ኢኮኖሚ ፡ የኢትዮጵያ የብር ኖት መቀየር የሚኖረው አንድምታ

የፎቶው ባለመብት, PM OFFICE FB
ኢትዮጵያ ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ስትገለገልባቸው የነበሩ የ10፣ የ50፣ እናየ100 የገንዘብ ዓይነቶችን ሙሉ ለሙሉ ለመተካት አዲስ የገንዘብ ኖቶች ይፋ አድርጋለች።
ከአዲሶቹ የገንዘብ ኖቶች ውስጥም በታሪኳ ለመጀመሪያ ጊዜም የባለ ሁለት መቶ ብር ኖትም አሳትማለች።
አገሪቷ ነባሮቹን የብር ኖቶቹን ለመቀየር ሌላ ወጪ ሳይጨምር ለህትመት ብቻ 3.7 ቢሊዮን ብር ማውጣቷን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ አስታውቀዋል።
አገሪቱ የገንዘብ ኖቶችን ለመቀየር በኢ-መደበኛ መልኩ ገንዘብ ከባንክ ውጭ በከፍተኛ ሁኔታ መንቀሳቀሱ፣ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የሚሉ ምክንያቶችን አስቀምጣለች።
ከዚህ ቀደም አገሪቷ ከፋይናንስ ዘርፍ (ከባንክ) ውጭ ያለው ገንዘብ ከመደበኛው ባልተናነሰ መልኩ ከፍተኛ በመሆኑም እንዴት ይሰብሰብ የሚሉ ጥያቄዎች የባንኮች ዋና ማዕከል ሆነውም ነበር።
በኢ-መደበኛ ሁኔታ ያለውን የገንዘብ ፍሰት ወደ መደበኛ ለማምጣትም ጥረቶች የተደረጉ ሲሆን በተለያየ ጊዜም የወጡ መመሪያዎችም ለዚህ ማመላከቻዎች ናቸው።
በኢትዮጵያ ከባንክ ውጭ ያለው ገንዘብ በቢሊዮኖች እንደሚቆጠር ከዚህ ቀደም በፋይናንስ ዘርፉ የተሰራ ጥናት የሚያሳይ ሲሆን በባለፈው ዓመትም አገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የጥሬ ገንዘብ እጥረት (ሊኩዊዲቲ) አጋጥሟት ነበር።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክም ይህንንም ችግር ለመፍታት አንዳንድ ጊዜያዊ መፍትሄዎችን መውሰዱ የሚታወስ ነው።
የውጭ ምንዛሪ እጥረትና የዋጋ ግሽበት የለውጡ ዋነኛ መሰናክል ሆነው ቆይተዋል በማለትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለምጣኔ ሀብቱ መዳከም ምክንያት ያሉትን ጠቁመዋል።
ኢትዮጵያ በዚህ ወቅት የገንዘብ ኖት ለውጥ ማድረጓም በከፍተኛ ሁኔታ ከዘርፉ ውጭ ያለውን ገንዘብ ወደ መደበኛ የገንዘብ እንቅስቃሴ ሂደት ለማምጣትም ይረዳታል በማለት የዘርፉ ባለሙያዎች ይናገራሉ።
የብሔራዊ ባንክ ገዢው ዶ/ር ይናገር ደሴ በበኩላቸው መንግሥት የገንዘብ ለውጥ ማድረግ ካስፈለገው ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ከገንዘብ ጋር የተገናኙ ሕገ-ወጥ ዝውውሮችን ለመግታት እንደሆነ በብሔራዊው ቴሌቪዥን ቀርበው አስረድተዋል።
የአገሪቱ ኢኮኖሚ በብዛት በጥሬ ገንዘብ ግብይት የሚካሄድበት መሆኑን የጠቀሱት ዶ/ር ይናገር ከባንኮች ውጭ ያለው ጥሬ ገንዘብ ከፍተኛ መሆኑን ተናግረዋል።
"አብዛኛው ኅብረተሰባችን ከባንክ ውጭ ነው ግብይት የሚያደርገው በዚህ ምክንያት ብዙ ጥሬ ገንዘብ ከባንክ ውጭ ይገኛል ማለት ነው። በዚህም የጥሬ ገንዘብ እጥረት ባንኮች ላይ ማጋጠም እድሉ ሰፊ ነው።ለ ገቢ አሰባሰብ አመቺ ሁኔታ ይፈጥራል የሚል እምነት ነው ያለን፤ ለአጠቃቀም የተሻለ አገልግሎት ይሰጣል፤ የህትመት ወጪንም በመቀነስ ረገድ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል" ብለዋል።
ከባንክ ውጭ ያለው ጥሬ ገንዘብ በአገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በጎረቤት አገራት ጭምር በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚገኝ ጠቅሰዋል።
