ገብርኤል ንጋቱ፡ የአፍሪካ ልማት ባንክ ቁልፍ ሰው

አቶ ገብርኤል ንጋቱ

አዲስ አበባ ውስጥ ተወልደው ያደጉት አቶ ገብርኤል ንጋቱ በአህጉራዊና በዓለም አቀፍ ግዙፍ ተቋማት ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ከሚገኙ ጥቂት ኢትዮጵያዊን መካከል አንዱ ናቸው።

በአፍረካ አገራት ውስጥ በሚካሄዱ የምጣኔ ሃብትና የልማት ተግባራት ላይ ቁልፍ ድርሻ ባለው የአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ ወሳኝ ከሚባሉ የባንኩ ባለስልጣናት አንዱ በመሆን ከ20 ዓመታት በላይ በ32 የአፍሪካ አገራት ውስጥ አገልግለዋል።

አቶ ገብርኤል ከአርባ ዓመታት በፊት ደርግ ወደ ስልጣን ላይ በወጣበት ጊዜ ነበር ከኢትዮጵያ ወጥተው ለአጭር ጊዜ አውሮፓ ውስጥ ከቆዩ በኋላ አሜሪካ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ኖረዋል።

አሜሪካ ውስጥ በስደት መኖር ሲጀምሩ ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ አስቸጋሪ እንደነበር የሚያስታውሱት አቶ ገብርኤል፤ መጀመሪያ ላይ አሜሪካ ውስጥ ለመኖር የሚያስፈልጋቸውን የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት እንደተቸገሩና ትምህርት ሳይጀምሩ ለተወሰነ ጊዜ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያ ውስጥ የነበረው ሁኔታ ሲባባስ ሕጋዊ የመኖሪያ ሰነድ ማግኘት ስለቻሉ ትምህርት ጀመሩ። ካሊፎርኒያ ስቴት ዩኒቨርስቲ ውስጥ የመጀመሪያ ዲግሪ በፕላኒንግ፣ ሁለተኛ ዲግሪን ደግሞ ከፒትስበርግ ዩኒቨርስቲ፣ ከዚያም በኋላ ሃርቫርድ ዩኒቨርስቲ እንዲሁም እንግሊዝ አገር ማንቺስትር ዩኒቨርስቲና ሌሎችም ቦታዎች ተምረዋል።

የስደት ፈተናና ጥረት

በንጉሡ የስልጣን ዘመን ማብቂያ ላይ ወደ አሜሪካ የመጡት አቶ ገብርኤል ህጋዊ በሆነ መንገድ ወደ አሜሪካ ስላልገቡ "በስደት ውስጥ ኑሮን ማሸነፍ ፈታኝ ነበር" ይላሉ።

የመኖሪያ ፈቃድ እኪያገኙ ድረስም በተለያዩ ችግሮች ውስጥ ማለፋቸውንና የሥራ ፈቃድ ስላልነበራቸው የጽዳት ሥራን ተደብቀው ይሰሩ እንደነበርም ያስታውሳሉ።

የንጉሡ ወዳጅ የነበሩት አሜሪካኖች ደርግ ስልጣኑን ይዞ ይወስዳቸው የነበሩትን እርምጃዎች ከተመለከቱ በኋላ ግን ለኢትዮጵያዊያን የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ሲጀምሩ በነጻነት የመኖርና የመስራት እድልን አገኙ።

"ኢትዮጵያዊ በተለይ ከአገሩ ሲወጣ ጠንካራ ነው" የሚሉት አቶ ገብርኤል ባገኙት አጋጣሚ ሁሉ የሚችሉትን ሁሉ እየሰሩ ለመማርና የተሻለ ህይወት ለመኖር መጣር ነበረባቸው።

ቢሆንም ግን ዝቅ ያለ ሥራ በመስራት የዕለት ተዕለት ወጪን ሸፍኖ ለመማር ከባድ እንደነበር የሚገልጹት አቶ ገብርኤል፤ ከሌሎች ሰዎች ጋር ተዳብለው በአንድ ላይ ቤት በመከራየት ከዚያም የተለያዩ ሥራዎችን በፈረቃ በመስራት ዛሬ ለደረሱበት ደረጃ ያበቃቸውን ትምህርት በፈታኝ ሁኔታ ውስጥ ሆነው መማር ጀመሩ።

