ደቡብ አፍሪካ፡ የመጤ ጠል ጥቃት የማያስቆማቸው ስደተኞች

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
ደቡብ አፍሪካ የሚገኘው የቢቢሲ ዘጋቢ አንድሪው ሃርዲን እንደሚለው በቅርቡ የሌሎች ሃገራት ዜጎች ላይ ከደረሰው ጥቃት በኋላ በአንዳንድ ሃገሪቱ ክፍሎች ''የጉልቤዎች ፖለቲካ'' ተንሰራፍቷል።
ከጥቂት ሳምንታት በፊት የንግድ ማእከል በሆነው የጆሃንስበርግ ምስራቃዊ ክፍል የውጪ ሀገራት ዜጎች የንግድ ተቋማት ላይ በደቦ በተፈፀመ ጥቃት አስር ሰዎች ሕይወታቸውን ያጡ ሲሆን ከሟቾቹ መካከል ሁለቱ የውጪ ዜጎች መሆናቸው ይታወሳል።
ጥቃቱ የተጀመረው የዕቃ ጫኝ መኪና አሽከርካሪዎች ከሌላ ሀገራት የመጡ ግለሰቦች ስራችንን እየነጠቁ ነው በሚል የስራ ማቆም አድማ ካደረጉ በኋላ ነው።
ምንም እንኳ ደቡብ አፍሪካ ባላት የስራ እድል የተነሳ ከተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት በርካታ ወጣቶች ቢፈልሱም በሃገሪቱ ዜጎች ዘንድ ከፍተኛ የሆነ የሥራ አጥ ቁጥር አለ፤ ለዚህም አንዳንድ የሀገሪቱ ዜጎች ከሌላ ሀገር የመጡ ግለሰቦች ሥራቸውን እየነጠቋቸው እንደሆነ ያስባሉ።
በተለይ ደግሞ 'ካትልሆንግ' በምትባለው አነስተኛ ከተማ ያለው ሁኔታ ተመሳሳይ ጥቃቶች ላለመፈጸማቸው ምንም ማስተማማኛ የለም።
በከተማዋ የአካባቢውን ነዋሪዎች በማስተባበር የሚታወቀው ፓፒ ፓፒ '' ድንገት ሊፈነዳ እንደሚችል ቦምብ ማለት ነው'' ሲል ይገልጸዋል ሁኔታውን። በጥቃቱ ህይወቱ ስላለፈው ዚምባብዌያዊ ሲያወራም '' አባረው ከያዙት በኋላ በገዛ መኪናው ውስጥ ነው በእሳት ያቃጠሉት'' ብሏል።
'' እነዚህ አካባቢዎች ከደቡብ አፍሪካውያን ይልቅ በስደተኞች የተሞሉ ናቸው። መንግስት ምንም ነገር አቅዶ እያደረገ አይደለም፤ ድንገት ነው እርምጃ የሚወስደው። ሌላው ቢቀር መሰረታዊ ግልጋሎቶች እንኳን በአግባቡ አልተሟሉም'' በማለት ነዋሪዎቹ ያሉበትን ሁኔታ ያብራራል።
አንድሪው ሃርዲን ቀረብ ብሎ የነጋገራቸው በመንገድ ላይ ቁጭ ብለው የነበሩ ወጣቶች በመጀመሪያ አጋጣሚውን ሌሎች የወንጀል ቡድኖች ተጠቀሙበት እንጂ ጥቃቱ እምብዛም የሚባል ነበር ብለዋል።
ትንሽ ቆይተው ግን የሌላ ሃገር ዜጎች እንዴት ስራ እንዳሳጧቸው ማማረር ጀመሩ።
