ትግራይ ፡ በመንግሥት ከተያዙት የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አምስቱ

አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) እና አቶ ስብሐት ነጋ

የፎቶው ባለመብት, SOCIAL MEDIA

የምስሉ መግለጫ, አቶ አባይ ወልዱ፣ ወ/ሮ ቅዱሳን ነጋ፣ አብረሃም ተከስተ (ዶ/ር)፣ ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) እና አቶ ስብሐት ነጋ

በትግራይ ክልል የተከሰተውን ወታደራዊ ግጭት ተከትሎ በአገርና በመንግሥት ተቋማት ላይ ከባድ ወንጀል ፈጽመዋል ተብለው የተጠረጠሩ ግለሰቦች ላይ ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግና የፌደራል ፖሊስ በበርካታ የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች ላይ የእስር ትዕዛዝ ማውጣታቸው ይታወሳል።

በተጠርጣሪዎቹ ላይ ለወጣው የመያዣ ትዕዛዝ እንደ ዋነኛ ምክንያት የተጠቀሱት ህወሓትን በበላይነት በመምራት በትግራይ ክልል በሚገኘው በአገር መከላከያ ሠራዊት የሰሜን ዕዝ ላይ ጥቃት በመፈፀም፣ የአገር ክህደት ወንጀል በመፈጸም፣ የመከላከያ ሠራዊትና የፖሊስ አባላት እንዲታገቱ በማድረግ በሚሉ ወንጀሎች ተጠርጥረው ነው።

ፌደራል መንግሥቱ ኃይሎች ከሦስት ሳምንታት ወታደራዊ ዘመቻ በኋላ የክልሉን መዲና ከተቋጣጠረ በኋላ መንግሥት ለግጭቱና ለተፈጠረው ለቀውስ ዋነኛ ተጠያቂ ናቸው ያላቸውን የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በቁጥጥር ስር እያዋለ ነው።

እስካሁን በመንግሥት መያዛቸው ይፋ ከተደረጉት ግለሰቦች መካከል አምስቱን እነሆ፡

አቶ ኣባይ ወልዱ

አቶ አባይ በ1969 ዓ.ም መጨረሻዎቹ ነበር ወደ ህወሓት የትጥቅ ትግል የተቀላቀሉት።

ታላቅ ወንድማቸው አቶ አውዓሎም ወልዱ ከህወሓት 11ዱ የትጥቅ ትግል መስራቾች አንዱ ሲሆኑ፤ የድንበር ጦርነቱ እስከተጀመረ ድረስ በኤርትራ የኢትዮጵያ አምባሳደር የነበሩ ናቸው።

ሆኖም በ1993 በድርጅቱ ውስጥ በተፈጠረ መከፋፈል ሁለቱም ወንድማሞቹ ለሁለት ተለይተው ከሁለቱ አንጃዎች አንጻር ቆመው ነበር። አቶ አውዓሎም ከድርጅቱ ከተባረሩት መካከል ነበሩ።

አቶ አባይ ወልዱ ለረዥም ግዜ የትግራይ ክልል ምክትል መስተዳደር ሆነው ከቆዩ በኋላ በ2002 ዓ.ም የክልሉ ርዕሰ መስተዳደርነትን ከአቶ ጸጋይ በርሀ ተረክበው እስከ 2011 ዓ.ም አገልግለዋል።

እንዲሁም ደግሞ ድርጅቱን ለረዥም ጊዜ የመሩት ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በ2004 መጨረሻ ድንገተኛ ሕልፈት ተከትሎ እስከ 2009 የህወሓት ሊቀመንበር ሆነው አገልግለዋል።

አቶ አባይ ወልዱ የኢህአዴግ ሥራ ፈጻሚ አባልም የነበሩ ያገለገሉ ሲሆን ኋላ ላይ በህወሓት 13ኛ ጉባኤ ላይ ተገምግመው ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ተደርጓል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳደር ሆነው ከመመረጣቸው ቀደም ብለው የክልሉ ማዕከላዊ ዞን አስተዳደር ከዚያም የክልሉ የግብርና ቢሮ ኃላፊ ሆነው ሰርተዋል።

አቶ ኣባይ ሁለተኛ ድግሪ ያላቸው ሲሆን ኢሮብኛ፣ አፋርኛ፣ ትግርኛ፣ አማርኛና እንግሊዝኛ ቋንቋዎችን አቀላጥፈው እንደሚናገሩ ይነገራል።