የወጣትነት ፈተናዎች

በአፍላ የወጣትነት ዕድሜያቸው ከአገር የወጡት አቶ ገብርኤል ንጋቱ፤ መጀመሪያ ጣሊያን ለተወሰኑ ወራት መቆየታቸውንና ከዚያም ወደ አሜሪካ ሲሄዱም ከቤተሰብ ቁጥጥር ነጻ መሆን ከእድሜ ጋር ተያይዞ የራሱ ፈተና አለው ይላሉ።

ነጻነቱ እንዲሁም ቁጥጥር የማይደረግበት የተወሰነ ገንዘብ በእጅ መኖር ወደ ተለያዩ አላስፈላጊ ልማዶች ሊመሩ የሚችሉበት አጋጣሚዎች እንደነበሩና በዚያ ሁኔታ ውስጥ ደግሞ ራስን የመግዛት ጥንካሬ ያስፈልግ እንደነበር ያስታውሳሉ።

ነገር ግን የቤተሰባቸው አስተዳደግና በኃይማኖት ተቀርጸው እንዲያድጉ መደረጋቸው ከቤተሰብ ርቀው ባገኙት ነጻነት ወዳልተፈለገ አቅጣጫ እንዳይሄዱ እንዳደረጋቸውም ያምናሉ።

አቶ ገብርኤል በወጣትነት ዘመናቸው ከትክክለኛው የሕይወት መስመር የሚያወጡ በርካታ ፈተናዎች የነበሩ ቢሆንም ወደዚያ ባለመሄዳቸው ለስኬት በቅተዋል። ነገር ግን ጥቂት የማይባሉ ጓደኞቻቸው ለፈተናዎቹ ተሸንፈው "ሕይወታቸው መመሳቀሉንና ለተለያዩ ችግሮች" መዳረጋቸውን ያስታውሳሉ።

የአፍሪካ ልማት ባንክ

አቶ ገብርኤል ጋብቻ መስርተው ልጆች ሲወልዱ ወደ ወጡበት አህጉር ተመልሰው ልጆቻቸውን የማሳደግ ፍላጎት እንዳደረባቸው፤ ለዚህም ከባለቤታቸው ጋር ተስማምተው ሥራ ሲያፈላልጉ፤ አፍሪካ ልማት ባንክ አይቮሪኮስት ውስጥ ዩኒሴፍ ደግሞ ኬንያ ውስጥ ላሏቸው ክፍት ቦታዎች ላወጡት ሥራ ተወዳደሩ።

ሁለቱም ተቋማት አቶ ገብርኤል ለተወዳደሩበት ቦታ ከሌሎች ልቀው መገኘታቸውን በማመልከት አንዳቸው አንዳቸውን ተከትለው ሥራ እንዲጀምሩ ጋበዟቸው። አቶ ገብርኤልም ምርጫቸው አፍሪካ ልማት ባንክ ላይ አርፎ ቤተሰባቸውን ይዘው ከአሜሪካ ወደ ምዕራብ አፍሪካ አቀኑ።

የአፍርካ ልማት ባንክ ኢትዮጵያን ጨምሮ የአህጉሪቱ አገራት በባለቤትነት የሚያስተዳደሩት ሲሆን ከአፍሪካ ውጪ ደግሞ በተለያዩ አህጉራት የሚገኙ አገራትም በባንኩ ውስጥ የባለቤትነት ድርሻ አላቸው።

አቶ ገብርኤል በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ ሥራ ሲጀምሩ ከዝቅተኛው የሙያተኛ ደረጃ የተነሱ ቢሆንም በየሁለትና በየሦስት ዓመቱ እየተወዳደሩ በማደግ በድርጅቱ ውስጥ ባሉ ኃላፊነት ቦታዎች ውስጥ አልፈው ዋና ዳይሬክተር ከሚባለው ከፍተኛ ቦታ ላይ ለመድረስ ችለዋል።

አቶ ገብርኤል እንደሚሉት ባንኩ እርሳቸው በመሩት መልሶ የማዋቀር ሥራ በአምስት ቀጠናዎች ተከፋፍሎ እንዲሰራ የሚያስችለውን ሥራ አከናውነዋል።

