የኢትዮጵያዊቷ ህክምና መቋረጥ በደቡብ አፍሪካ አነጋጋሪ ሆነ

ዓለም ኦርሲዶ

የፎቶው ባለመብት, Dawit

ለአስር ዓመታት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ የኖረችው ኢትዮጵያዊት አሳሳቢ የጤና ችግር አጋጥሟት ሆስፒታል ገብታ ህክምና ማግኘት ከጀመረች በኋላ በፍርድ ቤት ውሳኔ እንድትወጣ መደረጉ ሌላ የፍርድ ቤት ሂደት ቀሰቀሰ።

በስደት ወደ ደቡብ አፍሪካ ገብታ፤ ለስድስት ወራት በሚታደስ የመኖሪያ ፈቃድ ለረዥም ዓመታት የግል ሥራ እየሠራች የቆየችው ኢትዮጵያዊት ዓለም ኦርሲዶ፤ ከባድ የኩላሊት ህመም አጋጥሟት ሆስፒታል ከገባች በኋላ ደቡብ አፍሪካዊ ዜግነት ወይም መደበኛ የጥገኝነት ወረቀት የላትም በሚል ህክምና አቋርጣ እንድትወጣ መደረጉ ተነግሯል።

በድንገተኛ ህመም ሆስፒታል ተወስዳ የኩላሊት እጥበት (ዳያሊስስ) እንደሚያስፈልጋት ተነግሯት፤ የህክምና እርዳታ ሲደርግላት የቆየችው ዓለም፤ አስፈላጊው የመኖሪያ ሰነድ እንደሌላት ተነግሯት ህክምናዋን አቋርጣ እንድትወጣ በመታዘዟ ጉዳይዋ ፍርድ ቤት ሄዶ ነበር።

ዓለም ከደቡብ አፍሪካ መንግሥት በጥገኝነት እንድትቆይ የተሰጣት ሰነድ በየስድስት ወሩ የሚታደሰ የመኖሪያ ወረቀት መሆኑን የሚናገሩት የኢትዮጵያዊቷን ጉዳይ በቅርበት የሚከታተሉት አቶ ዳዊት አስገዶም ለቢቢሲ ተናግረዋል።

በዚህ የጥገኝነት ወረቀት በርካታ ኢትዮጵያዊያን ደቡብ አፍሪካ ውስጥ እንደሚገኙ የሚናገሩት አቶ ዳዊት ዓለም ሆስፒታል እያለች ያጋጠማት ነገር ሁሉንም ማስደንገጡን ና ማሳዘኑን ገልጸዋል።

ዓለም ያላት በየስድስት ወሩ የሚታደሰው የመኖሪያ ፈቃድ የጤና ችግር አጋጥሟት ሆስፒታል በቆየችበት ጊዜ የአገልግሎት ጊዜው በማብቃቱ መታደስ የነበረበት ሲሆን፤ በህክምና ላይ በቆየችበት ጊዜ አስፈላጊው የመኖሪያ ሰነድ ስላልነበራት ህክምናዋ እንዲቋረጥ ተደርጓል።

ጉዳዩም ወደ ፍርድ ቤት አምርቶ፤ ፍርድ ቤቱም ዓለም የሚያስፈልጋትን ህክምና ለማግኘት የሚያስችላት የመኖሪያ ሰነድ እንደሌላት በመግለጽ ከሆስፒታል እንድትወጣ መወሰኑ ተገልጿል።

ደቡብ አፍሪካ የሚኖሩት ኢትዮጵያዊ አቶ ዳዊት አስገዶም እንደሚሉት፤ ዓለም ወደ ደቡብ አፍሪካ ከሄደች አስር ዓመት የሆናት ሲሆን፤ በነዚህ ዓመታት ውስጥ የመኖሪያ ሰነዷን በየስድስት ወሩ እያሳደሰች ስትኖር ቆይታለች።

የስድስት ወር የመኖሪያ ፈቃድ ለአጭር ጊዜ የሚሰጥ መሆኑን የሚናገሩት አቶ ዳዊት፤ "ከዚህ ፈቃድ ተከትሎ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ሲኖርባቸው፤ ለዓመታት በአጭር ጊዜ የጥገኝነት ሰነድ እንድትቆይ ማድረጋቸው የነሱ ችግር ነው" በማለት ጠቅሰዋል።

