በአንበጣ መንጋ ስጋት ሶማሊያ ብሔራዊ አደጋ አዋጅ አወጀች

የፎቶው ባለመብት, EPA
የበረኃ አንበጣ በምስራቅ አፍሪካ መስፋፋቱን ተከትሎ ሶማሊያ ብሔራዊ አደጋ አዋጅ አወጀች።
የሶማሊያ የግብርና ሚንስቴር በከፍተኛ ሁኔታ አዝርእትን ሊያወድም የሚችለው አንበጣ "በሶማሊያውያን የምግብ ደህንነት ላይ አደጋ ደቅኗል" ብሏል።
ምርት ከሚሰበሰብበት ሚያዚያ ወር በፊት የአንበጣ መንጋውን በሶማሊያ መቆጣጠር እንደማይቻል ተነግሯል።
የተባበሩት መንግሥታት በሶማሊያ እና በኢትዮጵያ የተከሰተው መንጋ በአገራቱ 25 ዓመታት ታሪክ ታይቶ የማይታወቅ ነው ብሏል።
የምግብ እና ግብርና ድርጅት (ፋኦ) እንደሚለው ጎረቤት አገር ኬንያ ደግሞ ይህን መሰል የአንበጣ መንጋ ሲገጥማት ከ70 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ ነው።
ይሁን እንጂ ሶማሊያ ብቻ ነች የአንበጣ መንጋው ሊያስከትል የሚችለውን አደጋ ከግምት በማስገባት ብሔራዊ አደጋ ስትል ያወጀችው።
በሶማሊያ ባለው የጸጥታ እክል በአውሮፕላን በመታገዝ ጸረ አንበጣ መድሃኒት ርጭት ማካሄድ አልተቻለም።
ባሳለፍነው ወር ፋኦ በአፍሪካ ቀንድ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ እራሱን በ500 እጥፍ ሊያሳድግ እንደሚችል በመጠቆም ዓለም አቀፍ ድጋፎች እንዲደረጉ ጥሪ አቅርቦ ነበር።
ከየመን በቀይ ባህር አድርጎ ወደ ምስራቅ አፍሪካ አገራት የተዛመተው አንበጣ በቀን 150 ኪ.ሜትር የመጓዝ አቅም አለው።
አንድ እድገቱን ያጠናቀቀ አንበጣ በቀን የራሱን ክብደት ያክል መመገብ ይችላል።
ከጥቂት ወራት በፊት ሶማሊያውያን የአንበጣውን መንጋ ለምግብነት በማዋል እየተዋጉት የመሆኑ ዜና የብዙዎች መነጋገሪያ መሆኑ ይታወሳል።