ከዘዚህ በኋላም አቶ ገብርኤል በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ ካሉ አምስት የዋና ዳይሬክተርነት ቦታዎች ውስጥ አንዱን በመምራት በባንኩ ታሪክ የመጀመሪያው ዋና ዳይሬክተር ለመሆን ከመብቃታቸው ባሻገር ለዚህ የኃላፊነት ቦታም በመብቃት የመጀመሪያው ኢትዮጵያዊ ናቸው።

አቶ ገብርኤል በአፍሪካ ልማት ባንክ የምሥራቅ አፍሪካ አገራት ዋና ዳይሬክተር በመሆን ለበርካታ ዓመታት ከማገልገላቸው በፊት በሰላሳ ሁለት አገራት ውስጥ የሚሰራውን የባንኩን የመዋዕለ ነዋይ አስተዳደር ክፍልን በማቋቋምና ለበርካታ ዓመታት በመምራትም ጉልህ አሻራቸውን እንዳኖሩ ይነገርላቸዋል።

ከባንኩ ዋና ዋና ክፍሎች አንዱ የሆነውና መቀመጫውን ኬንያ ውስጥ ያደረገውን የ13 አገራትን የሚከታተለው የባንኩን የምሥራቅ አፍሪካ ቅርንጫፍን የመሰረቱት እንዲሁም ለረጅም ዓመታት የመሩት አቶ ገብርኤል ንጋቱ ናቸው።

ባንኩ የአገራትን ሕዝብና የምጣኔ ሃብት ዕቅድን መሰረት በማድረግ የሚያማክር ሲሆን አስፈላጊ በሚሆንበት ጊዜም በብድርም ሆነ በዕርዳታ የሚያስፈልጋቸውን ገንዘብ እንዲገኝና ዕቅዳቸው በተገቢው ሁኔታ ተግባራዊ እንዲሆን ክትትልና ድጋፍ በማድረግ በኩል ሚናው ከፍተኛ ነው።

አቶ ገብርኤል ንጋቱ

ፈተናና ስኬት

አቶ ገብርኤል በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ የቆዩበት ጊዜ በስኬት ብቻ የተሞላ አልነበረም፤ የዛሬ 12 ዓመት ገደማ የዓለም የኢኮኖሚ ቀውስ በተከሰተበት ጊዜ በአፍሪካ ሃብታም ከሚባሉ ጥቂት አገራት መካከል አንዷ የነበረችው ቦትስዋናን ለመደገፍ የተደረገው ጥረት እጅጉን በሥራ ሕይወታቸው ፈታኙ ነበር።

እጅግ ውድ የነበረውና ቦትስዋና በስፋት የምትታወቅበት የአልማዝ ምርት ገበያ በወቅቱ በመውደቁ አገሪቱ ከባድ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ በመውደቋ የአገሪቱ መንግሥት የአፍሪካ ልማት ባንክ ድጋፍ እንዲያደርግለት ጥሪ አቀረበ።

ለዚህ ሥራ ደግሞ በባንኩ ውስጥ ቀዳሚ ተመራጭ ሆነው የቀረቡት አቶ ገብርኤል ንጋቱ ነበሩ። ኃላፊነቱ እንደተሰጣቸው ለሥራው የሚያስፈልጋቸውን ቡድን አዋቅረው በመምራት ወደ ቦትስዋና ሄደው ድርድር በማድረግና ውድቀት አፋፍ ላይ የነበረውን የቦትስዋናን ኢኮኖሚ ለመታደግ የሚያስፈልጉ ፕሮጀክቶችን የመቅረጽ ሥራን ጀመሩ።

በወቅቱ አገሪቱ የገጠማት የኢኮኖሚ ቀውስ እጅግ አሳሳቢ ስለነበረ የሚያስፈልጋትን ድጋፍ ለይቶ በማወቅና መደረግ ያለባቸውን የማሻሻያ ዕርምጃዎች በማቅረብ በቶሎ እርምጃ ካልተወሰደ ፖለቲካዊ ቀውስ ሊፈጠር የሚችልበት ዕድል ስለነበረ፤ በአቶ ገብርኤል የሚመራው ቡድን ለአንድ ወር ያህል ለ24 ሰዓታት ያለዕረፍት በመስራት ጥረት አድርጓል።

