ኮሮናቫይረስ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የሚጠቁም መላ ሊፈጠር ነው

አፕል እና ጉግል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አፕል እና ጉግል ኮሮናቫይረስ ካለበት ሰው ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች የሚጠቁም መሣሪያ እየሠሩ ነው።

መሣሪያው አንድ ሰው በቫይረሱ ከተያዘ ግለሰብ ጋር የቅርብ ግንኙነት ካደረገ ለግለሰቡ መረጃ የሚሰጥ ነው።

መሣሪያው በበሽታው ከተያዙ ሰዎች ጋር ንክኪ ያላቸውን ሰዎች ለማሰስ ጥቅም ላይ ለሚውሉ መተግበሪያዎች የመረጃ ግብዓት እንደሚሰጥ ተገልጿል።

መሣሪያውን መጠቀም የሚፈልጉ ሰዎች ማንነታቸውን ሳያሳውቁ መመዝገብ ይችላሉ። ቫይረሱ ከያዛቸው ሰዎች ጋር ንክኪ ማድረግ አለማድረጋቸው የሚጣራውም የስልካቸውን ብሉቱዝ በመጠቀም ነው።

መሣሪያውን የሚጠቀም ሰው ካገኛቸው ሰዎች መካከል ኮቪድ-19 የተገኘባቸው ግለሰቦች ካሉ፤ መሣሪያው የማስጠንቀቂያ መልዕክት ይልካል።

አፕል እና ጉግል በጥምረት ባወጡት መግለጫ፤ መሣሪያው የተጠቃሚዎችን የግላዊነት መብት እንደማይጋፋ ተናግረዋል።

የአሜሪካው ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ፤ መሣሪያው ጠቃሚ ቢሆንም ብዙዎች የግላዊነት መብት ሊጥስ ይችላል የሚል ስጋት እንዳላቸው ጠቁመዋል። መንግሥታቸው መሣሪያውን ፈትሾ የሚደርስበትን ውሳኔ እንደሚያሳውቅም አክለዋል።

የአውሮፓ ሕብረት በበኩሉ፤ መሣሪያው መጠናት ቢኖርበትም፤ እስካሁን ባለው መረጃ መሰረት የተጠቃሚዎችን የግል መረጃ መብት አይጋፋም ብሏል።

ሴጋፖር፣ እስራኤል፣ ደቡብ ኮርያ እና ፖላንድ በኮሮናቫይረስ ከተያዙ ሰዎች ጋር የተገናኙ ሰዎችን የሚጠቁም መሣሪያ እየተጠቀሙ ነው።

ዩናይትድ ኪንግደም፣ ፈረንሳይ እና ጀርመንም መሰል መገልገያ ለመሥራት አቅደዋል።

አፕል እና ጉግል በጋራ መሥራት ከጀመሩ ሁለት ሳምንት ተቆጥሯል። መሣሪያው ስኬታማ ከሆነ ምናልባትም አገራት እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን ገደብ እያላሉ ሊሄዱ ይችላሉ ተብሏል።

ኮሮና
Banner