አንበጣ መንጋ፡ በአማራ ክልል 80 ሺ ሄክታር የሚጠጋ መሬት ላይ የአንበጣ መንጋ ተከስቷል

የበረሃ አንበጣ

በአማራ ክልል ከመስከረም ወር መጀመሪያ ሳምንት ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከፍተኛ ጉዳት እያደረሰ መሆኑን የክልሉ ባለስልጣናት ለቢቢሲ ተናገሩ።

የአንበጣ መንጋው በአንዳንድ ቀበሌዎች የተዘራ ሰብልን ሙሉ በሙሉ ያወደመ ሲሆን በአንዳንዶቹ ደግሞ የጉዳት መጠኑ ከ50 በመቶ በላይ መሆኑ ተገልጿል።

በአማራ ክልል በሚገኙ ሦስት ዞኖች፣ በስምንት ወረዳዎች እና በ66 ቀበሌዎች የአንበጣ ወረርሽኝ መከሰቱን የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በክልሉ ከሚገኙት የኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር፣ ደቡብ ወሎ እና ሰሜን ወሎ ዞኖች በተጨማሪ ጉዳቱ ያን ያክል የከፋ ባይሆንም በሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት ወረዳ በቅርቡ ወረርሽኙ መከሰቱንም ያብራራሉ።

በእነዚህ አካባቢዎች ከ151 ሺህ ሄክታር መሬት በላይ አሰሳ ተደርጎ በ78 ሺህ 800 ሄክታር ላይ የአንበጣ መንጋው መከሰቱ መረጋገጡን ምክትል ቢሮ ኃላፊው ገልፀዋል።

የአንበጣ መንጋውን ለመከላከልም በሰው ሃይል እና በአውሮፕላን በመታገዝ ቢያንስ ከ51 ሺህ ሄክታር በላይ የሚሆነውን መሬት ማጽዳት ተችሏል ብለዋል።

ነገር ግን አሁን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከእስካሁኑ የከፋ ጉዳት ሊያደርስ እንደሚችል ይገመታል ሲሉ ስጋታቸውን ይገልጻሉ።

አቶ ተስፋሁን ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየሰሩ መሆናቸውን ይናገራሉ።

የአማራ ክልል ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰንባቸው አካባቢዎች ከሰሜን ሸዋ ዞን ቀወት እስከ ሰሜን ወሎ ዞን ራያ ቆቦ ወረዳ ድረስ ባለው አካባቢ የአንበጣ መንጋው በስፋት መከሰቱን የአካባቢው ነዋሪዎች ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በየአካባቢው በተለያየ ጊዜ አንበጣው የተከሰተ ሲሆን፤ በአብዛኛው ግን ከመስከረም ወር የመጀመሪያው ሳምንት ጀምሮ የተከሰተ መሆኑንም ጨምረው ያስረዳሉ።

በራያ ቆቦ ወረዳ የአንበጣ መንጋው ለመጀመሪያ ጊዜ የተከሰተው በመስከረም ስድስት ነው ያሉት የወረዳው አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሸብር፤ ከዚያን ጊዜ ጀምሮ ሕብረተሰቡ በተለያዩ የመከላከያ መንገዶች ለመከላከል ጥረት ቢያደርግም በየቀኑ ከአፋር ክልል እየተፈለፈለ የሚመጣው አዲስ የአንበጣ መንጋ ከአቅም በላይ እየሆነ መምጣቱን ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋው በወረዳው ከአፋር ክልል ጋር በሚዋሰኑ ዘጠኝ ቀበሌዎች የተከሰተ መሆኑን የተናገሩት አቶ መንገሻ፤ ወርቄ እና ያያ የሚባሉ ቀበሌዎች ላይ በሰብል ላይ ከፍተኛ ጉዳት አድርሷል ብለዋል።

በእነዚህ ቀበሌዎች እስከ 500 ሄክታር ድረስ በሰብል የተሸፈነ መሬት በአበንጣው መጎዳቱንም ገልጸዋል።

የጉዳት መጠኑም ከ50 እስከ 100 በመቶ መድረሱን አስተዳዳሪው በማስረዳት፤ እስካሁን ከ20 ሺህ ሄክታር በላይ ቅኝት በማድረግ ከግማሽ በላይ የሚሆነውን መከላከል መቻሉንም ገልጸዋል።

በሃብሩ ወረዳ በተመሳሳይ በዘጠኝ ቀበሌዎች ላይ የአንበጣ መንጋው ጉዳት ማድረሱን የሚናገሩት የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዮሃንስ ተሰሜ እንደገለጹት፤ አንድ ቀበሌ ሙሉ በሙሉ የወደመ ሲሆን፤ በሌላ አንድ ቀበሌ ላይ ደግሞ ከ50 እስከ 100 በመቶ የሚሆን ሰብል ላይ ጉዳት ደርሷል ብለዋል።