ፕሮጀክት በማዘጋጀት፣ የፖሊሲ ሃሳቦችን በመቅረጽና ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር በመደራደር ቡድናቸው በቀንና በሌሊት ፈረቃ ተከፍሎ መፍትሄዎችን ለማምጣት ጥረት ማድረጋቸውን የሚናገሩት አቶ ገብርኤል "ሥራው እጅግ አስጨናቂና ውጥረት የተሞላበት ነበር" ይላሉ።

ይህ ለአንድ ወር የተሰራው ሥራ በመጨረሻም የቦትስዋና መንግሥት ማድረግ የሚገባውን የማሻሻያ ሃሳቦች ለባንኩ ቦርድ ቀርቦ ከስምምነት ላይ በመደረሱ በአፍሪካ ልማት ባንክ ታሪክ በወቅቱ ለአንድ ፕሮጀክት የተሰጠ ከፍተኛው ገንዘብ ለመሆን ችሏል።

ይህም ለቦትስዋና የተፈቀደ ከፍተኛው ብድር 1.5 ቢሊየን ዶላር ሲሆን አቶ ገብርኤልም ሐሳቦችን ከመቅረጽ አንስቶ ከመንግሥት ባለስልጣናት ጋር የሚደረገውን ድርድር በመምራት ወሳኝ ሚና ነበራቸው።

ይህም በአቶ ገብርኤል የአፍሪካ ልማት ባንክ የሥራ ህይወታቸው ውስጥ "እጅግ የተጨነቅኩበትና ለስኬቱም አጥብቄ የጸለይኩበት ጉዳይ ነበር" ሲሉ ያስታውሱታል። በአፍሪካ ጠንካራ ኢኮኖሚ ካላቸው አገራት አንዷ የሆነችው ቦትስዋናም ከአሳሳቢው የውድቀት አፋፍ ተመልሳ አሁን የተረጋጋ ኢኮኖሚ እንዲኖራት በማድረጋቸው አድናቆትን አግኝተዋል።

ኢትዮጵያና የአፍሪካ ልማት ባንክ

አቶ ገብርኤል ንጋቱ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ጋር በተያያዘ አገራቸው ኢትዮጵያን በሚመለከት ከፍ ያለ ፈተና ገጥሟቸው እንደነበር ያስታውሳሉ።

ወቅቱ አወዛጋቢው የ1997 ዓ.ም ብሔራዊ ምርጫን ተከትሎ "በአገሪቱ ቀውስና አለመረጋጋት ያጋጠመበት ነበር" ይላሉ። በአገሪቱ በተከሰቱ ግድያዎች ሳቢያ የዓለም የገንዘብ ተቋማት ለኢትዮጵያ የገንዘብ ድጋፍ እንዳይሰጡ ግፊት በሚደረግበት ጊዜ ውሳኔው መንግሥትን ብቻ ሳይሆን ሕዝቡንም የሚጎዳ በመሆኑ ሌላ አማራጭ እንዲፈልግ ጥረት አድርገዋል።

በዚህም አቶ ገብርኤል የሚሰጠው ድጋፍ ወደ መንግሥት እጅ ከመግባት ይልቅ ቁጥጥር እየተደረገበት ለሕዝቡ የሚቀርቡ 'መሰረታዊ አገልግሎቶችን ለመጠበቅ' የሚያስችል ፕሮግራም በመንደፍ አሁን ድረስ የዘለቀ አማራጭን አቅርበዋል።

ከዚህ በተጨማሪም አቶ ገብርኤል በባንኩ ድጋፍ ኢትዮጵያ ውስጥ የተካሄዱ ትልልቅ ፕሮጀክቶችን ጨምሮ የኢትዮጵያን የኤሌክትሪክ አቅርቦት ከጎረቤት አገራት ጋር ለማገናኘት እንዲሁም የመንገድ ግንባታዎችን በተመለከቱ ወሳኝ ፕሮጀክቶች ውስጥ ሚና ነበራቸው።