"ከባንክ ውጭ የሚገኝ ገንዘብ ደግሞ ለሕገ-ወጥ ተግባራት ሲውል ነው የሚታየው፤ በተለይ በኮንትሮባንድ [ሕገ-ወጥ ንግድ] የተሰማሩ ግለሰቦች ይጠቀሙበታል" ብለዋል።
ዶ/ር ይናገር ከዚህ በተጨማሪ ግለሰቦች ግብር ላለመክፈል ሲሉ ገንዘባቸውን ከባንክ ውጭ የማስቀመጥ ልማድም እየሰፋ መምጣቱን ጠቁመው አሁን ያለውን የገንዘብ ኖት መቀየር አስፈላጊ መሆኑ እንደታመነበት አስረድተዋል።
ከባንክ ውጭ የተጠራቀመ ገንዘብ ጥቅም የለውም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዚህ በኋላም በአውሮፕላን ጣቢያዎችና ድንበሮች እንዲሁም በባንኮች አካባቢ ከፍተኛ ቁጥጥርም ይደረጋል ተብሏል።
የፀጥታ ኃይሎች በሕገወጥ ገንዝብ ላይ ከፍተኛ ቁጥጥር ከማድረግ በተጨማሪ በሕገ ወጥ መንገድ የሚሰበሰብ ገንዘብ ካገኙ እንደሚወርሱም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
ከባንኮች ውጭ ያለው ገንዘብ ወደ ባንኮች ሲመለስም የሂሳብ ደብተር ተከፍቶ ባንኮች ውስጥ እንዲቀመጥ ይደረጋል።

የፎቶው ባለመብት, PMO
ለመሆኑ የብር ኖትን መቀየር እንደ ኮንትሮባንድ እና ሕገ-ወጥ የገንዘብ ዝውውርን እንዴት ሊያስቆም ይችላል?
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ዋሲሁን በላይ ኢትዮጵያ ውስጥ ከባንክ ሥርዓት ውጭ የሚንቀሳቀስ ከ113 ቢሊየን ብር በላይ መኖሩን ይናገራሉ።
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች ያሉት ሲሆን የዋጋ ንረት ከፍተኛ በመሆኑና ባንክ ቤቶች ብር ለሚያስቀምጥ የሚሰጡት ወለድ ዝቅተኛ በመሆኑ ሰዎች ገንዘቤን በእጄ እይዛለሁ የሚል አስተሳሰብ መኖሩን እንደ አንድ ምክንያት ያነሳሉ።
በሌላ በኩል በሙስናና በሌሎች ምክንያቶች "ተቋማትም ግለሰቦችም ሲዘርፉ ስለነበር ነው" ይላሉ።
ለዚህ ንግግራቸውም ከለውጡ በኋላ የተከማቹ በርካታ ገንዘቦች በጆንያ እየታጨቁ እና በመኪና እየተጫኑ ሲዘዋወሩ መያዛቸውን እንደ ምሳሌም ይጠቅሳሉ።
የገንዘብ ኖቶቹ ላይ ለውጥ መደረጉም ሰዎች ገንዘባቸውን ለመቀየር ባንክ በሚሄዱበት ጊዜ፤ በጤናማ የግብይት ሥርዓት ገንዘቡን ማግኘት አለማግኘታቸውን ለማረጋገጥ እድል ይሰጣል ብለዋል ባለሙያው።
በመሆኑም እስካሁን የተሰሩ የሙስና ምንጮችን ለማወቅም ሆነ ከአሁን በኋላ የሚሰሩ ሙስናዎች ላይ ፍራቻ እንዲፈጥር ሊያደርግ እንደሚችልም ተናግረዋል።
በአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የምጣኔ ሀብት መምህር የሆኑት ረዳት ፐሮፌሰር ጉቱ ለገስ ደግሞ ከገንዘብ ጋር ተያይዞ ያሉ ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎችን ለመግታት የብር ኖቶች መቀየር አንዱ እንጂ፤ ብቸኛው መፍትሔ አለመሆኑን ያሰምሩበታል።
ረዳት ፕሮፌሰር ጉቱ "አንድ ነገር ሲተዋወቅ ውጤታማ ለመሆን አለመሆኑ አንዱ ወሳኙ ነገር፤ ተቋማዊ አደረጃጃትና የመተግበር አቅም ነው። ይህ ካልሆነ ግን አዙሪት ነው የሚሆነው" ብለዋል።
መንግሥት ገንዘቡን ከቀየረ በኋላ ሕገ-ወጥ ገንዘብ ይዘዋል ተብለው የሚጠረጠሩ ግለሰቦችና ድርጅቶች የየራሳቸውን እርምጃ መውሰዳቸው እንደማይቀር የጠቆሙት ረዳት ፕሮፌሰሩ፤ መንግሥት ተቋማዊ አደረጃጀቱ ጠንካራ ሆኖ ይሄን ነገር ልብ ብሎ መከታተል እንዳለበት መክረዋል።
አሁን የተወሰደው እርምጃ ቀደም ብለው የተሰሩ ሥራዎች ስላሉ ውጤታማ ይሆናል ተብሎ ይገመታልም ብለዋል።
ነገር ግን "ቀድሞ የነበረው የውጭ ምንዛሬ ጋር ተያይዞ ያለው ሙስናና ደካማ አስተዳደር ካልተስተካከለ ተመልሶ ያው ነው የሚሆነው" ሲሉ አስጠንቅቀዋል።
አዲስ የ200 ብር ኖት ማስገባት ለምን ተፈለገ?
