ቤንሻንጉል ጉሙዝ፡ በክልሉ የተከሰተው ምንድን ነው?

ከሳምንት በፊት ጀምሮ ማንነታቸው ያልታወቀ የታጠቁ ኃይሎች በተለያዩ በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል አካባቢዎች በፈጸሟቸው ጥቃቶች ቁጥራቸው ያልታወቁ ሰዎች እንደተገደሉና ንብረት ላይም ጉዳት መድረሱን ቢቢሲ ያናገራቸው ነዋሪዎች ገልጸዋል።
በጥቃቱ ጉዳት ከደረሰባቸውና የቤተሰብ አባላቸው ከተገደለባቸው ሰዎች መካከል አንዱ የሆኑት አቶ ኃይሉ አዲሱ አባታቸው በቡለን ወረዳ ውስጥ እንደተገደሉባቸው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
አቶ ኃይሉ እንደሚሉት አባታቸው ከሳምንት በፊት ጳጉሜ 01/2012 ዓ.ም እሁድ ምሽት አንድ ሰዓት አካባቢ ነበር በታጣቂዎቹ የተገደሉት።
ነገር ግን ከአንድ ሳምንት በኋላ እስካሁን ድረስ የአባታቸውን አስከሬን አግኝተው ለመቅበር አለመቻላቸውን በምሬት አስረድተዋል።
እሳቸው እንዳሉት የአባታቸውን አስከሬን ለማግኘት ከጸጥታ አካላት ትብብር ቢጠይቁም "ቆዩ መግባት አልቻልንም" የሚል ምላሽ እየተሰጣቸው እንደሆነ ተናግረዋል።
አባታቸው አቶ አዲሱ ከብቶቻቸውን ከዱር ይዘው ሲመለሱ መንገድ ላይ በታጣቂዎቹ እንደተገደሉ የሚናገሩት አቶ ኃይሉ፤ "ገዳዮቹ ለሚፈጽሙት ግድያ ምንም አይነት ምክንያት እንደሌላቸውና ፍላጎታቸው ምን እንደሆነ አለመታወቁ ነዋሪውን ግራ እንዳጋባ" ጠቅሰዋል።
ጥቃት ፈጻሚዎቹ ሰዎችን ከመግደል በተጨማሪ መኖሪያ ቤታቸውንም እንደሚያቃጥሉና ዘረፋ እንደሚፈጽሙ ነዋሪዎች ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ለደኅንነታቸው ሲሉ ስሜ አይጠቀስ ያሉ ሌላኛው የአካባቢው ነዋሪ ደግሞ ለቀናት የዘለቀው ጥቃት ከመፈጸሙ በፊት በነዋሪው ዘንድ ስጋቶች እንደነበሩ ገልጸው፤ በዚሁ ምክንያትም ቀደም ብለው ቤተሰቦቻቸውን ወደ ሌላ ቦታ ልከው እርሳቸው ቤታቸውን እየጠበቁ መቆየታቸውን ለቢቢሲ ተናግረዋል።
የፈሩት እንዳልቀረ የሚናገሩት እኚህ ግለሰብ እሁድ ጳጉሜ አንድ ግን የታጠቁ ኃይሎች "አካባቢውን ማተራመሳቸውን" እንደሰሙ ወደ ጫካ ሸሽተው ሕይወታቸውን ማትረፋቸው ተናግረዋል።
ነገር ግን ሲጠብቁት የነበረው የቤታቸው ንብረት ሙሉ ለሙሉ እንደተወሰደባቸውና በአካባቢው የሚኖሩ የሌሎች ሰዎች ንብረትም በታጣቂዎቹ መዘረፉን ለቢቢሲ ገልጸዋል።
ነዋሪው ከጥቃቱ ሸሽተው ይትረፉ እንጂ እንደ እሳቸው ዕድለኛ ያልነበሩ የአካባቢው ነዋሪዎች መገደላቸውን ተናግረዋል።
እሳቸው እንዳሉትም የተገደሉ ሰዎችን ብዛት በትክክል ለመናገር ቢቸገሩም ቁጥራቸው ጥቂት የማይባሉ ሰዎች በታጣቂዎቹ ተገድለዋል ብለዋል።
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ውስጥ በታጣቂዎች የሚፈጸሙ ጥቃቶች በተለያዩ ጊዜያት የሚያጋጥሙ ሲሆን ባለፈው ሰሞን የተፈጸመው ግን በቀናት ውስጥ መደጋገሙን እንዲሁም በተለያዩ አካባቢዎች መፈጸሙን ነዋሪዎች ይናገራሉ።
