ኮሮናቫይረስ፡ ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የዓለም አገራት ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል- የዓለም ምግብ ድርጅት

የፎቶው ባለመብት, Reuters
ኢትዮጵያን ጨምሮ አስር የዓለም አገራት ከፍተኛ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል ሲል የዓለም ምግብ ድርጅት አስታወቀ።
የተባበሩት መንግሥታቱ ድርጅት ይህንን ያለው ዓለም በኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ምክንያት ለከፍተኛ ረሃብ ትጋለጣለች ሲል ባስጠነቀቀበት ሪፖርቱ ላይ ነው።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ኃላፊ የሆኑት ዴቪድ ቤስሊ እንዳሉት የሚደርሰውን ቀውስ ለማስወገድ ፈጣን እርምጃ መውሰድ ያስፈልጋል።
ይፋ የተደረገው ጥናት እንደሚያሳየው ከሆነ በረሃብ የሚጎዱ የዓለም ዜጎች ቁጥር ከ135 ሚሊየን ወደ 250 ሚሊዮን ከፍ ይላል።
በረሃቡ ይጠቃሉ ተብለው ከተቀመጡ አገራት መካከል አስሩ በግጭት፣ በኢኮኖሚ ቀውስ እና በአየር ጠባይ ለውጥ የተጎዱ መሆናቸውን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ሪፖርት ያሳያል።
ይህ በዓለም የምግብ ቀውስ ላይ የወጣው አራተኛው ዓመታዊ ሪፖርት የመን፣ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ፣ አፍጋኒስታን፣ ቬንዝዌላ፣ ኢትዮጵያ፣ ደቡብ ሱዳን፣ ሱዳን፣ ሶሪያ፣ ናይጄሪያ እና ሄይቲ የረሃብ አደጋ ተደቅኖባቸዋል ብሏል።
ደቡብ ሱዳን ባለፈው ዓመት ከአጠቃላይ ሕዝቧ 61 በመቶ ያህሉ በምግብ እጥረት መቸገሩን ሪፖርቱ ያትታል።
የኮሮና ወረርሽኝ ከመከሰቱም በፊት ቢሆን የምስራቅ አፍሪካ እና ደቡብ እስያ አንዳንድ አገራት በድርቅና በበረሃ አንበጣ ወረራ ምክንያት የምግብ እጥረት ገጥሟቸው ነበር።
ለተባበሩት መንግሥታት የፀጥታው ምክር ቤት በቪዲዮ ኮንፍረንስ ማብራሪያ የሰጡት ቤስሊ "በአግባቡና በፍጥነት ልንሰራ ይገባል" ብለዋል።
"በጣም በቅርብ ወራት ተደራራቢ ድርቅ አስከፊ በሆነ መልኩ ሊገጥመን ይችላል" ካሉ በኋላም " እውነታው ጊዜ ከእኛ ጋር አለመሆኑ ነው" ብለዋል።
አክለውም " ያለን እውቀትና ልምድ እንዲሁም አጋርነትን በመጠቀም ቡድኖችንና ፕሮግራሞችን ወደ አንድ በማምጣት ኮቪድ-19 የሰው ልጅ እና የምግብ ቀውስ እንዳይሆን መስራት እንደምንችል አምናለሁ" ብለዋል።
የዓለም ምግብ ፕሮግራም ከፍተኛ የምጣኔ ሃብት ባለሙያ የሆኑት ሃሪፍ ሁሴን የወረርሽኙ ምጣኔ ሃብታዊ ተጽዕኖ "ቀድሞውንም ህይወታቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ" ሚሊየኖች ላይ ጉዳት የሚያደርስ ነው ብለዋል።
" ለሚሊየኖች በእለት ገቢ ለሚተዳደሩ አሽመድማጅ ነው" ነበር ያሉት በመግለጫቸው ላይ።
" የቤት ውስጥ መቀመጥ ገደብ እና የአለም ምጣኔ ሃብት መቀዛቀዝ በእነዚህ ወገኖች ላይ ጫናቸው የበረታ ነው፤ እንደ ኮቪድ-19 ያሉ ችግሮች ጉዳዩን ወደ ጠርዝ ይገፋዋል፤ ስለዚህ የዓለም ቀውስን ለመመከት በጋራ መስራት አለብን" ብለዋል።