አቶ አባይ ከድርጅቱ ሊቀ መንበርነትና ከክልሉ ርዕሰ መስዳደርነት ተነስተው በደብረጽዮን ገ/ሚካኤል (ዶ/ር) ነበር የተተኩት።

ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ

የአቦይ ስብሐት ነጋ ታናሽ እህት ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ በ1970 ዓ.ም መጨረሻ ላይ ህወሓትን ከተቀላቀሉት ቀደምት ሴት ታጋዮች መካከል አንዷ ናቸው።

በትጥቅ ትግል ወቅት ብዙ ጊዜ 'ክፍለ ሕዝብ' ተብሎ በሚጠራው የድርጅቱ የሕዝብ ቅስቀሳ ክፍል የሰሩ ሲሆን በተጨማሪም የታጋይ ሴቶች ማኅበር ሊቀመንበርም ሆነው ለረዥም ግዜ እንደሰሩ ይነገራል።

የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ሆነው የተመረጡት ከደርግ ውድቀት በኋላ በ1987 ዓ.ም ነው።

ወይዘሮ ቅዱሳን የመቀለ ከንቲባ ሆነው የሰሩ ሲሆን ቀጥለው የትግራይ ክልል ምክር ቤት አፈጉባኤ ሆነው ለበርካታ ዓመታት አገልግለዋል። ወይዘሮ ቅዱሳን ነጋ ጥቅምት 12 ቀን 2011 ዓ.ም ነበር በክብር ከኃላፊነታቸው የተሰናበቱት።

በ1993 ዓ.ም በህወሓት ውስጥ በተፈጠረው መከፋፈል ወቅት ከባለቤታቸው አቶ ጸጋይ በርሀ ጋር አቋማቸውን ቀይረው ከጠቅላይ ሚኒስትር መለስ ከወገኑት መካከል ናቸው።

አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር)

አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) ህወሓት/ኢህአዴግን ከተቀላቀሉት አዲሱ ትውልድ አመራሮች መካከል የሚመደቡ ሲሆን፤ የአገሪቱ የገንዘብና ኢኮኖሚ ልማት ሚኒስትር ዲኤታ ሆነው አገልግለዋል።

እንዲሆም ደግሞ ባለፉት ሁለት ዓመታት በኢህአዴግና በአገሪቱ ውስጥ ለውጥ ከተደረገ በኋላ ወደ ትግራይ ሄደው ምክትል ርዕሰ መስተዳደርና የፋይናንስና ልማት ቢሮ ኃላፊ ሆኖው ሰርተዋል።

አብርሃም ተከስተ (ዶ/ር) የህወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴና ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው።

ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር)

በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ የትራንስፖርት ቢሮ ኃላፊ የነበሩት ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳነ (ዶ/ር) ባለፈው ዓመት በተደረገ ሹም ሽር ወቅት ከፌዴራል መንግሥት የኃላፊነት ቦታዎች ከተነሱ የህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል አንዱ ነበሩ።

ሰለሞን (ዶ/ር) በአዲስ አበባ ከተማ ከነበራቸው ኃለፊነት ከተነሱ በኋላ የትግራይ ክልል ከተማ ልማትና የፋይናንስ ኃላፊ ሆነው ሲያገለግሉ ቆይተዋል።

ኢንጂነር ሰለሞን በህወሓት ውስጥ ካሉ ጥቂት ወጣት አመራሮች መካል አንዱ ሲሆኑ የድርጅቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ናቸው።

አቶ ስብሐት ነጋ

ከቀደምት የህወሓት ታጋዮች መካከል አንዱና ድርጅቱ በትግል ላይና በመንግሥት ሥልጣን ላይ በቆየበት ጊዜ ከፍተኛ ተጽእኖና ተደማጭነት የነበራቸው አመራር ነበሩ።

ከድርጅቱ ባሻገር ኤፈርት ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆን የሠሩ ሲሆን የኢትዮጵያ የውጭ ግንኙነት ስትራተጂያዊ ጥናት ተቋምን ዋና ዳይሬክተር ሆነው ሰርተዋል።

ከባላባት ቤተሰብ የወጡት የ86 ዓመቱ አዛውንት አቦይ ስብሐት ነጋ መምህር፣ የመንግሥት ሠራተኛ፣ ታጋይ፣ ህወሓትን ለአስር ዓመታት በሊቀመንበርነት የመሩ መስራች ናቸው።