ተመሳሳይ የታጣቂዎች ጥቃት በመተከል ዞን ዲባጢ እና ወንበራ ወረዳዎች ላይ በታጣቂዎች መፈጸሙንና የሰዎች ህይወት መጥፋቱን ቢቢሲ ያነጋገራቸው የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች አመልክተዋል።
ታጣቂዎቹ በቁጥር በርካታ መሆናቸውን የሚገልፁት ነዋሪዎች ከዚህ በፊትም በተለያዩ አካባቢዎች እየተዘዋወሩ ጥቃት መፈፀማቸውን አስታውሰዋል።
በቡለን ወረዳ ጥቃት የደረሰው ጳጉሜን 2/2012 ዓ.ም መሆኑን የሚናገሩት ነዋሪዎች በሁለት ቀበሌ ውስጥ ነዋሪ የሆኑ እና "ከጉሙዝ ተወላጅ ውጪ" የሆኑ ሰዎች ላይ ጥቃት መፈፀሙን ተናግረዋል።
ወንበራ ላይ ከጳጉሜን 2/2012 ዓ.ም በፊት ሦስት ሰዎች መገደላቸውን እንዲሁም አራት የሚደርሱ ሰዎች ደግሞ በታጣቂዎቹ ታግተው ወዳልታወቀ ስፍራ መውሰዳቸውን ተናግረዋል።
ወንበራ ላይ ከዚህ ቀደምም ታግተው የተወሰዱ ሴቶች መኖራቸውን ያስታወሱት ነዋሪዎቹ እነሱም እስካሁን የት እንደደረሱ እንደማይታወቅ ገልጸዋል።
ቡለን ላይ ከታገቱት መካከል ሁለቱ ተለቅቀዋል የሚባል ወሬ ቢሰማም እስካሁን ድረስ ግን ከተማ አለመድረሳቸውን ነዋሪዎቹ ጨምረው ለቢቢሲ ተናግረዋል።
በክልሉ በተለያዩ ቦታዎች በተፈጸሙ የታጣቂዎች ጥቃት ምን ያህል ሰዎች እንደተገደሉና በንብረት ላይ የደረሰ ውድምትን በተመለከተ የተለያዩ አሃዞች ቢጠቀሱም፤ ቢቢሲ ትክክለኛውን ቁጥር ለማወቅ ያደረገው ጥረት አልተሳካለትም።
በነዋሪዎች ግምት መሰረት ግን በጥቃቱ አስከ 50 የሚደርሱ ሰዎች መሞታቸው ሲገለልጹ፤ የወደመውና የተዘረፈው ንብረት መጠንን ለማወቅ እንዳልቻሉ ተናግረዋል።
በተለያዩ ቀናት ሲፈጸም የነበረውን ጥቃት ተከትሎም የክልሉ ልዩ ኃይል እና የመከላከያ ሠራዊት ሰኞ ዕለት ወደ አካባቢዎቹ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ቢቢሲ ከሰኞ ጀምሮ ከክልሉ ከፍተኛ አመራሮችና የጸጥታ ኃላፊዎች ስላለው ሁኔታ ዝርዝር ማብራሪያ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም።
የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልላዊ መንግሥት ኮሚኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዛሬ እንዳለው በመተከል ዞን አንዳንድ አካባቢዎች "የተፈጠረውን የጸጥታ ችግር የማረጋጋትና የሕግ የበላይነት የማስከበር ሥራ" በመከላከያ ሠራዊት፣ በፌዴራል ፖሊስና የክልሉ የጸጥታ ኃይል እየተከናወነ መሆኑን አመልክቷል።
ጨምሮም በዞኑ ቡለንና ወምበራ ወረዳ ውስጥ በሚገኙ አንዳንድ ቀበሌዎች "በፀረ ሠላም ኃይሎች የተፈጠረው የጸጥታ ችግር" ወደ አንጻራዊ ሠላም በመመለስ ላይ መሆኑን የክልሉን ሠላም ግንባታና ጸጥታ ቢሮን ጠቅሶ ገልጿል።
ቢሮው ኃላፊ አቶ አበራ ባያታ ጥቃቱ በተፈጸመባቸው አካባቢዎች የንጹሃን ዜጎች ህይወት መጥፋቱን ቢገልጹም፤ የሟቾችን ቁጥርም ሆነ የደረሰው የጉዳት መጠን ትክክለኛ መረጃ በመጣራት ላይ በመሆኑ የደረሰውን ጉዳት መጠን ከመግለጽ ተቆጥበዋል።














