ትግራይ ፡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህወሓትን ሕጋዊ ሰውነት ሰረዘ

የፎቶው ባለመብት, TPLF FACEBOOK
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የህዝባዊ ወያነ ሓርነት ትግራይን (ህወሓት) ሕጋዊ ሰውነት መሰረዙን አስታወቀ።
ቦርዱ እዚህ ውሳኔ ላይ የደረሰው ህወሓት በአመጻ ተግባር ላይ መሰማራቱን በተመለከተ ለማጣራት በፓርቲው የተሰጡ መግለጫዎችንና "በይፋ የሚታወቁ ጥሬ ሃቆችን በማቅረብ ፓርቲው ኃይልን መሠረት ያደረገ የአመጻ ተግባር ላይ መሣተፉን" በማረጋገጡ መሆኑን ገልጿል።
በዚህ መሠረትም ቦርዱን ሕጋዊ ሂደቶችን በመከተል "የፓርቲውን ሕጋዊ ሰውነት ሰርዞታል" በማለት የፓርቲው ኃላፊዎች በፓርቲው ስም መንቀሳቀስ እንደማይችሉም ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ጨምሮም ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ በፓርቲውና በፓርቲው አመራሮች ላይ በሚያደርገው ምርመራ የሚገኙ በህወሓት ስም የተመዘገቡ ተንቀሳቃሽና የማይንቀሳቀስ ንብረቶችን በተመለከተ ያገኘውን ዝርዝር መረጃ እንዲያሳውቀው ጠይቋል።
በዚህም መሠረት የፓርቲው ንብረት ተጣርቶ ዕዳ ካለበት ለዕዳው መሸፈኛ እንዲውል፤ እዳውን ሸፍኖ የሚተርፍ ንብረት ከተገኘ ቀሪው ገንዘብና ንብረት ለሥነ ዜጋና መራጮች ትምህርት እንዲውል ቦርዱ ወስኗል።
የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ እንዳለው፤ ፓርቲው መልስ የመስጠት እድል እንዲያገኝ በሚል በፓርቲውና በቦርዱ መካከል አገናኝ በመሆን ይሰሩ የነበሩት ያላቸውና በስም ያልተቀሳቸውን የፓርቲውን የአዲስ አበባ ቢሮ የቀድሞ ተወካይ ለማነጋገር ጥረት ያደረገ መሆኑን ገልጾ "ተወካዩም ፓርቲውን መወከል እንደማይችሉ ገልጸዋል" ብለዋል።
ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በህወሓት ላይ ካስተላለፈው ውሳኔ በተጨማሪ ሦስት በትግራይ ውስጥ የሚንቀሳቀሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሕገወጥ ምርጫ ላይ በመሳረፍና በአመጽ ተግባር ላይ ተሰማርተዋል በሚል መረጃ መሠረት ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
ህወሓት ከ17 ዓመታት የትጥቅ ትግል በኋላ ወታደራዊውን መንግሥት ከጣለ በኋላ ኢህአዴግ የተባለውን የአራት ፓርቲዎች ግንባር በበላይነት መስርቶ አገሪቱን ለሦስት አስርት ዓመታት ለሚጠጋ ጊዜ ሲመራ መቆየቱ ይታወሳል።
በህወሓት የበላይነት ሲመራ በነበረው የኢትዮጵያ መንግሥት ላይ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ሕዝባዊ ተቃውሞ እያየለ በመጣበት በ2010 ዓ. ም. ላይ በወሰደው የለውጥ እርምጃ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ አህመድ ወደ ስልጣን ከመጡ በኋላ ህወሓት ቀደም ሲል በመንግሥት ላይ የነበረውን የበላይነት ሙሉ ለሙሉ ማጣቱ ይታወሳል።
ህወሓት ዋነኛ አባል የነበረበት አውራው ፓርቲ ኢህአዴግ በጠቅላይ ሚኒስትሩ መሪነት ከስሞ ብልጽንና የተሰኘው ፓርቲ ሲመሰረት ቀሪዎቹ የግንባሩ አባላት ወደ አዲሱ ፓርቲ ሲጠቃለሉ ህወሓት ከውህዱ የብልጽግና ፓርቲ እራሱን አግልሎ ከጠቅላይ ሚኒስትሩና ከፌደራል መንግሥቱ ጋር ውዝግብ ውስጥ ገብቶ ቆይቶ ነበር።
ባለፈው ዓመት ሊካሄድ ታስቦ የነበረው አገራዊና ክልላዊ ምርጫ በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለሌላ ጊዜ እንዲሸጋገር ሲደረግ ህወሓት በምርጫ ቦርድና በፌደራል መንግሥቱ እውቅናን ያላገኘ ክልላዊ ምርጫ አካሂዶ ሙሉ በሙሉ ሊባል የሚያስችለውን የክልሉን ምክር ቤት ወንበር ማሸነፉ ይታወሳል።
ከዚህ ምርጫ በኋላ ከፌደራል መንግሥቱ ጋር የነበረው የተበላሸ ግንኙነት ይበልጡኑ እየተካረረ ከሄደ በኋላ ጥቅምት ወር ማብቂያ ላይ በትግራይ ክልል በነበረው የሰሜን ዕዝ ላይ የተሰነዘረውን ጥቃት ተከትሎ የፌደራል መንግሥቱ ባካሄደው ወታደራዊ ዘመቻ ህወሓት ከክልሉ አስተዳዳሪነት ተወግዷል።
በክልሉ በነበረው የፌደራሉ ሠራዊት ላይ ጥቃት እንዲፈጸምና ግጭት እንዲቀሰቀስ በማድረግ የህወሓት አመራሮች ተጠያቂ ሆነው በፌደራል ፖሊስና በጠቅላይ ዐቃቤ ሕግ የፍርድ ቤት የእስር ትዕዛዝ ወጥቶባቸው እየተፈለጉ ይገኛሉ።
ከእነዚህም መካከል ጥቂት የማይባሉት የህወሓት ፖለቲካዊና ወታደራዊ አመራሮች በቁጥጥር ስር ሲውሉ ሌሎች ደግሞ እርምጃ እንደተወሰደባቸው የአገሪቱ ሠራዊት አሳውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ቦርዱ በትግራይ ክልል ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ሦስት ፓርቲዎች ስለእንቅስቃሴያቸው ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ትዕዛዝ ሰጥቷል።
በዚህም ሠረት ብሔራዊ ባይቶ አባይ ትግራይ (ባይቶና) እና ሳልሳይ ወያነ ትግራይ (ሣወት) ባለፈው ዓመት ማብቂያ ላይ ሕገ ወጥ በተባለው ምርጫ ላይ በመሳተፍና የፓርቲዎቹ አመራሮች በአመጽ ተግባር ላይ በመሰማራታቸውን የሚያመለክት መረጃ በመገኘቱ ማብራሪያ እንዲያቀርቡ ታዘዋል።
በተጨማሪም ዓሲምባ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ (ዓዴፓ) በኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በምዝገባ ሂደት ላይ እያለ በትግራይ ክልል በተካሄደው የተናጠል ምርጫ ላይ ስለመሳተፉ ማብራሪያ እንዲያቀርብ መታዘዙ ተገልጿል።
















