አሳሳቢው የአንበጣ መንጋ ስጋት በኢትዮጵያና በአካባቢው አገራት

የፎቶው ባለመብት, EPA
ኢትዮጵያን ጨምሮ በምሥራቅ አፍሪካ አገራት ጥቂት ወራት ውስጥ በሁለተኛ ዙር የበረሃ አንበጣ መንጋ መጠቃታቸው ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተዳምሮ በአካባቢው ሕዝብ ላይ ከባድ አደጋን ደቅኗል።
በበረሃ አንበጣ ወረራ በአህጉሪቱ በሕዝብ ብዛት ሁለተኛ የሆነችውን ኢትዮጵያንና የአካባቢው ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴ ማዕከል በሆነችው ኬንያ እንዲሁም ለአስርታት አለመረጋጋት ውስጥ የምትገኘው ሶማሊያ ክፉኛ የተጠቁ አገራት ናቸው።
ከዕለት ዕለት በወረርሽኙ የሚያዙ ሰዎች ቁጥር እየጨመረና ምጣኔ ሃብታዊ እንቅስቃሴዎች በተገቱበት በአሁኑ ወቅት እንዲሁም የረሃብ ስጋት የአካባቢውን አገራት ሕዝብ ስጋት ላይ በጣለበት ጊዜ ይህ የአንብጣ መንጋ ወረራ ችግሩን ውስብስብ ያደርገዋል።
ይህ ሁለተኛ ዙር የበረሃ አንበጣ ወረራ ከመጀመሪያው በ20 እጥፍ የላቀ ሲከፋም በመጪው ሠኔ ወር ላይ እስከ 400 እጥፍ በላይ በመሆን አገራቱ ላይ ውድመት ያደርሳል ተብሎ ተሰግቷል።
"በቁጥቋጦዎች ውስጥ፣ በከብት መኖ ላይ፣ በመስኖ ልማት አካባቢዎች እንዲሁም በጫካ ውስጥ ሳይቀር አንበጣ አግኝተናል" ያሉት በአማራ ክልል በአሁኑ ጊዜ ያለውን የአንበጣ ወረራ ላይ ግምገማ ያደረጉት ወይዘሮ መሰረት ኃይሉ ናቸው።
የአንበጣ መንጋው የጤፍ ምርትን ጨምሮ ሽንኩርትን የመሳሰሉ የአትክልት ምርቶችን ሳይቀር እያወደሙ መሆኑን ተናግረዋል።
ከሦስት ወራት በፊት በጀመረው የመጀመሪያ ዙር የአንበጣ መንጋው ወረራ ወቅት በኢትዮጵያ፣ በኤርትራና በጂቡቲ በከፍተኛ መጠን የተከሰተ ሲሆን እንዲሁም በደቡብ ሱዳን፣ በኬንያ፣ በሶማሊያ፣ በኡጋንዳና በታንዛኒያ ደግሞ በአነስተኛ ቁጥር ተከስቶ ነበር።
ለሃያ አምስት ዓመታት እንዲህ ያለ አደገኛ የአንበጣ መንጋ ወረርሽኝ አጋጥሟቸው የማያውቁት የአካባቢው መንግሥታት መንጋውን ለመከላከል ጭንቅ ውስጥ ገብተዋል።
"የመጀመሪያው ዙር የአንበጣ መንጋ በደረሰበት አካባቢ በመራባት እንቁላል ጥሎ ነበር፤ አሁን ሁለተኛው ትውልድ ደግሞ አድጎ ለጥፋት ደርሷል፤ የመከላከል ሥራውም አስቸጋሪ ሆኗል" ይላሉ ሲሪል ፌራንድ ከተባበሩት መንግሥታት የምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ)።
አዲሶቹ የአንበጣ መንጋዎች ያገኙትን ሁሉ በመመገብ የማውደም አቅማቸው ከፍተኛ ነው። ይህ መንጋም ከኬንያና ሶማሊያ የድንበር አካባቢዎች ወደ ኢትዮጵያ እየተስፋፋ ይገኛል።
ከየካቲትና እስከ ግንቦት የሚኖረው አጭር የዝናብ ወቅት በሠኔ ወር ላይ ለሚሰበሰበው ምርት ወሳኝ የእርሻ ጊዜ ነው።
ባለፉት ዓመታት በአካባቢው ያጋጠመውን ድርቅ ተከትሎ በዚህ ዓመት ጥሩ የሚባል ዝናብ ተገኝቶ ነበር። ነገር ግን ያለው እርጥበታማ ሁኔታ ለአንበጣ መንጋው እንቁላል መፈልፈል አመቺ ሁኔታን ፈጥሯል።
ቀደም ሲል በሰሜናዊና ማዕከላዊ ኬንያ ውስጥ የአንበጣ ወረራ ብዙም አያጋጥምም ነበረ። አገሪቱም ከ70 ዓመታት በላይ ለሚሆን ጊዜ እንዲህ አይነቱ የአንበጣ ወረራ አጋጥሟት አያውቅም። አሁን ግን ግዙፍ የአንበጣ መንጋ እየተፈለፈለ መሆኑ ተነግሯል።

