ትግራይ፡ የተያዙና የተገደሉ የህወሓት አመራሮችና ወታደራዊ መኮንኖች ዝርዝር ይፋ ሆነ

የፎቶው ባለመብት, EBC
የኢትዮጵያ ፈደራል መንግሥት በትግራይ ክልል ሕግ ማስከበር ባለው ዘመቻ ውስጥ በቁጥጥር ስር የዋሉና ተገደሉ ወታደራዊ መኮንኖችን ስም ዝርዝር የአገር መከላከያ ሠራዊት ይፋ አደረገ።
የአገሪቱ መከላከያ ሠራዊት ስምሪት መምሪያ ኃላፊ ብርጋዴል ጄኔራል ተስፋዬ አያሌው ለአገር ውስጥ መገናኛ ብዙሃን እንደገለጹት የመከላከያ ሠራዊትና የፌዴራል ፓሊስ በጋራ በወሰዱት እርምጃ ነው መኮንኖቹ የተያዙትና እርምጃ የተወሰደባቸው።
ኃላፊው እንዳሉት በርካታ ከህወሓት አመራሮች ጋር የተሰለፉ ወታደራዊ መኮንኖች እና የልዩ ኃይል አባላት እጃቸውን መስጠታቸውን ጠቅሰው እጅ ለመስጠት ፈቃደኛ ያልሆኑት "መደምሰሳቸውን" ገልጸዋል።
ብርጋዴር ጄነራል ተስፋዬ እንዳሉት ጥቅምት 30/2013 በሰሜን ምዕራብ ኢትዮጵያ ከ600 በላይ ሰዎች ተገድለውበታል የተባለውን የማይካድራውን ጭፍጨፋ መርተዋል የተባሉትን ኮሎኔል የማነ ገብረሚካኤልን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖች መገደላቸውን አመልክተዋል።
በተጨማሪ መገደላቸው የተገለጸው መኮንኖች ኮሎኔል ዓለም ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል ቢንያም ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል አምባዬ፣ ኮሎኔል ማዕሾ፣ ኮሎኔል ይርጋ ስዩም፣ ኮሎኔል ሃዱሽ፣ ኮሎኔል አጽብሃ፣ ኮሎኔል ተስፋዬ ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል ዮሐንስ ካልአዩ፣ ኮሎኔል ተክለእግዚአብሄርና ሌተናል ኮሎኔል ብርሃኔ ቶላ ናቸው።
ጨምረውም ሌሎች በስም ያልተገለጹ አራት ኮሎኔሎች እንዲሁም ሁለት የዞን አመራሮች መገደላቸውን አስታውቀዋል።
ተደብቀው እየተፈለጉ ያሉ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችና አባላትን መከላከያ ሠራዊትና ፖሊስ እየተከታተሏቸው መሆኑን ገልጸው፤ ለዚህም የተለያዩ አካባቢዎችን ላይ ፍተሻና አሰሳ እያደረጉ መሆኑን የገለፁት ብርጋዴር ጄነራሉ "ፍለጋው ከሰፊ ወደ ጠባብ ቦታ መጥቷል" ማለታቸው ተዘግቧል።
እየተካሄደ ባለው ፍተሻ የቡድኑ አመራሮች በየዋሻውና በየቤተክርስቲያኑ ተደብቀው መገኘታቸውንና የቤተክርስቲያን አባቶችን አልባሳት በብሰው የተገኙ መኖራቸውንም ጠቅሰው፤ የተደበቁ የህወሓት አመራሮች ከማንም ጋር የሚገናኙበት ዕድል የላቸውም በማለት ተናግረዋል።
እጅ ከሰጡ የሕወሓት አመራሮች መካከልም የቀድሞ የትራንስፖርት ሚኒስትር ሚኒስትር ዴኤታ ወይዘሮ ሙሉ ገብረ እግዚአብሔር፣ የትግራይ ክልል ኦዲት ኃላፊ የነበሩት ሃዱሽ ዘውገ ገዛኸኝ፣ የክልሉ ልማት ስልጠና ኃላፊ የነበሩት አቶ ሰለሞን ህሉፍ ንጉሤ እንዲሁም የክልሉ ጠቅላይ አቃቤ የነበሩት አቶ ኪዳነማሪያም ገብረክርስቶስ ፋሲል ይገኙበታል።
በተጨማሪም የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት አቶ ባህታ ወልደሚካኤል፣ የክልሉ ኢኮኖሚ ቢሮ የልማት እቅድ አስተባባሪ አቶ ሀጎስ ወልደኪዳን ገብረማሪያምና የመቀለ ዩኒቨርሲቲ የሕግ መምህር የሆኑት አቶ ገብረአምላክ ይኸብዮ እንዳሉበት ወታደራዊ ኃላፊው ገልፀዋል።