እስከሁን በባህላዊ መንገድ እና በኬሚካል ርጭት የመከላከል ስራው እየተሰራ ነው። በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት የተደረገ ቢሆንም አካባቢው ካለው መልከዓ ምድራዊ ስፋት አንጻር በቂ ርጭት አለመደረጉን አቶ ዮሃንስ ያነሳሉ።

በሃብሩ ወረዳ በአውሮፕላን የታገዘ ርጭት የተደረገው ሦስት ጊዜ ብቻ መሆኑንም ያስረዳሉ።

አንበጣው በየጊዜው የሚጨምር እና የወረራ መጠኑም ከጊዜ ወደ ጊዜ የሚሰፋ በመሆኑ የአደጋውን አስቸጋሪነት ከፍ እንዳደረገው አቶ ዮሃንስ ገልጸዋል።

አቶ ዮሃንስ አውሮፕላኑ ለርጭት ስምሪት የሚሰጠው ከሰመራ መሆኑን በማንሳት ይህም መጓተት ማስከተሉን ተናግረዋል። ይህ በቅርበት ለመወያየት አመች ስለማይሆን ወደ ኮምቦልቻ ቢቀየር የተሻለ መሆኑንም አመላክተዋል።

ሰመራ ላይ የነበረው አውሮፕላን መነሻው ከ25/01/13 ዓ. ም. ጀምሮ ወደ ኮምቦልቻ ተዛውሮ ሌላ አንድ ተጨማሪ አውሮፕላን መጨመሩንም የአማራ ክልል ግብርና ቢሮ ምክትል ኃላፊ አቶ ተስፋሁን መንግስቴ ለቢቢሲ ተናግረዋል።

የግብርና ሚንስትርም የመርጫ መሳሪያ የተገጠመላቸው ተሽከርካሪዎች እንደሚያቀርብ ቃል ገብቶ ነበር ያሉት አቶ ዮሃንስ፤ እስካሁን አለመላኩን ያነሳሉ።

በግብርና ሚንስትር በኩል "አብዛኛው ድጋፍ እየተደረገልን ነው፣ እርሱን ወደየአካባቢዎቹ የማሰራጨት ሥራ እንሰራለን" ያሉት ምክትል ቢሮ ሃላፊው፤ አሁንም ግን አንበጣው መብረር ስለጀመረ ከሰው ኃይል ይልቅ በአውሮፕላን ርጭት መከላከል እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል።

ተጨማሪ አውሮፕላን እንዲመደብ ከሚመለከታቸው አካላት ጋር እየተነጋገርን ነውም ብለዋል።

ቢቢሲ ያነጋገራቸው የሃብሩ እና የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪዎች ችግሩ በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን ገልጸዋል።

የሚያነሱት ምክንያት ደግሞ የአንበጣው ዋና መፈልፈያው አፋር ክልል በመሆኑ በየወረዳቸው የሰፈረውን የአንበጣ መንጋ መቀነስ ቢቻልም በየጊዜው ከክልሉ እየተፈለፈለ ወደ አማራ ክልል እየገባ መሆኑን ነው።

ርጭቱ የአንበጣ መንጋው የተከሰተበት ቦታ ላይ መካሄድ አለበትም ብለዋል።

ከአሁን በፊት የአንበጣ መንጋው በተከሰተበት አካባቢ የሚኖሩ አፋሮች፤ ኬሚካሉ ለከብቶቻችን ስጋት ይሆናል በሚል ፈቃደኛ እንዳልነበሩ የተናገሩት የራያ ቆቦ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ መንገሻ አሸብር፤ አሁን ግን እነሱም የችግሩ ሰለባ እየሆኑ በመምጣታቸው በቅርቡ ባደረጉት ውይይት ርጭቱ መካሄድ እንዳለበት መስማማታቸውን ይናገራሉ።

ምክትል ቢሮ ኃላፊው አቶ ተስፋሁን፤ እስካሁን ቅድሚያ ተሰጥቶት የነበረው በሰብል ላይ ጉዳት ሲያደርስ የነበረውን አንበጣ መከላከል መሆኑን በማስታወስ፤ በዚህም የተነሳ ወደ አፋር ሂዶ መፈልፈያው ላይ መርጨት አለመቻሉን ገልጸዋል።

አሁን ግን ሁለት አውሮፕላኖች ስለተመደቡ አንደኛውን ወደ አፋር በመላክ አንበጣውን ከመፈልፈያው የማክሰም እና የመከላከል ስራው እንደሚሰራ ገልጸዋል።