮ-ኤርትራ ጦርነትን ተከትሎ እንደነበረ ይታወሳል።

ከአጼ ኃይለ ሥላሴ አስተዳደር ዘመን ጀምሮ በኢትዮጵያ ሥራ ላይ በነበሩ የገንዘብ የወረቀት ገንዘቦች ላይ በተለያዩ ጊዜያት ለውጥ የተደረገ ሲሆን፤ ወደ አምሳ ዓመታት በሚጠጋው የንጉሡ የሥልጣን ዘመን አራት ጊዜ የብር ኖቶች ለውጥ ተደርጓል።

ወታደራዊው መንግሥት ዘውዳዊውን ሥርዓት አስወግዶ አገሪቱን መምራት ከጀመረ ከጥቂት ዓመታት በኋላ በ1969 ዓ.ም የንጉሡ ምስልን የያዙትን የመገበያያ ገንዘቦች ለውጦት ቆይቷል።

በተመሳሳይም ኢህአዴግ ደርግን አስወግዶ አገሪቱን ከተቆጣጠረ በኋላም ለሰባት ዓመታት ያህል ቀድሞ የነበረውን ገንዘብ ሲጠቀም ቆይቶ በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል የድንበር ጦርነት ከተቀሰቀሰ በኋላ በአጭር ጊዜ ውስጥ የብር ኖቶቹ እንዲቀየሩ አድርጓል።

በኢትዮጵያ ከንጉሡ ዘመን ጀምሮ አገልግሎት ላይ የነበሩት የገንዘብ ኖቶች 1፣ 5፣ 10፣ 50 እና 100 ብር የነበሩ ሲሆን፤ ለረጀም ጊዜ ከፍተኛ ዋጋ ያለው የገንዘብ ኖት 100 ብር ሆኖ ቆይቷል።

ቢሆንም ግን በአጼ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ለመጀመሪያ ጊዜ አገልግሎት ላይ ከዋሉት የብር ኖቶች መካከል የ2 ብር እና የ500 ብር ኖቶች ነበሩበት።

ስለዚህም በአገሪቱ የወረቀት ገንዘብ ታሪክ ውስጥ ከፍተኛ ዋጋ የነበረው የብር ኖት ባለ 500 ብር ኖት የነበረ ሲሆን በኋላ ላይ ግን ከግብይት እንዲወጣ መደረጉን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል።

ስለዚህም አሁን ከወረቀት የብር ኖቶች መካከል እንዲገባ የተደረገው የባለ 200 ብር ኖት በታሪክ ሁለተኛው ከፍተኛ ዋጋ ያለው ሲሆን ወደገበያ ሲገባም ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።

ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ የብር ኖት ለውጥ እንደሚደረግ በተለያዩ መንገዶች ሲነገር የቆየ ሲሆን፤ ከብር ዋጋ መቀነስ ጋር ተያይዞ 500 ዋጋ ያለው የብር ኖት ወደ ገበያ እንደሚገባ አንዳንድ ሰዎች ሲገልጹ ቆይተው ነበር።

በአገሪቱ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ለውጦች መደረግ ከጀመሩባቸው ባለፉት ሦስት ዓመታት ውስጥ ከፍተኛ ሕገወጥ የገንዘብ ዝውውር እንደሚካሄድ በጉምሩክና በፖሊስ በኩል በተደጋጋሚ የሚወጡ ሪፖርቶች የሚያመለክቱ ሲሆን፤ ይህም ለውጥ ያስፈለገው ይህንኑ ለመከላከል መሆኑ ተነግሯል።