ህወሓት ክልላዊ ምርጫ ቢያከናውን "ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንም" ወ/ት ብርቱኳን

ብርቱኳን ሚደክሳ

የፎቶው ባለመብት, MICHAEL TEWELDE

የትግራይ ክልልን የሚያስተዳድረው ህወሓት በክልሉ ምርጫ ለማካሄድ የሚያስችል የሕግ ድጋፍ እንደሌለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ገለጹ።

ህወሓት ለቀናት ሲያደርግ የነበረውን ስብሰባ ካጠናቀቀ በኋላ ባወጣው መግለጫ ላይ መንግሥት የሥራ ዘመኑን በማራዘም ምርጫ ለማካሄድ ያቀረበውን አማራጭ በመቃውም፤ በክልል ደረጃ ምርጫ ለማካሄድ ዝግጅት አደርጋለሁ ማለቱ ተከትሎ ነው ሰብሳቢዋ ይህንን ያሉት።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ የሆኑት ወ/ት ብርቱኳን ሚደቅሳ ይህንን በተመለከተ "የክልሉ መንግሥትም ሆነ ክልሉን ሚያስተዳድረው ፓርቲ ምርጫ ማካሄድ ሕጋዊ አሆንም" ሲሉ ለብሔራዊው ቴሌቪዥን ኢቢሲ ተናግረዋል።

ህወሓት ምርጫውን በክልል ደረጃ ለማካሄድ ስለመወሰኑ ለብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለማሳወቁን ወ/ት ብርቱኳን "ለእኛ በይፋ የደረሰን ነገር" የለም በማለት አስረድተዋል።

"ክልላዊ ምርጫውን ለማካሄድ አስበው ከሆነ ትክክለኛ አካሄድ አይሆንም። ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንም" ያሉት የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢዋ፤ በሕገ-መንግሥቱ አንቀጽ 102 የተቋቋመው እርሳቸው የሚመሩት ምርጫ ቦርድ በፌደራል፣ በክልል እና በቀበሌ ደረጃ የሚካሄዱ ምርጫዎችን የማስፈጸም ብቸኛ ስልጣን የተሰጠው መሆኑን ጠቅሰዋል።

ከዚህ ውጪ የክልል መንግሥታትም ሆኑ የፌደራል አስፈጻሚ አካል ተስቶ ምርጫን በተመለከተ ውሳኔ ቢያስተላልፍ ሕገ-መንግሥታዊ አይሆንምም ብለዋል።

ወ/ት ብርቱኳን ከአጠቃላይ ምርጫ በተለየ ጊዜ የአንድ አካባቢ ምርጫ ሊካሄድ እንደሚችል ግን ጠቁመዋል። እንደ ምሳሌም፤ ከዚህ ቀደም በሶማሌ ክልል አብዛኛው ድምጽ ሰጪ በኑሮ ዘያቸው ምክያት በድምጽ መስጫ አካባቢ የማይገኙበት ሁኔታ ተፈጥሮ እንደነበረ በማስታወስ ከአጠቃላይ ምርጫ በኋላ በክልሉ ምርጫ እንደተከናወነ አስታውሰዋል።

መንግሥት የምርጫ ጊዜን በማራዘም ምርጫውን ማካሄድ ያስችላሉ ያላቸውን አራት አማራጮች ማቅረቡ ይታወሳል።

ከቀረቡት አማራጮች መካከል ደግሞ ዛሬ ረፋድ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ ሚለውን አማራጭ አጽድቋል።

line

ህወት ምን አለ?

የህወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ከሚያዝያ 23-25 በክልሉ እና በአገራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን ፓርቲው በፌስቡክ ገጹ ላይ አስታውቋል።

መንግሥት ምርጫውን በቀጣይ ለማካሄድ ካስቀመጣቸው አመራጮች አንዱ የሕገ-መንግሥት ትርጓሜ መጠየቅ የሚለው አንዱ ነው። ህወሐት በመግለጫው "የብልፅግና ፓርቲ ሕገ-መንግስቱን ለመተርጐም በሚል ሰበብ የጀመረውን ገሀድ የወጣ እንቅስቃሴ በአስቸኳይ እንዲያቆም" ሲል ጠይቋል።

ህወሐት የትግራይ ህዝብ በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ራስን በራስ የማስተዳደር መብት እንዳለው በማስታወስ፤ ለትግራይ ህዝብ ሙሉ እውቅና ከሚሰጡ የፖለቲካ ሃይሎች ጋር በመሆን ክልላዊ ምርጫን ለማካሄድ ዝግጅት እንዲደረግ ውሳኔ ተላልፏል ብሏል።

ድምጽ መስጫ ኮሮጆ

የፎቶው ባለመብት, ZACHARIAS ABUBEKER

ለመሆኑ ህወት የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላል?

ህወሓት ምርጫ የማይካሄድ ከሆነ በክልል ደረጃ ምርጫ እንዲካሄድ ዝግጅት አደርጋለሁ ብሏል።

በእርግጥ የትግራይ ክልል የራሱን ምርጫ ማካሄድ ይችላል?

ዶ/ር አደም ካሴ በኔዘርላንድስ የአስተዳደር እና ዲሞክራሲ አማካሪ ናቸው። ምርጫን የማካሄድ፣ የምርጫ ሕግን የማውጣት፣ የወጣውን ደግሞ ማስተዳደር ሥልጣን ያለው የፌደራሉ መንግሥቱና ምርጫ ቦርድ ነው ሲሉ ይናገራሉ።

ከዚያ ውጪ የህወሐት አመራሮች ሕጉን ተከትለው ካልተቃወሙ በስተቀር በራሳቸው ዝም ብሎ መሄድ ስልጣኑም የላቸውም ይላሉ።

በዚህ ሃሳብ የሚስማሙት ደግሞ የሕግ አማካሪው አቶ ኤፍሬም ታምራት ናቸው። አቶ ኤፍሬም "ምርጫን በሚመለከት ሊጠሩ የሚገቡ ነጥቦች አሉ ብዬ አስባለሁ" ካሉ በኋላ ምርጫ በዋናነት አላማው ዜጎች በመሰረታዊ ጉዳዮች ላይ ራሳቸው በቀጥታ ወይንም በተወካዮቻቸው አማካኝነት የመሳተፍ መብት ከሚለው እሳቤ መመንጨቱን ያስረዳሉ።

በዚህም የተነሳ የምርጫ ሥርዓት መዘርጋቱን፣ ዜጎችም መምረጥና የመመረጥ መብት እንደሚኖራቸው ይገልፃሉ።

"መንግሥት የሕዝቦች ፈቃድ ነው ስለሚባል ዜጎችን በመምረጥና በመመረጥ ማሳተፍ ብቻ ሳይሆን ምርጫው ነፃና ገለልተኛ መሆን አለበት" የሚሉት አቶ ኤፍሬም፤ በዚህም የተነሳ በሕገ መንግሥቱ ምርጫ ቦርድ ነጻና ገለልተኛ ሆኖ መቋቋሙን ይናገራሉ።

"ይህ ምርጫ ቦርድ የፌደራል የዲሞክራሲያዊ ተቋም ነው። በክልል ጽህፈት ቤቶች አሉት። አገር አቀፍ ምርጫ ባልተደረገበት በክልል ምርጫ እንደርጋለን ማለት፣ የፌደራል ዲሞክራሲያዊ ተቋም ባልተሳተፈበት፣ ባልታዘበበት ምርጫ ማድረግ የምርጫውን ሕጋዊነት፣ ነፃና ገለልተኝነት ጥያቄ ውስጥ ይጥለዋል" በማለትም ክልሉን የሚያስተዳድረው ፓርቲ ህወሐት፤ ምርጫ ማካሄድ እንደማይችል ያብራራሉ።

"ምርጫ ሲባል ዝም ብሎ አንድ ቀን ሄዶ መምረጥ አይደለም" የሚሉት ዶ/ር አደም በበኩላቸው "በቅድሚያ የምርጫ ወረዳዎች መወሰን አለባቸው። ያለውን እንኳ ይጠቀማሉ ቢባል ያም እንደገና መወሰን አለበት። ከዚያም ሲያልፍ የፖለቲካ ፓርቲዎች መመዝገብ ያስፈልጋቸዋል" በማለት ሂደቱን ያብራራሉ።