ከዚህ ባሻገር ደግሞ ዶክተር ዓለም ብርሃኔ፣ ኮሎኔል መብርሃቱ ገብረመድኅን፣ ኮሎኔል ሃዱሽ ሃጎስ፣ ኮሎኔል ህሉፍ ተ/መድኅን፣ ሌተናል ኮሎኔል ተክለ ህይወት አሰፋ እጃቸውን ከሰጡ መካከል እንደሚገኙበት ብርጋዴል ጄኔራሉ በመግለጫቸው ላይ አመልክተዋል።
ከወታደራዊና ከሲቪል አመራሮች በተጨማሪም በርካታ ቁጥር ያላቸው የሚሊሻና ልዩ ኃይል አባላት እጃቸውን መስጠታቸውንም አብራርተዋል።
እስካሁን ድረስ የክልሉ ርዕሰ መስተዳደር የነበሩት ዶ/ር ደብረፂዮንም ሆኑ ሌሎች ከፍተኛ ሹማምንቶች ያሉበት ሁኔታ በዚህ መግለጫ ላይ አልተጠቀሰም።
ከጥቂት ሳምንት በፊት የመከላከያ ሠራዊቱ ከፍተኛ የህወሓት አመራሮች ያሉበትን ለጠቆመ የ10 ሚሊዮን ብር ሽልማት ማዘጋጀቱን መግለጹ ይታወሳል።
መንግሥት በቁጥጥር ስር ውለዋል ወይም ተገድለዋል ያላቸውን የህወሓት ወታደራዊ መኮንኖችና ሲቪል አመራሮችን በተመለከተ ከቡድኑም ሆነ ከሌላ ገለልተኛ ወገን የተሰማ ነገር የለም።
የክልሉ ዋና ከተማ መቀለ በፌደራል መንግሥቱ ሠራዊት ቁጥጥር ስር ስትገባ የህወሓት አመራሮች ውጊያውን እንደሚቀጥሉ ከገለጹ በኋላ ስላሉበት ሁኔታና ወቅታዊ ጉዳዮች በይፋ የሰጡት መግለጫ የለም።
አሁን መገደላቸው እንዲሁም እጃቸውን መስጠታቸው ከተገለፁ የህወሓት አባላት ሌላ የቀድሞዋን የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባዔ ኬርያ ኢብራሂም ጨምሮ ጉዳያቸው በፍርድ ቤት እየታየ የሚገኙ የተለያዩ ከፍተኛ ወታደራዊ መኮንኖችና የቀድሞ ባለሥልጣናት ይገኛሉ።
ጥቅምት 24/2013 ዓ.ም ምሽት የህወሓት ኃይሎች በሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት መፈፀማቸውን ተከትሎ በትግራይ ክልል ወታደራዊ ግጭት ተቀስቅሶ ክልሉን ይመራ የነበረው ህወሓት ከሥልጣን መወገዱ ይታወሳል።
በትግራይ ክልል ከተከሰተው ቀውስ ጋር በተያያዘ የፌደራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በ167 ሰዎች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣቱን ይፋ አደረጎ ነበር።
ከዚህ በተጨማሪም የፌደራል ፖሊስ ኮሚሽን ህወሓትን በበላይነት በመምራት፣ በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል ፈጽመዋል ያላቸውን ግለሰቦች አድኖ በመያዝ ለሕግ ለማቅረብ ተፈላጊ ናቸው ባላቸው የህወሓት ከፍተኛ አመራሮችንና አባላትን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሚያስችል የፍርድ ቤት የመያዣ ትዕዛዝ በ96 ግለሰቦች ላይ ማውጣቱን አስታወቆ ነበር።
በተጨማሪም የፌደራል ፖሊስ በአገር ክህደት እና ትግራይ ውስጥ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ አድርገዋል ብሎ የጠረጠራቸውን ከአርባ በላይ የቀድሞ ከፍተኛ መኮንኖች ላይ የመያዣ ትዕዛዝ ማውጣቱን አስታወቋል።
እነዚህ የቀድሞው የአገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም የነበሩት ሜጀር ጄኔራል ጻድቃን ገብረተንሳይን ጨምሮ፣ ከፍተኛ የቀድሞ የኢትዮጵያ አየር ኃይል፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አመራሮች የተጠረጠሩትም በአገር ክደትና በሠራዊት አባላት ላይ በተፈጸመ ወንጀል መሆኑ በወቅቱ ተገልጿል።














