"የአንበጣ መንጋው ጉዳት ማድረሱን ባንክድም፤ ምን ያህል እንደሆነ ለጊዜው አልታወቀም" የግብርና ሚኒስቴር

የፎቶው ባለመብት, KALLU COMMUNICATION AFFAIRS
ከየመንና ከሶማሌላንድ እንደመጣ የተነገረው የአንበጣ መንጋ በተለያዩ አገሪቷ ክፍሎች ውድመት እያስከተለ እንደሆነ እየተነገረ ነው። በአማራ ክልል፣ በአፋር፣ ደቡባዊ ትግራይ፣ ምስራቅ ኦሮሚያና ምስራቅ ሀረርጌ አንዳንድ አካባቢዎች መከሰቱ ይታወቃል። መንጋው ቀደም ሲል ያልገባባቸው ቦታዎች ላይ አሁንም እየዘመተ ነው።
የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል በቃሉ ወረዳ ከሁለት ቀናት በፊት የአውሮፕላን ርጭት ለማድረግ ተሞክሮ በአካባቢው የመልክዓ ምድር አቀማመጥ ምክንያት ሳይሳካ መቅረቱን የወረዳው የኮሚዩኒኬሽን ኃላፊ አቶ አብዱ እንድሪስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።
አቶ አብዱ አክለውም በሰው ኃይል ሰብሉን ለመሰብሰብ ጥረት ቢደረግም ያለጊዜው በመሰብሰቡ ከውድመት እንደማይድን ያክላሉ።
በዚያው ወረዳ ያነጋገርናቸው አርሶ አደር አህመድ ሀሰን "የአንበጣ መንጋው በተለያዩ ፎቶዎች ላይ እንደሚታየው አይደለም፤ ረዥምና ሰፊ ነው" ይላሉ።
ከአንዱ ሥፍራ ሲያባርሩት ወደ አንዱ የሚሰደደው የአንበጣ መንጋ ሦስተኛው ዙር ትናንት እነርሱ ጋር ውሎ አራተኛው ከሌላ ቦታ እንደሚመጣ ተነግሯቸው በስጋት እየጠበቁ እንደሆነ ይገልፃሉ።
አቶ አህመድ እንደሚሉት በአካባቢው እርሳቸውን ጨምሮ በርካታ አርሶ አደሮች ሰብላቸው ወድሞባቸዋል።
የአንበጣ መንጋው በዚያው ደቡብ ወሎ ዞን ወረባቦ ወረዳም በተለያዩ ቀበሌዎች ተከስቶ ዛሬ ወደ ሰሜን ወሎ ዞን መግባቱን ቢሰሙም አሁንም ስጋቱ እንዳላበቃ እና እየመጣ ያለ መንጋ መኖሩን የወረዳው ኮሚኒኬሽን ኃላፊ አቶ ሳዳም ሽመልስ ይገልፃሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ማህበረሰቡን በማንቀሳቀስ በባህላዊ መልኩ በጩኸትና በዛፍ ዝንጣፊ በማባረር ለመከላከል ቢሞከርም ተከታትሎ የሚመጣው መንጋ አሁንም ፈተና እንደሆነ ነው።
በአርጎባ ብሔረሰብ አስተዳደር ላይም በ6 ቀበሌዎች ተከስቷል። የመከላከል ሥራ ሲሠሩ ቢቆዩም አሁንም በሁለት ቀበሌዎች ላይ በስፋት ይገኛል ያሉት የወረዳው ኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አህመድ ጌታቸው ናቸው።
"አርጎባ ተራራማ አካባቢ ነው፤ ዳገት ቆፍረው ነው ሰብል የሚያመርቱት ከዛም ብሶ አንበጣ በላው። ስጋት ላይ ነው ያለነው" ብለዋል።
ከሳምንት በፊት ከወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ያገኙት መረጃን ጠቅሰው እስካሁን በወረዳው 275 ሄክታር ሰብል ላይ ጉዳት መድረሱን የገለፁት አቶ አህመድ በሚዲያዎች ላይ በሰብል ላይ ጉዳት አለመድረሱን የሚዘገበው ትክክል አይደለም ሲሉ ተችተዋል።

የፎቶው ባለመብት, KALLU COMMUNICATION AFFAIRS
በዚሁ ወረዳ አርሶ አደር ዙቤር ሸህ አዩብ ሰብላቸው ከወደመባቸው አንዱ ናቸው።
"አወዳደሙ ከመውደምም በላይ ነው፤ ሰብሉን ለመሰብሰብ በገባንበት ሰዓት ድንገት ከደረሰ ፊትም ጆሮም ይመታል፤ እዚያው እህሉ ውስጥ ነው ቁጭ የምንለው፤ የምናደርገው የለም" ሲሉ እርሳቸው 2 ሄክታር ላይ ያለ ሰብል እንደወደመባቸው ገልፀዋል።
እስካሁን በሰብል ላይ የደረሰውን ጉዳት አስመልቶ ጥያቄ የቀረበላቸው በግብርና ሚኒስቴር የዕፅዋት ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ዘብዲዎስ ሰላቶ፤ በተባይ መከላከል ሥርዓት ውስጥ ጉዳት የሚታወቀው መከላከሉ ሲጠናቀቅ ነው ብለዋል።
ከሥር ከሥር ጉዳቱን ለመግለፅ ጊዜ እንደሌላቸው የገለፁት ዳይሬክተሩ፤ "ጉዳት ማድረሱ ባይካድም የጉዳቱን መጠን ግን ምን ያህል እንደሆነ አናውቀውም፤ ይሄ ነው ብለን አንገልፅም፤ የራሱ ሂደት ስላለው" ብለዋል።
በአብዛኛው በመከላከል ሂደቱ ላይ ትኩረት እንዳደረጉ ገልፀዋል። ይሁን እንጅ በፀጥታ ችግር ምክንያት፣ በቦታዎች የመልክዓ ምድር አቀማመጥ እንዲሁም በአንዳንድ ቦታዎች ጫት ላይ ጉዳት ያደርስብናል በሚል ምክንያት የኬሚካል ርጭት ለማካሄድ ተግዳሮት እንደገጠማቸው ሳይጠቅሱ አላለፉም።
ኬሚካሉ በተጠኑ ቦታዎች ላይ በጥንቃቄ እንደሚረጭም በመግለፅ ለህብረተሰቡ ግንዛቤ ለመፍጠር እየሠሩ መሆናቸውን አስረድተዋል።
አንበጣን በጭስ፣ በጥይት፣ በርችት፣ በጩኸት፣ በጅራፍ. . ?
