“ገደቦችን በአጭር ጊዜ ማንሳት ወረርሽኙ በአስከፊ ሁኔታ እንዲሰራጭ ያደርጋል” ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም

የዓለም ጤና ድርጅት ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

አገራት እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን ገደብ በአጭር ጊዜ ካነሱ፤ የወረርሺኙ ስርጭት በከፍተኛ ሁኔታ ሊጨምር እንደሚችል የዓለም ጤና ድርጅት አስታወቀ።

የድርጅቱ ኃላፊ ዶ/ር ቴድሮስ አድኃኖም እንዳሉት፤ ምንም እንኳን እንቅስቃሴ ላይ የተጣለው ገደብ በአገራት ምጣኔ ኃብት ላይ ጫና ቢያሳድርም፤ መንግሥታት እገዳውን ከማንሳታቸው በፊት ጥንቃቄ ሊያደርጉ ይገባል።

ቫይረሱ በከፍተኛ ሁኔታ የተሰራጨባቸው ስፔን እና ጣልያን እንቅስቃሴ ላይ የጣሉትን እገዳ ባያነሱም፤ እርምጃዎቻቸውን እያላሉ ነው።

ዶ/ር ቴድሮስ፤ በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የወረርሽኙ ስርጭት እየቀነሰ እንደሆነ ተናግረዋል። የኮሮናቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተጣሉ እገዳዎች እንዲላሉ፤ የዓለም ጤና ድርጅት ከተለያዬ አገራት ጋር እየተነጋገረ ቢሆንም፤ እርምጃው በአጭር ጊዜ ሊወሰድ እንደማይገባ አስረድተዋል።

“የተጣሉትን ገደቦች በአጭር ጊዜ ማንሳት ወረርሽኙ በአስከፊ ሁኔታ እንዲሰራጭ ያደርጋል” ብለዋል ኃላፊው።

ስፔን የፋብሪካ እና የግንባታ ሠራተኞች ወደ ሥራ እንዲመለሱ ለመፍቀድ እየተዘጋጀች ነው። ሆኖም ዜጎች ማኅበራዊ ርቀትን መጠበቅ እንዳያቆሙ ማሳሰቢያ ተሰጥቷል።

አገሪቱ ከ17 ቀናት በኋላ አነስተኛውን የሟቾች ቁጥር ያስመዘገበችው አርብ ነበር። እስካሁን በስፔን በቫይረሱ ሳቢያ የሞቱ ሰዎች 15,843 ደርሰዋል።

የጣልያኑ ጠቅላይ ሚንስትር ጁሴፔ ኮንቴ እስከቀጣዩ ወር እንቅስቃሴ እንዲገታ ትዕዛዝ ሰጥተዋል። ሆኖም ካለፈው ወር ጀምሮ የተዘጉ አንዳንድ የንግድ ዘርፎች እንዲከፈቱ ተወስኗል።

መጻሕፍት ቤቶች፣ የልጆች አልባሳት ሱቆች በድጋሚ ከሚከፈቱት መካከል ይጠቀሳሉ።

እስካሁን አገልግሎት እየሰጡ የነበሩት የመድኃኒት እና የምግብ መደብሮች ብቻ ነበሩ።

ባለፈው አርብ በበሽታው የተያዙ ሰዎች ቁጥር 570 የደረሰ ሲሆን፤ በቫይረሱ የሚያዙ አዲስ ሰዎች ቁጥር ከ4,204 ወደ 3,951 ወርዷል።

ሌሎች አገራትስ ምን እርምጃ ወሰዱ?

የአየርላንድ ጠቅላይ ሚንስትር ሊዮ ቫራድከር አገራቸው ውስጥ እስከ ቀጣይ ወር ድረስ እንቅስቃሴ እንደሚቆም ተናግረዋል።

ቱርክ በ31 ከተሞቿ የ48 ሰዓት የሰዓት እላፊ ገደብ ጥላለች። ፖርቹጋል ደግሞ እስከሚቀጥለው ወር ድረስ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ደንግጋለች።

ዩናይትድ ኪንግደም የቫይረሱ ስርጭት እስኪቀንስ የእንቅስቃሴ ገደብ አይነሳም ብላለች።

በደቡብ አፍሪካ ለ21 ቀናት ታውጆ የነበረው የእንቅስቃሴ እገዳ በሁለት ሳምንት ተራዝሟል።

የቫይረሱ ስርጭት እየቀነሰ ነው?

የዓለም ጤና ድርጅት፤ በአንዳንድ የአውሮፓ አገራት የበሽታው ስርጭት ዝግ እያለ መሆኑን ባለፈው አርብ በሰጠው መግለጫ ጠቁሟል።

ከኋይት ሀውስ፤ ዴቦራ ብሪክስ እንደተናገሩት፤ ወረርሽኙ ከፍተኛ ደረጃ አለመድረሱን የሚያሳዩ ተስፋ ሰጪ ምልክቶች አሉ።

በሌላ በኩል በሽታው ወደሌሎች አገሮች እየተሰራጨ መሆኑን ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል። በተለይም በአፍሪካ በገጠራማ አካባቢዎች ቫይረሱ እየተስፋፋ መጥቷልም ብለዋል።

“በአፍሪካ ከ16 በላይ አገራት ውስጥ በሽታው ወደ ማኅበረሰቡ ተሰራጭቷል። ከከተሞች አንጻር ደካማ የጤና ሥርዓት ያላቸው ገጠራማ አካባቢዎች በእጅጉ ይፈተናሉ” ሲሉ ዶ/ር ቴድሮስ ተናግረዋል።

ኮሮና
Banner