ኮሮናቫይረስ፡ አሜሪካ ለቀጣዮቹ 60 ቀናት ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ መስጠት ልታቆም ነው

ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህ እርምጃቸው የአሜሪካውያንን የሥራ እድል ይታደጋል ብለዋል

የፎቶው ባለመብት, Getty Images

የምስሉ መግለጫ, ፕሬዝዳንት ትራምፕ ይህ እርምጃቸው የአሜሪካውያንን የሥራ እድል ይታደጋል ብለዋል

ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ በኮሮናቫይረስ ምክንያት በአሜሪካ ለቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ለማግኘት የሚያመለክቱ የውጭ ዜጎች መቀበል ማቆማቸውን ተናገሩ።

ፕሬዝዳንቱ አሻሚ የሆነ ትዊታቸውን ከጻፉና እርምጃቸውን ካሳወቁ በኋላ ውሳኔው የአሜሪካውያንን ሥራ ይታደጋል ብለዋል።

አብዛኛዎቹ የቪዛ ጥያቄዎች በወረርሽኙ ምክንያት ቀድመው የተቋረጡ በመሆኑ አሁን ይህ እንዴት ተግባራዊ እንደሚሆን የታወቀ ነገር የለም።

የፕሬዝዳንቱ ተቺዎች ግን ዶናልድ ትራምፕ የቫይረሱን ወረርሽኝ ምላሽ የሰጡበት መንገድ ስላስተቻቸው ትኩረት ለመስረቅ ያደረጉት ነው ብለዋል።

በአሜሪካ 45 ሺህ ሰዎች ከቫይረሱ ጋር በተያያዘ ሞተዋል።

ዲሞክራቶች በበኩላቸው የትራምፕ አስተዳደር የቫይረሱን ወረርሽኝን ስደተኞችን ለማጥቃት እየተጠቀመበት ነው ሲሉ ተደምጠዋል።

ይህ የፕሬዝዳንቱ እርምጃ የምርጫ ዘመቻቸው አካል የነበረ ቢሆንም የኮሮና ወረርሽኝ መከሰት እንዲቀዛቀዝ አድርጎት ነበር።

ፕሬዝዳንት ትራምፕ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ላይ ይህንን ውሳኔያቸውን ረቡዕ እለት ፊርማቸውን እንደሚያኖሩበት ተናግረዋል።

ይህ እገዳ የአሜሪካ ምጣኔ ሃብት መሻሻል እስኪያሳይ ድረስ እንደሚቆይ ፕሬዝዳንቱ ጨምረው ገልፀዋል።

ሰኞ እለት የትኛውንም ወደ አሜሪካ የሚደረግ ጉዞ ለማገድ ቃል ከገቡ በኋላ ከአንዳንድ የቢዝነስ ሰዎች ተቃውሞ በመሰማቱ የመጀመሪያ እቅዳቸውን ሰርዘውታል።

የፕሬዝዳንቱ የቀደመ ውሳኔ በግብርና ላይ በጉልበት ሥራዎች ላይ ለመሳተፍ እንዲሁም ከፍተኛ የቴክኖሎጂ ባለሙያ ሆነው ለሚቀጠሩ ጊዜያዊ ቪዛ ለመስጠት አያስችልም ሲሉ ነበር ቅሬታቸውን ያቀረቡት።

በአሜሪካ ከኮሮናቫይረስ ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ ከ20 ሚሊዮን በላይ አሜሪካውያን ሥራቸውን አጥተዋል፤ ፕሬዝዳንት ትራምፕም እነዚህ አሜሪካውያን ተመልሰው ሥራ እንዲይዙ የማድረግ "ኃላፊነት አለብን" ብለዋል።

አክለውም " በቫይረሱ ምክንያት ሥራቸውን ያጡ አሜሪካውያንንን በሌሎች ስደተኞች ሥራቸውን እንዲነጠቁ ማድረግ ስህተትም ነው ፍትሃዊም አይደለም" ብለዋል።

በተጨማሪም "ለአሜሪካውያን ሰራተኞች መከላከል ነው የምንፈልገው፤ ወደፊት ደግሞ የበለጠ እንከላከላለን" በማለት ለዚህ እርምጃ አንዳንድ የሚዘለሉ ነገሮች እንደሚኖሩ ፍንጭ ሰጥተው ነበር።

ይህ የፕሬዝዳንቱ ውሳኔ ግን የሕግ ተግዳሮት ይገጥመዋል የሚሉ አልጠፉም።

እንደጆንስ ሆፕኪንስ አሁናዊ መረጃ ከሆነ አሜሪካ በኮሮናቫይረስ ክፉኛ ከተጎዱ አገራት መካከል ስትሆን እስካሁን ድረስ 820 ሺህ ሰዎች በቫይረሱ መያዛቸው ተመዝግቧል።

የአሜሪካ ግሪን ካርድ ሕጋዊ ቋሚ የመኖሪያ ፈቃድ ሲሆን ለአሜሪካ ዜግነት ለማመልከት እድል ይሰጣል። አሜሪካ በየዓመቱ አንድ ሚሊየን ግሪን ካርድ ትሰጣለች።

ኮሮና