ህወሓት ፡ በ5ኛው ዘመን የሕዝብ ተወካዮችና የፌደሬሽን ምክር ቤት የተገኙት ብቸኛዋ የህወሓት አባል

ያየሽ

የፎቶው ባለመብት, YAYESH

ህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ (ህወሓት) በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲሁም በፌዴሬሽን ምክር ያሉና በተለያዩ የፌደራል መንግሥት የፖለቲካ ሹመት ላይ የሚገኙ አባላቱ የተወከሉበትን ምክር ቤትና ኃላፊነት ለቅቀው እንዲወጡ አዝዟል።

በመሆኑም መስከረም 25/2013 ዓ.ም በተካሄደው 5ኛው የሕዝብ ተወካዮች እና የፌዴሬሽን ምክር ቤቶች 5ኛ የፓርላማ ዘመን 6ኛ ዓመት የሥራ ዘመን የመክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ የትግራይ ክልል ተወካዮች እንደማይሳተፉ ተገልጾ ነበር።

ይህንንም ተከትሎ ህወሓት ካሉት 38 የትግራይ ክልልን እና አምስት አዲስ አበባን ወክለው በምክር ቤቱ ከሚገኙት እንደራሴዎች መካከል 42ቱ ሳይገኙ ቀርተዋል። በስብሰባ ላይ የተገኙት አንድ ተወካይ ብቻ ነበሩ። እርሳቸውም ወ/ሮ ያየሽ ተስፋሁነይ ናቸው።

ወ/ሮ ያየሽ በአዲስ አበባ ከተማ የካ ክፍለ ከተማ ህወሓትን (ኢህአዴግ) ወክለው ነበር ከአምስት ዓመት በፊት በተካሄደው ምርጫ ላይ በመሳተፍ የምክር ቤት አባል የሆኑት። ቢቢሲ ከእርሳቸው ጋር አጭር ቆይታ አድርጓል።

መስመር

የምክር ቤቱ ስብሰባ እንዳትሳተፉ ከህወት የመጣውን ትዕዛዝ እንዴት ነበር የሰሙት?

ወ/ሮ ያየሽለእኔ በደብዳቤም ሆነ በስልክ የደረሰኝ ነገር የለም። ከመገናኛ ብዙሃን ነው የሰማሁት።

በጉዳዩ ላይ የተደረገ ውይነበር?

ወ/ሮ ያየሽእኔ አልተወያየሁም። ሌሎችን ወክዬ መናገር አልችልም። ስለሌሎቹ ግን አላውቅም።

ከእርስዎ በስተቀር በምክር ቤቱ ያሉ ሁሉም የህወት ተወካዮች በስብሰባው ላይ አልተገኙም። እርስዎ ለመገኘት እንዴት ወሰኑ?

ወ/ሮ ያየሽ እንደሚታወቀው የተወካዮች ምክር ቤት የሥራ ዘመን በአምስት ዓመት ነው የሚያበቃው፤ ይሁን እንጂ በአገራችን በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከተፈጠረው ስጋት፣ ፍርሃትና ችግር አንፃር ምርጫ ቦርድ ምርጫ ለማካሄድ የተቸገረ መሆኑን ገልጾ፤ በሕገ መንግሥቱ አግባብ መሰረት ወደ ተወካዮች ምክር ቤት መጥቶ፤ ከዚያም የፌደሬሽን ምክር ቤት ባደረገው ውሳኔ መሰረት ምርጫው እንዲራዘም ሆኗል።

ይህ አካሄድ ሕገ-መንግሥታዊ ስለሆነ፣ መርህን የተከተለ እና ለሕዝብ የሚጠቅም በመሆኑ፤ እኔ የመረጥኩት ይህንን ሕጋዊ አግባብን ተከትሎ የተሰጠ ውሳኔ ስለሆነ ነው በስብሰባው ላይ ልገኝ የቻልኩት።

እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ ከቤተሰብም ሆነ ከሌላ አካል የደረሰበዎት ጫና አለ?

