ኢትዮጵያ ከኮሮናቫይረስ ምጣኔ ሐብታዊ ጫና ትተርፋለች?

የፎቶው ባለመብት, Elias Meseret- News Cafe
እስከ ሚያዝያ አንድ ድረስ ኢትዮጵያ ውስጥ ስድሳ አምስት ሰዎችን አጥቅቶ፣ ሦስቱን ለሞት ያበቃው የኮቪድ 19 ወረርሽኝ፤ እንደሌሎች የዓለም ክፍሎች ሁሉ ተያያዥ የሥነ ጤና፣ ማኅበራዊ እና ምጣኔ ኃብታዊ ጠንቆችን እንደሚያስከትል ይጠበቃል።
ወረርሽኙ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ አኳኋን በፍጥነት መዛመት፤ ይዟቸው የሚመጣቸውን ጣጣዎችም በዚያው ልክ የገዘፉ እንዲሁም በዓለም ዙርያ የተሰራጩ አድርጓቸዋል።
በዚያውም ልክ መጭውን ለመተነብይም አዳጋች ሆኗል።
ይሁንና በልዩ ልዩ ዘርፎች የተሰማሩ ባለሞያዎች የጉዳቱን መጠን ለመስፈር፤ የድኅረ-ወረርሽኝ አቅጣጫዎችንም ለመቀየስ መሞከራቸው አልቀረም።
ወረርሽኙ በሰዎች የሥራ እና የገቢ ሁኔታ ላይ የሚያሳርፈውን ጡጫ በተመለከተ ጥናት ያደረገው ዓለም አቀፉ የሥራ ድርጅት (አይ.ኤል.ኦ) እ.ኤ.አ መጋቢት 18 ቀን 2020 ባሳተመው ግምገማው ምንም እንኳ የኮሮናቫይረስ በዕድሜ የገፉትን እና ቀደም ሲል በሽታ የነበረባቸውን ግለሰቦችን የማጥቃት ከፍ ያለ ዕድል ቢኖረውም፤ ከወረርሽኙ በኋላ የሚከሰት የሥራ አጥነት ቀውስ ወትሮውኑም ሥራ ማጣት የሚያበረታባቸው ወጣቶች ላይ ሊጠነክር ይችላል ይላል።
በአገልግሎት ዘርፍ በብዛት ተሰማርተው የሚገኙት ሴቶች፣ ዋስትና አልባ ሥራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች (ለምሳሌ የራሳቸውን ሥራ የሚሰሩ እና በጊዜያዊነት የተቀጠሩ) አንዲሁም ስደተኛ ሠራተኞች አንዲሁ ክፉኛ በሥራ አልባነት ማዕበል ክፉኛ ሊደቆሱ ይችላሉ ይላል የአይ.ኤል.ኦ ግምገማ።
በምጣኔ ኃብት ያልጠነከሩ አገራት
ኢትዮጵያም ወረርሽኙ የሚያስከትለውን የጤና ቀውስ ለመቋቋም ከምታደርጋቸው ጥረቶች ባሻገር ይዞት የሚመጣው የምጣኔ ኃብት ጡጫ ያሳሰባት ይመስላል።
ከሳምንታት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ የበለፀጉ አገራት ኢትዮጵያን ለመሳሰሉ የአፍሪካ አገራት የዕዳ ቅነሳ እና የአስቸኳይ ጊዜ ድጋፍ እንዲያደርጉ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ባገባደድነው ሳምንት አዲስ አበባ ላይ በተደረገ የድረ ገፅ ላይ ውይይት የሥራ ፈጠራ ኮሚሽነሩ ኤፍሬም ተክሌ ሌማንጎ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ሰዎች ሥራዎቻቸውን ሊያጡ እንደሚችሉ መናገራቸው ተዘግቧል።
የሥራ ዕጦቱ በአገሪቱ ትልቁ ኩባንያ የኢትዮጵያ አየር መንገድ የጀመረ ይመስላል።
የአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈፃሚ ድርጅታቸው ከወረርሽኙ ጋር በተያያዘ 550 ሚሊዮን ዶላር ማጣቱን በገለፁበት መገለጫቸው ላይ ቋሚ ያልሆኑ ሠራተኞችን ለጊዜው ሥራ እንዲያቆሙ መደረጋቸውን ገልፀዋል።
የኢትዮጵያ የምጣኔ ኃብት ማኅበር ያሳተመው የአራት ባለሞያዎች ምልከታ ከወረርሽኑም በፊት ለብዙዎቹ ኢትዮጵያውያን መሠረታዊ ግልጋሎቶችን ማግኘት አዳጋች ነበር፤ ይህም ወረርሽኙን ለመከላከል መደረግ ያለባቸውን እርምጃዎች ቀላል እንዳይሆኑ ያደርጋቸዋል ይላል።
እንደአብነትም ከጠቅላላው ሕዝብ መካከል ስድስት በመቶ የሚሆነው ያህል በመኖርያው አቅራቢያ የመታጠቢያ ውሃ አለው ይላል።