በዚህም ምክንያት ዓለም የሚያስፈልጋትን ህክምና እንዳታገኝ መደረግ የለባትም በሚል አቶ ዳዊትና ሌሎች ኢትዮጵያዊያን ከሰብዓዊ መብት ቡድኖች ጋር በመሆን ገዳዩን መልሰው ወደ ፍርድ ቤት መውሰዳቸውንም ተናግረዋል።

ዓለም የግድ የኩላሊት እጥበት በሳምንት ሦስት ጊዜ ማድረግ እንዳለባት በሃኪሞች የተነገራት ቢሆንም፤ ከሆስፒታል እንድትወጣ ከተደረገች በኋላ ላለፉት አስር ቀናት አድርጋ እንደማታውቅ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።

ዓለም የሚያስፈልጋትን የህክምና ድጋፍ እንድታገኝ ለማድረግም አቶ ዳዊትና የሰብዓዊ መብት ተሟጋቾች በኢንተርኔት በኩል በጎ አድራጊ ኢትዮጵያዊያንና ሌሎችም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበው መዋጮ እኣሰባሰቡ እንደሚገኙም ለማወቅ ችለናል።

ዓለም አሁን ያለችበት ሁኔታ ከቀን ወደ ቀን አሳሳሲ ወደ ሆነ ደረጃ እየደረሰና ምግብ ለመመገብም እየተቸገረች መሆኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ጤንነቷ እንዲስተካከል የኩላሊት እጥበቱን ማድረግ መጀመር እንዳለባትና በመደበኛነት መከታተል እንደሚያስፈልግ ሃኪሞች መክረዋል።

ለረዥም ዓመታት ደቡብ አፍሪካ ውስጥ መኖሯና በተገቢው ሁኔታ የጥገኝነት ሰነድ አለማግኘቷ ጉዳዩ የሚመለከተው የደቡብ አፍሪካ መንግሥት አካል ችግር መሆኑን በመግለጽ፤ የጀመረችው ህክምና እንድታገኝ እንዲደረግ ለፍርድ ቤት የቀረበው ጥያቄ ጊዜ የሚፈልግ ሰለሆነ በዙሪያዋ ባሉ ሰዎች በሚደረገው ጥረት ብቻ ነው በሕይወት እንድትቆይ ማድረግ የሚቻለው ሲሉ አቶ ዳዊት ተናግረዋል።

እጅግ አስፈላጊ የሆነውን የኩላሊት እጥበት አቋርጣ ከሆስፒታሉ እንድትወጣ በፍርድ ቤት የተሰጠው ውሳኔ በደቡብ አፍሪካ በሚገኙ የሰብዓዊ መብት ተቆርቋሪዎች በኩል ከባድ የሰብዓዊነት ጥያቄ ያስነሳ ሲሆን፤ ጉዳዩ ተመልሶ ወደ ፍርድ ቤት እንዲሄድ ያደረጉትም ለዚህ እንደሆነም ተነግሯል።

ደቡብ አፍረካዊ ባለመሆኗና የመኖሪያ ፈቃድ ለዓመታት ማግኘት ባለመቻሏ በሕይወት ለመቆየት እጅግ አስፈላጊ የሆነውን ህክምና አቋርጣ እንድትወጣ በመደረጓ፤ ሕይወቷ አደጋ ላይ እንዲወድቅ እንዳደረገ በመግለጽ ደቡብ አፍሪካ ውስጥና በሌሎችም ቦታዎች የሚገኙ ኢትዮጵያዊያን ለዓለም ድጋፍ እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።

ዓለም ኦርሲዶ ከአስር ዓመት በፊት ወደ ደቡብ አፍሪካ ሄዳ የግል ሥራ በመሥራት እራሷን በማስተዳርና ኢትዮጵያ ውስጥ የሚገኙ ቤተሰቦቿን ትደግፍ እንደነበር በአሁኑ ወቅት አስጠግተዋት ህክማና እንድታገኝ ጥረት እያደረጉ የሚገኙት አቶ ዳዊት ለቢቢሲ ተናግረዋል።