ወ/ሮ ያየሽበማንም የደረሰብኝ ጫና ወይም ተፅዕኖ የለም። መታወቅ ያለበት ነገር እኔ ራሴን የቻልኩኝ አዋቂ ሰው ነኝ። ከ18 ዓመት በላይ የሆነ ሰው በራሱ መወሰን እንዳለበት በአፅንኦት የማምን ሰው ነኝ።

እንደዚህ ዓይነት ሃሳቦች መምጣታቸው ባይገርምም፤ ሰው በራሱ አመለካከት እና እይታ የሚወስን ፍጡሩ መሆኑ መታወቅ አለበት። አንድ ሚዲያም ይህንኑ ሲጠይቀኝ በምሳሌ ነበር ያስረዳሁት።

ምን ብለው?

ወ/ሮ ያየሽየቀድሞ የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ ኮፊ አናን አንድ ጊዜ 'ልጅዎ እንደዚህ ያደርጋል፣ እንደዚህ ያጠፋል፣ ምናምን እያሉ ጋዜጠኞች ጠየቋቸው። ጥያቄያቸው የልጃቸውን ጥፋት ከእርሳቸው ጋር ለማገናኘት ነበር። እናም እርሳቸው 'He is an adult! He is a man' ብለው ነበር የመለሱት።

እኔም እንደዚያ ነው የማስበው። እኔ ራሴን የቻልኩ ሴት፣ ራሴን የቻልኩ ብቁ ሰው ነኝ ብዬ ነው የማስበውና በራሴ እምነት የመሰለኝን ለማድረግ ብቁ ሰው ነኝ ብዬ ነው የማምነው።

ከቤተሰብ ጋር ተመሳሳይ ወይም የተለያየ ሃሳብ ሊኖረኝ ይችላል። እምነቴ ግን የራሴ ነው።

የትግራይ ክልል የብልፅግና ፓርቲ አባል ነዎት?

ወ/ሮ ያየሽአይደለሁም።

ታዲያ ምርጫ እስከሚካሄድ ማንን ወክለው ነው በምክር ቤቱ የሚቀጥሉት? ህወትን? ወይስ . . . ?

ወ/ሮ ያየሽምክር ቤት ውስጥ ስንወከል የሕዝብ ውክልና ይዘን እንጂ ለፓርቲ ውክልና በሚል አግባብ አይደለም። ስለዚህ እኔ የሕዝብ ውክልና ይዤ ነው የምቀጥለው።

በምክር ቤቱ ህወሓት ይህን ያህል መቀመጫ አለው ብሎ የሚወስድ ካለም መውሰድ ይችላል።

በዚህ ዓመት በሚካሄደው ምርጫ የመወዳደር ሃሳብ አለዎት?

ወ/ሮ ያየሽአልወሰንኩም።

ቢወዳደሩ ግን ማንን ወክለው የሚወዳደሩ ይመስልዎታል?

ወ/ሮ ያየሽእሱንም አልወሰንኩም።

ከዚህ ቀደም የክልል ምክር ቤት ወይም የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል ሆነው ያውቃሉ?

ወ/ሮ ያየሽበሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመጀመሪያ ጊዜዬ ነው። የክልል ምክር ቤት አባል ሆኜም አላውቅም። አንድ ወቅት ግን በ1992 ዓ.ም የመቀሌ ከተማ ምክር ቤት አባል ሆኜ አውቃለሁ።

በፌደራልና በትግራይ ክልል መንግሥት መካከል ፖለቲካዊ መካረሮች እንዳሉ ይታወቃል። እርስዎ ይህንን ጉዳይ እንዴት ነው የሚያዩት?

ወ/ሮ ያየሽለሕዝብ ችግር መፍትሔ ለመስጠት፣ ሕዝብ የተቸገረበትን ጉዳይ ፍትሃዊ የሆነ ውሳኔ ለመስጠት፤ ሁላችንም መቆም አለብን ብዬ ነው የማስበው።

ግለሰቦች ወይም ፓርቲዎች በተለያዩ ሃሳቦች ሊጠላለፉ ይችላሉ፤ ነገር ግን አሁን በሰለጠነ ጊዜ ላይ ነው ያለነው። በመሆኑም የሕዝብ ጥቅምን መሰረት በማድረግ በጋራ ቁጭ ብሎ በመነጋገርና ውሳኔ በመስጠት በጋራ ችግሮችን መቅረፍ አለብን የሚል አስተያየት ነው ያለኝ።

በምክር ቤቱ ስብሰባ ላይ የተገኙ ብቸኛ የህወትን አባል ኖት። ይህን መወሰንዎ ምን ውጤት ይኖረዋል ብለው ያስባሉ?