በኢትዮጵያ በቅርብ አመታት ውስጥ የገንዘብ የመግዛት አቅም በከፍተኛ ሁኔታ ያሽቆለቆለ ሲሆን ከዚህም አንፃር ባለ ሁለት መቶ ኖቶች ወደ ገበያው ውስጥ መግባት አስፈላጊ እንደሆነም የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ።
ረዳት ፕሮፌሰር ጉቱ የዋጋ ንረቱ በጣም ከፍተኛ ከመሆኑ የተነሳ በተለያየ ግብይት ሂደት ውስጥ የሚሳተፈው ኅብረተሰብ ብዙ ብር ለመያዝ እየተገደደ መሆኑን በመጥቀስ ያንን ሊያስቀርላቸው እንደሚችል ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ ወደ ኤሌክትሮኒክስ የግብይት ሥርዓት እንዲገቡም እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል። ኢኮኖሚው ሲያድግ ወደዚያ መግባቱ እንደማይቀር በመግለፅ።
አቶ ዋሲሁን በበኩላቸው የገንዘብ ኖት ከፍ እያለ ሲመጣ ገንዘቦች መግዛት አቅማቸው መዳከሙን የሚያመላክት መሆኑን ይናገራሉ።
በምሳሌ ሲያስረዱም "አሁን 5 ብር ዝቅተኛው ገንዘብ እየሆነ ነው። አንድ ብርና ሁለት ብር የሚገዛቸው ነገሮች እየጠፉ ነው። ሰዎች መቶ ብርም ይዘው በፊት የሚገዙትን ያህል እቃ መግዛት አይችሉም፤ በመሆኑም ሰዎች ብዙ የወረቀት ገንዘብ ይዘው ከሚሄድ ያድናቸዋል" ይላሉ።
ነገር ግን ከ20 በመቶ በላይ የዋጋ ንረት በሚመዘገብበት ሁኔታና የ100 ብርና የ200 ብር ልዩነት ብዙም ባለመሆኑ መሆን የነበረት የ500 ወይም የ1000 ብር ኖት ወደገበያው መግባት እንደነበር አቶ ዋሲሁን ሙያዊ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
የገንዘብ መቀየሩን ተከትሎ ምን ሊፈጠር ይችላል?
መንግሥት አሮጌ የብር ኖቶቹን ለመቀየር የሦስት ወር የጊዜ ገደብ አስቀምጧል። የምጣኔ ሀብት ባለሙያው እንደሚሉት ከሆነ አዲሱ መገበያያ ገንዘብ ይፋ መደረጉን ተከትሎ በቀጣይ ሳምንታት ውስጥ ባልተለመደ መልኩ የገንዘብ ዝውውር ሊስተዋል ይችላል።
"ሰዎች አዳዲስ የሒሳብ ቁጥር እየከፈቱም ሊያስቀምጡ ይችላሉ። ጥሬ ገንዘቡን ወደ ባንክ ላለማስገባትም የንብረት ግዥ ሊጧጧፍ ይችላል። መኪና፣ ቤት መግዛት ሊኖር ይችላል" ሲሉ ግምታቸውን አስቀምጠዋል።
በሌላ በኩል በሙስና የተከማቸ አሊያም ከገቢያቸው ጋር የማይመጣጠን ገንዘብ በእጃቸው የያዙ ግለሰቦች፤ የሚመጣባቸውን ጥያቄን በመፍራት በዘመድ አዝማዶቻቸው ስም በርካታ የሒሳብ ቁጥሮችን ሊከፍቱ እንደሚችሉም አመላክተዋል።