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ይህንን አስጊ የበረሃ አንበጣ መንጋ ለመቆጣጠር ጸረ አንበጣ መድኃኒትና በተፈጥሮ አካባቢ ላይ ጉዳትን የማያደርሱ መንገዶችን መጠቀም ያስረፈልጋሉ። እነዚህም የሚገኙት ከጃፓን፣ ከኔዘርላንድስና ከሞሮኮ ነው።
ነገር ግን የኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ የአየር ትራንስፖርት አገልግሎትን በማስተጓጎሉ የአንበጣ መንጋውን ለመቆጣጠር የሚያስፈልጉትን መገልገያዎች ለማጓጓዝና ጥቅም ላይ ለማዋል የአቅርቦት ሁኔታው አስተማማኝ ካለመሆኑ በተጨማሪ ወጪውም በጣም ከፍተኛ ሆኗል።
"መከላከያውን የማስመጣት ሂደቱ በጣም አዝጋሚ ነው። የጸረ አንበጣ መድኃኒቱን በጊዜው መርጨት ካልተቻለ መንጋው በከፍተኛ መጠን ይጨምራል። ኬንያ ውስጥ ደግሞ ሁኔታው የከፋ ነው" ይላሉ የምሥራቅ አፍሪካ የበረሃ አንበጣ መቆጣጠሪያ ድርጅት ዋና ዳይሬክትር ዶክትር ስቴፈን ንጆካ።
የአንበጣ መንጋውን እንቅስቃሴ ለመከታተል የሚያስፈልጉትን ሄሊኮፕሮችን ወደ አካባቢው የማምጣቱ ሂደት ዘግይቷል። ሲደርሱም አብራሪዎቹ ወደ ለይቶ ማቆያ መግባት ይጠበቅባቸዋል።
ለጸረ አንበጣ መድኃኒት መርጨት ሥራ የሚያስፈልጉት የመከላከያ አልባስት በአብዛኛው የመሚመረቱት ቻይና ውስጥ ሲሆን፤ ፋኦ እንደሚለው በአሁኑ ወቅት በቂ ክምችት አለ። ነገር ግን በቀጣይ አቅርቦቶች ላይ ያለው መዘግየት ከቀጠለ አሳሳቢ እንደሆነ አመልክቷል።
እንደ ተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ትንበያ የአንበጣ መንጋው ወረርሽኝ በቶሎ በቁጥጥር ስር ካልዋለ በሠኔ ወር ላይ የመንጋው መጠን እስከ 400 እጥፍ በመድረስ በምርት ላይ ከፍተኛ ጉዳትን ያስከትላል።
"ሰብሉ ሲያቆጠቁጥ በአንበጣው ይበላል፤ በዚህም ለምርቱ የተደረገው ጥረትም መና ይቀራል። አምራቹ ሁሉንም ስለሚያጣ ካለምንም ምርት ይቀራል" ይላሉ የፋኦው ፌራንድ።
በአንበጣ መንጋው ክፉኛ ከተጠቁት አገራት መካከል አንዷ በሆነችው ኢትዮጵያ መንጋው 200 ሺህ ሔክታር የሚሆን የሰብል እርሻንና አንድ ሚሊዮን ሔክታር የሚሆን የእንስሳ መኖን አውድሟል።
የዓለም ምግብና እርሻ ድርጅት (ፋኦ) እንደሚለውም በዚህ ሳቢያም አንድ ሚሊዮን የሚደርስ ሕዝብ ለረሃብ ችግር ተዳርጓል።
ይህ ክስተትም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት በየአገራቱ ከተጣሉት የእንቅስቃሴ ገደቦች ጋር ተዳምሮ ባለሙያዎችን እጅጉን አሳስቧል። ምክንያቱም በሰብል ላይ የሚደርሰው ውድመት ረሃብንና ድህነትን በከፍተኛ ደረጃ ሊያባብስ ስለሚችል ነው።
የምሥራቅ አፍሪካ መንግሥታት የጋራ ድርጅት በሆነው ኢጋድ ውስጥ የምግብ ፖሊሲ ተንታኝ የሆኑት ያስፐር ምዌሲግዋ እንደሚሉት፤ በስድስቱ አገራት ውስጥ እራሳቸውን ለመመገብ ፈተና የገጠማቸው 25 ሚሊዮን የሚደርሱ ሰዎች አሉ።
የአንበጣ መንጋውን በጊዜ መቆጣጠር ካልተቻለ ደግሞ ተጨማሪ አምስት ሚሊዮን ሰዎች ላይ የምግብ ዋስትና ስጋትን ይደቅናል ሲሉ የችግሩን አሳሳቢነት ይገልጻሉ።
"ይህም በአካባቢው አገራት ያሉ ሰዎች ከዚህ ቀደም ከገጠማቸው የምግብ ዋስትና ችግር ሁሉ ከፍተኛው ይሆናል" ሲሉ ያስፐር ጨምረዋል።