ወ/ሮ ያየሽእኔ ህወሓትን ወክዬ የተወዳደርኩት በአዲስ አበባ የካ ክፍለ ከተማ ነው። አዲስ አበባ ላይ አምስት የህወሓት ተወካዮች ነን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የገባነው።

እኔ ፓርላማ ስገባ ድምፁን የሰጠኝን ሕዝብ አክብሬ፤ የሕዝብ ጥያቄ ማስተናገድና ግዴታና ኃላፊነት የጣለብኝን ሕዝብ ማገልገል አለብኝ ብዬ ነው። መታየት ያለበትም ከዚህ አንፃር ነው።

ፓርላማ ስንገባ የህወሓትን ወይም የኢሕአዴግ ሃሳብን ብቻ ለማራመድ አይደለም፤ የሕዝብ ጥያቄንም ለመመለስ ነው የገባሁት።

ይህንን ውሳኔዎን ተከትሎ ያጋጠመዎ ነገር አለ?

ወ/ሮ ያየሽበቀጥታ የመጣ ጥያቄም ሆነ የደረሰብኝ ነገር የለም። አሁን ወጣቱም ሆነ ሕዝቡም በሰፊው የሚጠቀመው ማኅበራዊ ሚዲያ አለ። በዚያ ላይ ለሕዝብ በመወገኔ ምክንያት ድጋፉን የሚገልጽልኝ ብዙ ነው።

ይሁን እንጂ የህወሓትን ሃሳብ የሚያራምዱ ጽንፈኛ የሆነ አመለካከል ያላቸው ሰዎች፣ በማኅበራዊ ሚዲያ የሚጽፉ ሰዎች፤ ተገቢ ያልሆነና የሰው ሃሳብ የማያከብር ስድብና ማስፈራሪያዎችን እያየሁ ነው ያለሁት።

ሁላችንም የተለያየ ሃሳብና አመለካከት ነው ያለን። ሃሳብና ተቃውሟቸውን ማቅረባቸውን አከብራለሁ፤ አደንቃለሁ። መሆንም አለበት። በዚያም ቅር አይለኝም፤ ነገር ግን በግል መሳደብ፣ አላስፈላጊ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ለማንም ስለማያስተምር ባይሆን ብዬ አስባለሁ። ከዚህ ውጪ በቀጥታ የመጣ ጥያቄ የለም።

ውሳኔዎን ተከትሎ ከህወት በኩል የደረሰዎ ነገር አለ?

ወ/ሮ ያየሽበቀጥታ የመጣ ነገር የለም፤ ነገር ግን ጽንፍ ይዘው በማኅበራዊ ሚዲያ በኩል የሚፅፉ በርካታ ሰዎች አሉ። በተዘዋዋሪ ግን የእነርሱ ወገን የሆኑ፣ የእነሱን ሃሳብ የሚያራምዱ ሰዎች የሚፅፉትን እያየሁ ነው። ይህም ከዚያ በኩል የመጣ ሊሆን ይችላል ብዬ እገምታለሁ።

እዚህ ውሳኔ ላይ በመድረስዎ ምክንያት ችግር ሊገጥመኝ ይችላል ብለው ይሰጋሉ?

ወ/ሮ ያየሽለሕዝብ ለምን ወገንሽ ብሎ ስጋት ላይ ሊጥለኝ የሚችል አካል መኖር አለበት ብዬ አላስብም፤ ነገር ግን የሚመጣውን ነገር ሁሉ ከሕዝብ ጋር ሆነን ችግሮችን በጋራ እንፈታለን ብዬ ነው የማስበው።