የፖለቲካ ፓርቲዎች ከተመዘገቡ በኋላ ምልክታቸውን ማሳወቅ፣ መራጮች መመዝገብ፣ ቅስቀሳ ማካሄድ እንደሚያስፈልግ በማስታወስ ህወሐት "ሁሉን ነገር የማድረግ የሕግ ሥልጣን ብቻ ሳይሆን በተግባር አቅምም፤ ተቋማዊ ዝግጅትም አለው ብዬ አላስብም" ይላሉ።

የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬም በበኩላቸው ምርጫ ቦርድ አገራዊ ምርጫውን ሲያራዝም አገሪቱ በኮሮናቫይረስ ውስጥ ስላለች ነው በማለት "አሁን ባለንበት ሁኔታ የተለያዩ የሲቪልና ፖለቲካዊ መብቶች ይገደባሉ" ይላሉ።

እነዚህ መብቶች መካከል ደግሞ የመመረጥና የመምረጥ መብት እንደሚገኝበት በመግለጽ ይህ ጉዳይ ሕገ መንግሥቱ ላይ የሰፈረ፣ ምርጫ ቦርድም በሕገ መንግሥቱ መነሻነት ያንን ውሳኔ ማሳለፉን ይገልፃሉ።

"ስለዚህ ሁኔታዎች ተሻሽለው ወደ መደበኛው ሕይወት እስክንመለስ ድረስ ስለምርጫ የምናወራበት ሕገ መንግሥታዊ መሰረት ያለን አይመስለኝም" ይላሉ።

ዶ/ር አደም በበኩላቸው የክልሉ መንግሥት ወይንም ህወሓት ምርጫውን አደርጋለሁ ብሎ እርምጃ ቢጀምር ያ ተቋም ነፃነት አለው ወይ? በሌሎቹ ይታመናል ወይ? እንደምርጫ ቦርድ ሆኖ የሚያገለግል ተቋማዊ መዋቅር ይኖረዋል? የሚሉ ጥያቄዎችን በማንሳት "እኔ ግን አለው ብዬ አላምንም" ይላሉ።

መፍትሔው ታዲያ ምንድን ነው?

የሕግ ባለሙያው አቶ ኤፍሬምም ሆኑ የአስተዳደርና ዲሞክራሲ አማካሪው ዶ/ር አደም ለተፈጠረው ፖለቲካዊ አለመግባባት ከመነጋገር የተሻለ ሌላ አማራጭ አይታያቸውም።

"የዚህ ችግር ምንጩ በአዲሱ የብልጽግና ፓርቲና በህወሓት ወይንም በነባሩ ኢህአዴግ መካከል ያለ የፖለቲካ ግጭት ነው" የሚሉት ዶ/ር አደም "የተወሰዱ እርምጃዎችና ውሳኔዎች ሕጉን ይጥሳሉ ወይም ይቃረናሉ የሚሉ ከሆነ፤ አይ እኔ ምርጫ አካሄዳለሁ ማለት ሳይሆን . . . ወደ ሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ፣ ከዚያም አልፎ ወደ ፌደሬሽን ምክር ቤት ሄዶ ለመፍታት መሞከር ይሻላል" በማለት ይመክራሉ።

"ምናልባት እነርሱ ሕጉን ጥሰዋል እኛም ሕጉን እንጥሳለን ከሆነ፤ የአንድ ጥሰት ሌላኛውን ጥሰት ትክክል አያደርገውም" በማለትም እንዲህ አይነት ቅራኔ ምንጩ ፖለቲካዊ ግጭት በመሆኑ ከሕግ ይልቅ ፖለቲካዊ ውሳኔ መፍትሄ ሊያመጣ እንደሚችል ይጠቁማሉ።

ጉዳዩ ላይ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አቋም ምን እንደሆነ ለማወቅ የምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ እና የቦርዱ ቃል አቀባይ የእጅ ስልክ ላይ ብንደውልም ልናገኛቸው አልቻልንም።