ምንም እንኳን አቶ ገብርኤል ከነበሩበት ኃላፊነት አንጻር ሁሉም የአፍሪካ አገራት አገራቸው እንደሆኑ ቢናገሩም ኢትዮጵያን በሚመለከት ግን ልባቸው የሚደላባቸው አጋጣሚዎች እንዳሉ አይሸሽጉም። በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ የአገራቸውን ጥቅም የሚነካ ነገር ካለ በዝምታ አያልፉም ይባልላቸዋል።

ባልደረቦቻቸውም ይህንን ስለሚያውቁ "ይህንን ገብርኤል አይቀበለውም" በማለት አስቀድመው እንደሚረዱ ገልጸው፤ ነገር ግን ይህ ድርጊታቸው ኢትዮጵያ ከሌሎች በተለየ እንድትጠቀም ሳይሆን "የኢትዮጵያ እንዳትበደልና የኢትዮጵያዊያን መብት እንዳይነካ የቻልኩትን ከማድረግ አንጻር ብቻ ነው" ይላሉ።

ነገር ግን ከሌሎች ጋር ከሚያደርጉት በተለየ ለአገራቸው ባለስልጣናት ጠቃሚ መረጃዎችንና ምክሮችን በመስጠት አገራቸውና ሕዝቡ እንዲጠቀም ከሙያቸው ሥነ ምግባር ሳይወጡ ካላቸው ኃላፊነት አንጻር የሚችሉትን ሁሉ ባገኙት አጋጣሚ ሲያደርጉ መቆየታቸውን ይናገራሉ።

ኢትዮጵያዊያን በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ

ኢትዮጵያ ከአፍሪካ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ ብትሆንም ዜጎቿ በአህጉራዊና በዓለም አቀፋዊ ተቋማት ውስጥ ያለቸው ተሳትፎ ዝቅተኛ መሆኑ "የሚያሳዝን ነው" ይላሉ አቶ ገብርኤል።

እንደምሳሌም የምዕራብ አፍሪካ አገር የሆነችው ጋምቢያን ያነሳሉ፤ ጋምቢያ በጣም ትንሽ የሕዝብ ቁጥር ቢኖራትም በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ በሚሰሩ ዜጎቿ ቁጥር ኢትዮጵያን በብዙ ዕጥፍ ትበልጣለች ይላሉ።

ለዚህም ከኃይለ ሥላሴ ሥርዓት መውደቅ በኋላ በነበሩት ጊዜያት ወደ ውጪ አገራት ሄዶ ለመማር የነበረው ዕድል መዘጋቱና ወደ ውጪ የሄዱትም ተምረው በትልልቅ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ከመግባት ይልቅ፤ የዕለት ኑሮን ለማሸነፍና ቤተሰብ ለመርዳት በተለያዩ ሥራዎች ላይ በመሰማራታቸው እንደሆነ ያስባሉ።

ወደ ተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ለመግባት በዋናነት የሚያስፈልገው ብቃት መሆኑን የሚጠቅሱት አቶ ገብርኤል ከዚህ ባሻገር ግን የመንግሥት ድጋፍ ወሳኝ ነው። መንግሥት ዜጎቹ ለተወዳደሩበት ተቋማት ባሉት የግንኙነት መስመሮች ሁሉ ድጋፍ ከሰጠና ተጽዕኖ መፍጠር ከቻለ ተቀባይነት ለማግኘት ወሳኝ እንደሆነ ይጠቅሳሉ።

ከዚህ አንጻር ግን ኢትዮጵያዊያን ብቃቱ ኖሯቸው ከመንግሥታቸው ድጋፍ ለማግኘት ስለሚቸገሩ የአገራቸውን ድጋፍ በሚያገኙ ሌሎች ተወዳዳሪዎች በመበለጥ ዕድሉን ያጣሉ።

"ላለፉት የኢትዮጵያ መንግሥታት እንዲዚህ አይነቱን ድጋፍ ለዜጎቻቸው ለመስጠት ኢትዮጵያዊ መሆን ብቻ በቂ አልነበረም፤ ነገሮች በፓርቲ አባልነት የሚወሰኑ ሆነው ቆይተዋል" የሚሉት አቶ ገብርኤል ይህ ግን አሁን እንደሚቀየር ያምናሉ።