ባለሞያዎቹ ብሔራዊው የስታትስቲክስ ድርጅት በማጠቀስ ከአራት ዓመት በፊት በተጠናቀረ መረጃ መሠረት አገሪቱ ውስጥ ካሉ ቤቶች ሰማንያ አምስት በመቶው ባለአንድ ወይንም ባለሁለት ክፍል መሆናቸውን አስታውሰው በኮቪድ 19 በሽታ ጥርጣሬ ቤት ውስጥ ተነጥሎ መቀመጥ አዋጭ አማራጭ ያለመሆኑን ይናገራሉ።
ወረርሽኑ የሚፈጥረው የምጣኔ ኃብት ንዝረት የአገልግሎት ዘርፉን፣ ቱሪዝምን እና የመስተንገዶ ኢንዱስትሪውን፣ የውጭ ንግድን እና የመጓጓዣ ዘርፍን ሊጎዳ እንደሚችል የሚገምተው የባለሞያዎቹ ምልከታ ግብርናም ቢሆን ከዚህ የሚተርፍ አይደለም ይላል- በተለይ በቀላሉ የሚበላሹ ምርቶች አብቃዮች እና አከፋፋዮች ለጉዳት ተጋላጭ መሆናቸው አይቀርም።
ወረርሽኙ የአቅርቦት ሰንሰለትን ያውካል። የሥራ መቀዛቀዝ በሚፈጥረው የገቢ እጥረት እንዲሁም የሚመጣው አይታወቅም በሚል ስጋት ምክንያት ሰዎች ገንዘብ ከማውጣት ስለሚቆጠቡ የፍላጎት እጥረትን ያስከትላል፤ አንዲሁም የንግድ ተቋማት የመንቀሳቀሻ ገንዘብ እጥረት እንዲያጋጥማቸው፣ ዕዳ መክፈል እንዲሳናቸውም ሊያደርግ ይችላል የባለሞያዎቹ ግምገማ እንደሚያመላክተው።
እነዚህ ችግሮች እርስ በእርስ እየተመጋገቡ የምጣኔ ኃብት እንቅስቃሴው በአዝጋሚነት ዘለግ ላለ ጊዝ የሚዘልቅ ከሆነ ምጣኔ ኃብታዊ መኮማተር (ሪሰሽን) ሊከተልም ይችላል።
ከኢትዮጵያ ጠቅላላ የአገር ውስጥ ምርት (ጂ.ዲ.ፒ.) ሰላሳ ዘጠኝ በመቶውን ድርሻ የሚይዘው የአገልገሎት ዘርፍ በወረርሽኙ ከሌሎች ዘርፎች በበለጠ ሊጎሳቆል ይችላል። ሰላሳ ሦሰት በመቶውን ድርሻ የሚይዘው ግብርና ግን ቢያንስ በአጭር ጊዜ ውስጥ በአንፃራዊነት ያነሰ ጉዳት ሊደርስበት ይችላል።
በባለሞያዎቹ ግምት መሠረት ወረርሽኙ አነስ ባለ የጉዳት ለሦስት ወራት ያህል ቢቆይ እንኳ ምጣኔ ኃብቱ እስከ 44 ቢሊዮን ብር የሚደርስ እጦትን ሊያስተናግድ ይችላል። ወረርሽኙ ለስድስት ወራት ቢቆይና የከፋ ጉዳት የሚያደርስ ቢሆን የእጦቱ መጠን ከሁለት መቶ ቢሊዮን ብር ይሻገራል።
ኮሮናቫይረስ ሠራተኞች ላይ ስለሚኖረው ተፅዕኖ የተሠራ አንድ ጥናት 3 ሚሊዮን ኢትዮጵያዊያን ሥራ-አጥ ሊሆኑ ይችላሉ ይላል።
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚስቶች ማኅበር ያሳተመው ጥናት ቫይረሱ ለረዥም ጊዜ የሚቆይ ከሆነ በርካቶች ሥራ-አጥ ሊሆኑ ይችላሉ ባይ ነው።
በቅርቡ የኢትዮጵያ ሥራ ፈጠራ ኮሚሽን በሠራው ጥናት እንደሚጠቁመው ቫይረሱ ለስድስት ወራት የሚቆይ ከሆነ በማኒዩፈክቸሪንግ ዘርፍ የተሰማሩ 60 በመቶ ሰዎች ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ።በተመሳሳይም በአገልግሎት ዘርፍ የተሰማሩ 74 በመቶ ሰዎች ሥራ-አጥ ይሆናሉ።
ጥናቱ አክሎም ከ9 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ተሰማርተውበታል በሚባለው የአገልግሎት ዘርፍ ብቻ 3 ሚሊዮን ሰዎች ሥራቸውን ሊያጡ ይችላሉ ይላል። ቫይረሱ በኅብረተሰቡ ውስጥ ከተንሰራፋ አደጋው የከፋ ሊሆን እንደሚችል ጥናቱ ያስጠነቅቃል።ጥናቱ የተሠራው የቫይረሱን ቆይታ በሁለት በመከፋፈል ነው።
የመጀመሪያው ለሦስት ወራት ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ስድስት ወራት ነው። የቫይረሱ ተፅዕኖ የከፋ ከሆነ ከ50 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን ችግር ላይ ሊወድቁ ይችላሉ ይላል።