ማህበረሰቡ የአንበጣ መንጋውን ለመከላከል ድምፅ የሚፈጥሩ ነገሮችን በማቃጨል፣ በጅራፍ፣ በጥይት፣ በጩኸት፣ በርችት፣ በዘፈን፣ በፉጨት፣ ጨርቅ በማውለብለብ ለመከላከል ሲሞክሩ ተስተውለዋል። ይህ ልማድ በሳይንስስ ይደገፍ ይሆን?
አንበጣ በኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ አዲስ አይደለም የሚሉት አቶ ዘብዲዎስ አንበጣን በባህላዊ መንገድ መከላከል በሳይንስም የሚደገፍ ነው ይላሉ።
እርሳቸው እንደሚሉት ኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ መከላከል አባል የሆነችው በአውሮፓዊያኑ 1940/42 አካባቢ ነው። ኤርትራ የኢትዮጵያ አካል በነበረችበት ጊዜ ቀይ ባህር አካባቢና ከሌሎች አረብ አገራት አንበጣ ይሻገር ስለነበር አንበጣን በባህላዊ መንገድ የመከላከል ልማድ ነበር።
አንበጣው ሰብል ላይ እንዳያርፍ የማባረር ሥራም ይሠራ ነበር። ነገር ግን ከቦታ ቦታ የመረጃ ልውውጥ መኖሩ እጅግ አስፈላጊ ነው። ወደ ሄደበት አካባቢ ሪፖርት ማድረግ መዘንጋትም የለበትም ይላሉ።
ይሁን እንጅ አሁን በተለያዩ አካባቢዎች አንበጣን በጥይት ለማባረር የሚደረገው ሙከራ ትክክል አይደለም ሲሉ ነቅፈዋል- በጥይት የማባረር ተግባር በአውሮፓዊያኑ 2016 ብዙ ዋጋ እንዳስከፈለ በማስታወስ።
እንደ ዳይሬክተሩ ከሆነ በወቅቱ ተከስቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ከምስራቅ ኢትዮጵያ መከላከል አምልጦ ወደ አዲስ አበባ የገባው በጥይት ምክንያት ነው። ከዚያም ወደ ሰሜን የአገሪቷ ክፍሎች አምርቶ በርካታ ቀበሌዎችን ማዳረሱ የቅርብ ጊዜ ትውስታቸው ነው።
በመሆኑም "ብዙ ጭስ ማጨስ ሳያስፈልግ፤ በጭስ፣ በቆርቆሮ ድምፅ፣ በልጆች ጩኸት ድምፅ፣ በተለይ በጅራፍ ከሰብል ላይ መንጋውን ማባረር በቂ ነው" ሲሉ ይመክራሉ።
ነገር ግን ከሰብል አቅራቢያ ያለ የግጦሽ መሬት ላይ፣ ደን አካባቢ እና ሌሎች አካባቢዎች ሄዶ ካረፈ ማደሪያውን ብቻ መከታተል እንደሚያስፈልግ ይናገራሉ።
በርካታ ሕዝብ የማይኖርበትና ለመጠጥና ለምግብነት የሚውሉ ሰብሎች ባሉበት ቦታ ካልሆነ ፀረ ተባይ ኬሚካል መርጨት እንደሚቻል በመግለፅ የመከላከሉን ሥራ ማቅለል እንደሚቻል አቶ ዘብዲዎስ አስገንዝበዋል።
የአንበጣ መንጋው አሁንም በኢትዮጵያ እንደሚቀጥልና ወደ ኤርትራ፣ ሱዳን፣ ሳዑዲ አረቢያ፣ ኦማን፣ የመን፣ ሕንድ፣ ፓኪስታን፣ እንዲሁም በሰሜን አፍሪካ አገሮችን ጭምር ሊከሰት እንደሚችል ትንበያ መኖሩን አቶ ዘብዲዎስ ለቢቢሲ ገልፀዋል።