ብዙ ኢትዮጵያዊያን ተምረውና ሰርተው ውጤታማ መሆንን የሚያስቡት በአገራቸው ውስጥ ነው። "ከዚህ ወጥተን ራሳችንን በዓለም ደረጃ ተወዳዳሪ መሆን እንደምንችልና በብቃታችን የሚገባንንም ለማግኘት አስከመጨረሻው መጠየቅና ገፍቶ መሄድ መልመድ አለብን" ብለዋል።

ለዚህ ደግሞ በተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ የሰሩ የተወሰኑ ኢትዮጵያዊያን በሥራቸው ብቁና የተመሰከረላቸው ስለሆኑ በችሎታ በኩል ኢትዮጵያዊያን ደፍረው መውጣት ከቻሉ ከማንም የሚያንሱበት የሥራ መስክ የለም ብለው ያምናሉ። ለዚህ ደግሞ ማበረታታትና ድጋፍ አስፈላጊ ነው።

ከዚህ አንጻር ለዜጎቻቸው ድጋፍ የሚያደርጉ አገራትን ሲያነሱ ሴኔጋልን በምሳሌነት ይጠቅሳሉ፤ በዓለም አቀፍ ተቋማት ውስጥ ለመስራት ለሚያመለክቱና ለሚሰሩ ዜጎቻቸው ድጋፍ የሚሰጥ ጽህፈት ቤት በአገሪቱ የውጪ ጉዳይ መስሪያ ቤቱ ውስጥ አለ።

ከዚህ በሻገርም አንድ ሴኔጋላዊ በየትኛውም ዓለም አቀፍ ድርጅት ውስጥ ለመቀጠር አመልክቶ ድጋፍ ካስፈለገው ፕሬዝዳንቱ ሳይቀሩ ለተቋማቱ ኃላፊዎች በመደወል ዕድሉ እንዲሰጣቸው እስከመጠየቅ የሚደርስ ድጋፍ ያደርጋሉ። ይህም የሚሆነው በፖለቲካ አመለካከት፣ በዕምነት ወይም በብሔር ሳይሆን ዜጋ በመሆን የሚሰጥ ድጋፍ ነው ይላሉ አቶ ገብርኤል።

ስንብት

ለ35 ዓመታት ከዘለቀው ትዳራቸው የሦስት ልጆች አባት የሆኑት አቶ ገብርኤል ንጋቱ፤ ከሃያ ዓመታት በላይ በአፍሪካ ልማት ባንክ ውስጥ በከፍተኛ የኃላፊነት ቦታ ላይ ቆይተው አክብሮትና ዝናን አትርፈዋል።

የአቶ ገብርኤል ዕውቅና ባገለገሉበት ድርጅት ውስጥ ብቻ ሳይሆን በተለያዩ የአፍሪካ አገራት መሪዎችና ከፍተኛ ባለስልጣናት ዘንድም "ንጋቱ" እየተባሉ አክብሮትን አግኝተዋል።

በዚህ ዓመት በጡረታ ከአፍሪካ ልማት ባንክ ሲሰናበቱ አቶ ገብርኤል በተለያዩ አገራት መሪዎች እየተጋበዙ ሽኝት ተደርጎላቸዋል፤ ድርጅታቸውም በአገልግሎት ዘመናቸው ላበረከቱት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በክብር ነበር የሸኛቸው።

"በቀጥታ ለአገሬና ለሕዝቧ ሰርቼ አላውቅም" የሚሉት አቶ ገብርኤል በውጪ አገር ለረጅም ዘመን ሰርተው ጡረታ ወጥተዋል። አሁን ባላቸው ዕውቀትና ልምድ አገራቸውን በሚጠቅሙ በተለያዩ መንገዶች ኢትዮጵያን ለማገልገል ፍላጎት እንዳላቸው ይናገራሉ።

በዳያስፖራ ትረስት ፈንዱ ውስጥ የአማካሪ ምክር ቤት አባል ሲሆኑ፣ ከተወሰነ የዕረፍት ጊዜ በኋላ በተለያዩ መስኮች ላይ በመሰማራት አገራቸውንና ሕዝቡ የሚጠቅሙ ሥራዎችን ለማከናወን ዕቅድ አላቸው።