'' እኔ የሌላ ሃገር ዜጎችን አልጠላም፤ ነገር ግን እነዚህ ሰዎች ማንኛውም አይነት ስራ ከመስራት ወደኋላ አይሉም። ስራውን እጅግ ዝቅተኛ በሆነ ዋጋ ለመስራት ስለሚሞክሩ እኛ እንዴት ስራ እናግኝ'' ሲል አንድ ወጣት ሁኔታውን ያስረዳል።
ሌላኛው ወጣትም በዚሁ ሃሳብ በመስማማት ''በደንብ ሊከፈለው የሚገባ ስራን በትንሽ ዋጋ ይሠሩታል። በዛ ላይ ደግሞ ከራሳቸው ዜጋ ውጪ ሰራተኛ አይቀጥሩም፤ ስለዚህ ለእኛ ስራ ማግኘት በጣም ከባድ ነው'' ብሏል።

የፎቶው ባለመብት, Getty Images
የደቡብ አፍሪካው ፕሬዚዳንት ሲሲል ራማፎሳ በቅርቡ መጤ ጠል በሆኑ የአፍሪካ ዜጎች የደረሰው ጥቃት እጅግ አድርጎ እንደሚያሳፍራቸው በመግለጽ ይቅርታ ጠይቀው ነበር።
ስሙ እንዲጠቀስ ያልፈለገውና አነስተኛ ግሮሰሪውን በትልቅ የደህንነት መጠበቂያ አጥር የከለለው የ 23 ዓመት ኢትዮጵያዊ ስደተኛ '' ጥቃቶቹን ፈርቼ ይህንን ስራ ባቆም ምን እንደምሆን አላውቅም። ምንም አማራጭ የለኝም፤ የት እንደምሄድ እንኳን አላውቅም'' ብሏል።
በደቡብ አፍሪካ ካሉት ከ50 ሚሊየን በላይ ዜጎች በተጨማሪ 3.6 ሚሊየን የሚደርሱ ስደተኞች እንደሚገኙ የሀገሪቱ ስታስቲስቲክስ ቢሮ በቅርቡ ያወጣው መረጃ ያሳያል።
70 በመቶ የሚሆኑት ስደተኞች ደግሞ እንደ ዚምባብዌ፣ ሞዛምቢክና ሌሴቶ ካሉ የጎረቤት ሃገራት ነው የሚመጡት።
ጆሃንስበርግ በሚገኘው ዊትስ ዩኒቨርሲቲ የስደተኞች ጉዳይ ባለሙያ የሆኑት ሎረን ላንዳው እንደሚሉት በአሁኑ ሰአት የአፍሪካ ከተሞች ትልቅ የሆነው የስራ አጦች ቁጥር እያሰቃያቸው ነው።
'' እኔ የአንድ ከተማ አስተዳዳሪ ብሆን በጣም ነበር የምፈራው፤ ምክንያቱም ከተሞቹ መሸከም ከሚችሉት በላይ በሰዎች ተጨናነቀዋል። ሌጎስ፣ ናይሮቢ አልያም ጆሃንሰበርግን ብንወስድ ገና ከዚህ በኋላ እየሰፉ ይመጣሉ። የስራ ፈላጊውም ቁጥር አብሮ ይጨምራል።''
30 በመቶ የሚሆነው ህዝብ ስራ አጥ በሆነባት ሀገር ወጣቶች በአፋጣኝ ስራ ማግኘት ካልቻሉ መጤ ጠልነትና አመጽ የማይቀሩ ነገሮች መሆናቸውን ባለሙያው ያስረዳሉ።
''በተጨማሪም የመንደር ፖለቲከኞች ስልጣናቸውን ለማስጠበቅና በህዝቡ ዘንድ ተወዳጅነት ለማግኘት የፌደራሉ መንግስት የውጭ ሃገር ዜጎችን እንዲያባርር የሚጠይቁ መልእክቶችን በተደጋጋሚ ማሰማታቸው በህዝቡ ዘንድ ሁሌም ቁጣ ይቀሰቅሳል።'' በማለት ጉዳዩ ምን ያክል የተወሳሰበና በአጭር ጊዜ ለመፍታት አስቸጋሪ እንደሆነ ያስረዳሉ ባለሙያው።












