የአውሮፓ ሕብረት 'የኢትዮጵያ ሁኔታ አሳስቦኛል' አለ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የአውሮፓ ሕብረት ሰኞ ባወጣው መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ እንዳሳሰበው አስታውቋል።
የሕብረቱ ምክትል ፕሬዝደንትና የውጭ ጉዳይ ከፍተኛ ተወካይ የሆኑት ጆሴፍ ቦሬል ባወጡት መግለጫ ነው የሕብረቱን አቋም ያንፀባረቁት።
'ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ሁኔታ አሳሳቢ ነው' የሚለው መግለጫው፤ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችና ጎረቤት አገራት ውጥረት ለመቀነስ መጣር እንዳለባቸው አሳስቧል።
መግለጫው አክሎ ሁሉም ቡድኖች "ግጭት ቀስቃሽ ቃላት" መጠቀም ማቆም እንዳለባቸውና ወታደራዊ እንቅስቃሴዎችን መግታት እንዳለባቸው አሳስቧል።
"ይህ መሆን ካልቻለ ግን" ይላል መግለጫው፤ "ይህ መሆን ካልቻለ ግን ጉዳቱ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለቀጣናውም ነው" ይላል።
መግለጫው ብሔራዊ መግባባት ለመፍጠር አገር አቀፍ ውይይቶች እንደሚያስፈልጉ አትቷል። በዚህ ውይይት ላይ ሁሉም የፖለቲካ ተዋናዮች ተሳታፊም እንዲሆኑም ጥሪ አቅርቧል።
ለኢትዮጵያ ሕዝብ መፃዒ ተስፋና ብልፅግና ብሔራዊ መግባባት እንጂ ግጭት መፍትሄ ሊሆን እንደማይችል የምክትል ፕሬዝደንቱ መግለጫ ያትታል።
የአውሮፓ ሕብረት የኢትዮጵያን ለውጥ ለመደገፍ ቁርጠኛ እንደሆኑም ጆሴፍ በመግለጫቸው ተናግረዋል።
የሰብዓዊ መብትና የሕግ የበላይነት መከበር በ2021 [በአውሮፓውያኑ] የሚካሄደው ምርጭ ነፃ፣ ተዓማናኒና ፍትሃዊ እንዲሆን ያግዛል ይላል የሕብረቱ መግለጫ።
ምንም እንኳ የሕብረቱ መግለጫ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉ ፓርቲዎችንም ሆነ የጎረቤት አገራትን ስም ባይጠቅስም በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ገዥ ፓርቲ ሕወሓት መካከል ያለው ውጥረት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተባባሰ መጥቷል።
አልፎም የኤርትራ መንግሥት ባለሥልጣናትና በኢትዮጵያ የኤርትራ ኤምባሲ ሕወሓትን የሚወርፍ መግለጫ ማውጣታቸው ይታወሳል።
በምላሹ የሕወሓት ከፍተኛ አመራር የሆኑት ጌታቸው ረዳ መግለጫውን አጣጥለው በማሕበራዊ ድረ ገፆቻቸው ላይ ፅፈዋል።
ዛሬ ከሰዓቱን ለጋዜጠኞች መግለጫ የሰጡት የትግራይ ክልል አስተዳዳሪ ደብረፅዮን ገብረሚካኤል [ዶ/ር] በበኩላቸው ከፌዴራል መንግሥት ጥቃት ሊሰነዘር ይችላል ሲሉ ተደምጠዋል።
በዚህ ጉዳይ ላይ ምላሽ እንዲሰጡ ቢቢሲ የፌዴራል መከላከለያ ሠራዊትንም ሆነ ሌሎች የመንግሥት አካላትን ለማግኘት ያደረገው ሙከራ አልተሳካም።
ዓለም አቀፉ ክራይሲስ ግሩፕ ባለፈው ሳምንት ባወጣው መግለጫ፤ በማዕከላዊው መንግሥትና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ያለው ውጥረት እንዲረግብ ሁለቱ አካላት ቅድመ ሁኔታዎችን አለዝበው ድርድር እንዲያደርጉ ማሳሰቡ አይዘነጋም።












