በአማራ ክልል አምስት ዞኖች የአንበጣ መንጋ ጉዳት እንደያደርስ ተሰግቷል

አንበጣ

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

በአማራ ክልል በሚገኙ 36 ወረዳዎች ላይ የተከሰተው የአምበጣ መንጋ በመስኖና በአረንጓዴ ልማት ሥራዎች ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ተሰግቷል።

የአንበጣ መንጋው በሰሜን ሸዋ፣ በደቡብና ሰሜን ወሎ፣ በሰሜን ጎንደር እና በዋግኽምራ የተለያዩ ወረዳዎች ውስጥ መከሰቱን የክልሉ ግብርና ቢሮ ለቢቢሲ ገልጿል።

የቢሮው ሕዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አምሳሉ ጎባው እንደገለጹት የአንበጣ መንጋው በተለያዩ በአምስት ዞኖችና በ36 ወረዳዎች ውስጥ ተከስቷል።

መንጋውን የመከላከል ሥራው በጠቅላላ በባህላዊ ዘዴ እየተከናወነ መሆኑን የጠቀሱት ዳይሬክተሩ "በጥሩምባ፣ በሰዎች ድምጽ፣ በመኪና፣ በጅራፍ እና በሌሎች መንገዶች" የአካባቢዎቹ ነዋሪዎች ጥረት እያደረጉ ነው።

የበረሃ አምበጣው አሁን ወቅቱ በጋ በመሆኑ መስክ ላይ ሰብል እንደሌለ ያመለከቱት አቶ አምሳሉ፤ ነገር ግን መንጋው "የመስኖ እና አረንጓዴ ልማታችችን እንዳያወድም" ስጋት መኖሩንና ይህንንም ለመከላከል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ተናግረዋል።

ዳይሬክተሩ አክለውም የአሁኑ የበረሃ አንበጣው የዕድገት ደረጃውን የጨረሰ በመሆኑ አጥፊ አለመሆኑን ጠቁመው፤ አንበጣው የሚያሰጋው ወደፊት መሆኑን ተናግረዋል።

የአንበጣ መንጋው "በዚህ ወቅት እንቁላል በመጣል ሊራባና ጉዳት ሊያደርስ ይችላል የሚል ስጋት ስላለ የቅድመ ዝግጅት ሥራ እየተሠራ ነው" ብለዋል።

በዚሁ ምክንያት አውሮፕላን ርጭት ለጊዜው አስፈላጊ አይደልም ያሉት ዳይሬክተሩ፤ ኬሚካል ግን በጣም በተወሰኑ ቦታዎች ላይ መጠቀማቸውን ተናግረዋል።

የበረሃ አንበጣው የደቀነውን ትልቅ ስጋት ከግምት በማስገባት ግብርና ቢሮው ከግብርና ሚንስቴር ጋር ከመረጃ ልውውጥ ጀምሮ እየሠራ ይገኛል።

መንጋው ከተከሰተባቸው አካባቢዎች አንዱ በሆነው በሰሜን ሸዋ ዞን የበረሃ አምበጣው በተደጋጋሚ እየተከሰተ መሆኑን የዞኑ የግብርና መምሪያ ኃላፊ ወ/ሮ መሠረት ኃይሌ ለቢቢሲ አረጋግጠዋል።

በአካባቢው መጋቢት 19 ከተከሰተ በኋላ በድጋሚ ካለፈው ሐሙስ ጀምሮ በዞኑ አራት ወረዳዎች ውስጥ በሚገኙ 16 ቀበሌዎች ላይ ተከስቷል።

ኃላፊዋ መንጋው ወደፊት "አስጊ" ሁኔታ ሊፈጥር ይችላል ያሉ ሲሆን፤ የበረሃ አምበጣውን ለመከላከል ከዞን እስከ ቀበሌ ድረስ ዝግጅት እየተደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።

በቅርቡ የተባበሩት መንግሥታት ባወጣው መረጃ መሰረት በአንበጣ መንጋ ክፉኛ ይጠቃሉ ተብለው ከተሰጋላቸው የምሥራቅ አፍሪካ አገራት መካከል ኢትዮጵያ አንዷ ስትሆን 22,550 ሔክታር ስፋት ያለው መሬቷ ለጉዳት ተጋላጭ እንደሚሆን ተነግሯል።

የዓለም የምግብና እርሻ ድርጅት-ፋኦ እንዳለው የአንበጣ መንጋው ክፉኛ ከሚያሰጋቸው አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ ሰፊ ቦታን የሚሸፍን አካባቢ በአንበጣው የውድመት ክልል ውስጥ እንደሆነ የተገለጸ ሲሆን በአፋጣኝ እርዳታው ተገኝቶ መከላከል ካልተቻለ ከባድ ቀውስን ሊያስከትል ይችላል ተብሏል።

የተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት ለቢቢሲ እንደገለጸው በአንበጣ መንጋው ክፉኛ በተጠቁት በኢትዮጵያ፣ በኬንያና በሶማሊያ በእያንዳንዱ አገር ውስጥ ቢያንስ 100 ሺህ ሔክታር ስፋት ያለው መሬት የጸረ አንበጣ መድኃኒት መርጨት ያስፈልጋል።

የአንበጣው መንጋው የተከሰተባቸው አካባቢዎች